በደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ የተፈጠረው አለመረጋጋት ለቀናት መቀጠሉ ተሰማ

በደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ የሚገኙ ተማሪዎች

የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ''በማንነታችን ምክንያት ጥቃት እየተሰነዘረብን ነው'' ሲሉ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ብሄር ተኮር ጥቃቶች እየተሰነዘሩብን ነው የሚሉት ተማሪዎቹ፤ በዩኒቨርሲቲው የተከሰተው አለመረጋጋት ለቀናት መዝለቁን ተናግረዋል።

''ወንድ ተማሪዎች በአንድ ህንጻ ሴት ተማሪዎችም ደግሞ በሌላ ህንጻ ውስጥ ሆነን በአንድ ቦታ እንድንቆይ ተደርገናል። ምግብ እንኳን ከበላን ዛሬ ሦስተኛ ቀናችን ነው። ችግራችሁ ምንድነው ብሎ የጠየቀን አካል እንኳ የለም'' በማለት ስሟ እንዳይጠቀስ የጠየቀች የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ለቢቢሲ ተናግራለች።

በዩኒቨርሲቲው ተከስቶ በነበረ ግጭት ጉዳት የገጠማቸው ተማሪዎችም ከህንጻው እንዳይወጡ ስለመደረጋቸው ተማሪዎቹ ይናገራሉ።

የሕክምና ባለሙያው ታካሚዎችን በመግደል ዘብጥያ ወረደ

የአምልኮ ቦታ የተነፈጉት የአክሱም ሙስሊሞች

የቱሉ ፈራ ደጋግ ኢትዮጵያዊ ልቦች

ከዩኒቨርሲቲው ሸሸቶ ወደ አዲስ አበባ እንደመጣ የሚናገረው ሌላው ተማሪ፤ በዩኒቨርሲቲው የተሰማሩ የፌደራል ፖሊስ እና የአማራ ክልል ጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ በተማሪዎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ማስቆም አልቻሉም ይላል።

''እነሱ [የጸጥታ አስከባሪዎች] ምንም ማድረግ አልቻሉም። ተማሪዎችን እንደበድባለን ብለው ሲነሱ ይማጸኗቸዋል እንጂ ምንም አይነት እርምጃ አይወስዱም። በቁጥጥር ሥር ቢያውሏቸውም ወደ ህግ አካል አያቀርቧቸውም'' ይላል።

በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ አለመረጋጋት ከተከሰተ ሁለት ሳምንታት የተቆጠሩ ሲሆን ከባለፈው እሁድ ወዲህ ግን ግጭቱ እየጠነከረ እንደመጣ ተማሪዎቹ ያስረዳሉ።

የግጭቱ መነሾ ይህ ነው ሊባል እንደማይችል የሚናገሩት ተማሪዎቹ፤ በአንድ ብሔር ተወላጅ ተማሪዎች ላይ ድብደባ መፈጸም እንደተጀመረ ያነጋገርናቸው ተማሪዎች ያስረዳሉ።

''እየደረሰብን ያለውን ጥቃት ሊያስቆምልን የሚችል አካል ባለመገኘቱ ሰኞ ዕለት ምን ማድረግ እንደሚኖርብን ለመነጋገር ውይይት ማድረግ ጀመርን'' በማለት ኢላማ ሆነናል ካሉት ተማሪዎች አንዱ ያስረዳል። ስብሰባ እያደረጉ በሚገኙበት ወቅት የተደራጁ ተማሪዎች ድንጋይ መወርወር መጀመራቸውን ይሄው ተማሪ ለቢቢሲ ተናግሯል።

የደብረ ብርሃን ከተማ ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ ምክትል ኮማንደር ዘነበ ገብሩ በበኩላቸው ''በሁለት ሰዎች መካከል የተፈጠረ ግጭት ወደ ቡድን ጸብ ተሸጋገረ'' በማለት የግጭቱን መንስዔ ይገልጻሉ።

የኦሮሚያ ክልል ተወላጅ የሆኑ ተማሪዎች ካለባቸው ስጋት የተነሳ ምግብ ለመመገብ ወደ ካፍቴሪያ እየሄዱ አይደለም ሲሉም የተማሪዎቹን ሀሳብ ትክክለኛነት ይናገራሉ።

ምክትል ኮማንደር ዘነበ በተማሪዎቹ ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንዳልደረሰባቸው እና የሚገኙባቸው ህንጻዎችን በጸጥታ ኃይሎች ተከቦ እንደሚገኝ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

''ድንጋይ ሲወረውሩ የተያዙ 10 ተማሪዎች ስማቸው በዩኒቨርሲቲው ከተመዘገበ በኋላ ምክር ተሰጥቷቸው ተለቀዋል። አሁን በእስር ላይ የሚገኝ ተማሪ የለም'' በማለት ያስረዱት ኮማንደሩ፤ ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ከግቢው ውጪ ያሉ አንዳንድ አካላትም ጥቃት አድርሰውብናል የሚለውን የተማሪዎች ክስ በፍፁም ሲሉ ያጣጥላሉ።

''ከግቢ ውጪ መጥቶ ጥቃት የሰነዘረ በፍጹም የለም'' አክለውም ''በሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎች ይገኛሉ። ከውጪ ገብቶ ችግር መፍጠር የሚፈልግ ሊኖር ይችላል። እስካሁን ግን በእኛ በኩል አልተረጋገጠም። የኦሮሞ እና የአማራ ብሄር ተወላጆች እንዲጋጩ የሚፈልግ አካል እንዳለ ይሰማናል'' በማለት ምክትል ኮማንደሩ ይናገራሉ።

ያነጋገርናቸው ተማሪዎች በዚህ ሁኔታ ትምህርት መቀጠል እንደሚከብዳቸው ተናግረው ወደ ቀያቸው መመለስ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

የዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎች ስበሰባ ላይ ነን በማለታቸው ሃሳባቸውን ማካተት አልቻልንም።

በዩኒቨርሲቲው በተፈጠረው ግጭትና ውጥረት ትምህርት የተቋረጠ ሲሆን አመሻሽ ላይ ባገኘነው መረጃ መሰረት ዛሬ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች እና ከመንግሥት ባለስልጣናት ጋር ውይይት ሲያደረጉ መዋላቸውን ሰምተናል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ