የሕክምና ባለሙያው ታካሚዎችን በመግደል ዘብጥያ ወረደ

የሕክምና ባለሙያው ታካሚዎችን በመግደል ዘብጥያ ወረደ Image copyright Reuters

ጀርመናዊው የቀድሞ ነርስ የ85 ታካሚዎችን ነብስ በማጥፋት ወንጀል ጥፋተኛ ተባለ።

በምስራቅ ጀርመን በሚገኙ ሁለት ሆስፒታሎች ይሠራ የነበረው ነርስ የ85 ታካሚዎችን ነብስ አጥፈተሃል ተብሎ ተፈርዶበታል።

ኒየልስ ኾግል የተባለ ግለሰብ በሁለት ሰዎች ግድያ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት ማረሚያ ነበር የሚገኘው።

ግለሰቡ በጀርመን የቅርብ ዓመታት ታሪክ በርካታ ሰዎችን የገደለ ሰው እንደሆነ ይገመታል።

የባህል ሃኪሙ የተማመነበት ጥይት ማርከሻ ባለመስራቱ ሞተ

'የሴቶች ቫያግራ' በአፍሪካዊቷ ሃገር

እ.ኤ.አ ከ1999 እስከ 2005 ባለው ጊዜ የልብ መድኃኒት ከሚፈቀደው በላይ በመስጠት ነው ታካሚዎች እስከወዲያኛው እንዲያሸልቡ ያደረገው ተብሏል።

ሰውዬው ግድያውን የፈፀመው ታካሚዎችን ለማዳን ነው ቢልም ታማሚዎቹ ከፈውስ ይልቅ ሞት እጣ ፈንታቸው ሆኗል።

የፍርድ አደባባይ ላይ የቀረበው የ42 ዓመቱ ኾገል የታካሚዎችን ቤተሰቦች ይቅር በሉኝ ሲል ተማፅኗል። ''ባለፉት ዓመታት ላደረስኩባችሁ በደል በሙሉ ከልብ ይቅርታ እንድታደርጉልኝ እጠይቃለሁ'' ቢልም በርካቶች የአዞ እንባ ሲሉ ኮንነውታል።

ቀድሞ ማረሚያ ቤት ከገባበት የሁለት ሰዎች ግድያ ጋር በድምሩ 100 ሰዎችን ገድሏል። ፖሊስ ግን ቁጥሩ ሳይልቅ አይቀርም የሚል ጥርጣሬ አለው።

የኒየልስ ኾግል ሰዎችን የመግደል አባዜው እንዲገታ የሆነው እ.ኤ.አ 2005 ላይ በሃኪም ያልታዘዘ መድሃኒት ለታካሚው ሲሰጥ በመገኘቱ ነበር። በዚህም ተግባሩ በግድያ ሙከራ 7 ዓመታትን በእስር እንዲያሳልፍ ተፈርዶበታል። በሌሎች ተመሳሳይ ክሶች ደግሞ እ.ኤ.አ 2015 ላይ የእድሜ ልክ እስራት ተበይኖበት ነበር።

ሰውዬው 55 ሰዎችን መግደሉን ፍርድ ቤት ፊት ቀርቦ አምኗል።

ዜናውን የሰሙ ጀርመናዊያን እስካሁን ከድንጋጤ የወጡ አይመስሉም።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ