ሎዛ አበራ፡ «የኔ ትውልድ ታሪክ እንደሚሠራ ትልቅ እምነት አለኝ»

ሎዛ አበራ ከደደቢት ጋር ዋንጫ ባነሳችበት 2010 ዓ.ም. ኮከብ ጎል አስቆታሪ ነበረች Image copyright Twitter/Loza Abera
አጭር የምስል መግለጫ ሎዛ አበራ ከደደቢት ጋር ዋንጫ ባነሳችበት 2010 ዓ.ም. ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ነበረች

ሰባት ልጆች ላፈሩት እናት እና አባቷ አምስተኛ ልጅ ናት፤ ተወልዳ ያደገችው የከንባታ ጠምባሮ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ዱራሜ ነው።

ሶስት ወንድሞች አሏት፤ ሁለቱ ታላቆቿ አንድ ደግሞ ታናሿ። ገና ልጅ ሳለች ነበር በኳስ ፍቅር የወደቀችው። ባደገችበት ሠፈር ካሉ ወንድ እኩዮቿ ጋር እየተጋፋች ኳስን ከመረብ [እርግጥ የሠፈር ሜዳ መረብ ባይኖረውም] ማገናኘት ያዘች።

ጉዞዋ ሠፈራቸው ከሚገኘው ሌሊሶ ሜዳ እስከ ብርቅዬው አዲስ አበባ ስታድዬም እንዲሁም ስዊድን ያደርስታል ብሎ የገመተ ላይኖር ይችላል፤ እርሷ ግን ውስጧ ነግሯታል።

ሎዛ አበራ

ሴት ልጅ ማዕድ ቤት እንጂ ከወንዶች እኩል ውስጧ የሻተውን ማድረግ በማትችልበት ማሕበረሰብ ውስጥ ብታድግም ሕልሟን ከማሳካት አላገዳትም።

እንደው ከወንዶች ጋር መጫወት አይከብድም? «እኔ ምንም አልከበደኝም ነበር። እንደውም ወንዶች እኔ ያለሁበት ቡድን ውስጥ ለመጫወት ይጣሉ ነበር''።

የሎዛ ፕሮፌሽናል ኳስ ተጫውነት ጉዞ የተጀመረው የከንባታ ዞንን ወክላ ስትጫወት ባይዋት መልማዮች አማካይነት ነው። ከዚያ ጉዞ ከዞን ወደ ክልል ሆነ። ደቡብ ክልልን ወክላ ለመላው ኢትዮጵያ ውድድር እንድትሳተፍ ሆነ። ጨዋታው ደግሞ የነበረው አዳማ ላይ።

የሆንግ ኮንግን የዘር መድልዎ የሚፋለሙ አፍሪካዊያን እግር ኳስ ተጫዋቾች

የያኔው የሐዋሳ ሴቶች እግር ኳስ ቡድን አሠልጣኝ የሆነው ዮሴፍ ገብረወልድ [ወፍዬ ይሉታል ልጆቹ ሲጠሩት] ነበር ሎዛን የመለመላት። ፈጣኑ የሎዛ ጉዞ ኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ደርሷል።

ምንም እንኳ ሎዛ ከሐዋሳ ጋራ ዋንጫ ባታነሳም እዚያ በቆየችባቸው ሁለት ተከታታይ ዓመታት የክለቡ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ነበረች። ሐዋሳም ቢሆን ሁለቱንም ዓመታት ፕሪሚዬር ሊጉን 3ኛ ደረጃ በመያዝ ነው ያጠናቀቀው።

አሁን ደግሞ ጉዞ ከሐዋሳ ወደ ደደቢት። ምንም እንኳ አሁን ደደቢት የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ቢከስምም በጊዜው አጅግ ድንቅ ብቃት ያሳዩ ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች ስብስበ ነበር።

«በደደቢት አራት ዓመታትን ቆይቻለሁ፤ እስከ አምና ማለት ነው። በእነዚህ ዓመታት በተከታታይ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ነበርኩኝ። እንደገና ሶስት ተከታታይ ዓመት ደግሞ የሴቶች ፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮና ነበርን። ግን አሁን ደደቢት ፈርሷል፤ እኛም በተፈጠረው ነገር በጣም አዝነናል።»

ጉዞ ወደ ስዊድን

ሎዛ ደደቢት ከመፍረሱ በፊት ነበር ለሙከራ ወደ ስዊድን ያቀናችው። «ደደቢት ነበርኩኝ። ፕሪሚዬር ሊጉ ሊጠናቀቅ ሁለት ጨዋታ ሲቀሩት እኔ ወደ ስዊድን አቀናሁ» ትላለች።

ግን እንዴት ወደ ስዊድን ልታቀና ቻለች?

«ስዊድናዊ ነው ሰውዬው። ላርስ ይባላል። ባለቤቱ ኢትዮጵያዊት በመሆኗ ይመጣ ነበር። ስለኔ ሲነግሩት ጊዜ ማዬት አለብኝ ብሎ ስጫወት ተመለከተኝ። ከዚያ እኔና ቱቱ [የብሔራዊ ቡድኑ የቀድሞ አምበል ቱቱ በላይ] ስዊድን ሄደን የሁለት ወር የሙከራ ልምምድ እንድናደርግ አመቻቸልን። ስዊድን የሚገኙ ክለቦች ውስጥ [ሮዘንጋርድ እና ፒቲያ አይ ኤፍ] ለአራት ወራት ያክል ቆየን። ከዚያ በኋላ የስዊድን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፈቃድ ሰጡን። ፊርማ ያኖርንለት ክለብ ግን አልነበረም። ልክ የስዊድን የሴቶች 'ቶርናመንት' ሲጠናቀቅ ተመለስን።»

ከዚያስ?

«ጥር ስዊድን የሴቶች ውድድር የሚጀምርበት ወር ነበር። እኛ ግን ተመልሰን መሄደ አልቻልንም። ምክንያቱ ደግሞ ፋይናንስ ነው። ከአውሮፓ የምትመጣ ሴት ሲያስፈርሙ ተጨማሪ ወጪ የለባቸውም። ከሌላ አህጉር ለምትመጣ ተጫዋች ግን ቀረጥ [የስራ ፈቃድ ወጭ] መክፈል ግድ ነው። ክለቡ ይህንን ማድረግ አልቻለም። እንጂ የችሎታ ወይም የአቅም ማነስ ጉዳይ አልነበረም።»

«ይገርምሃል እነሱ 1ኛ ደቂቃ ላይም 90ኛው ደቂቃ ላይ ያላቸው አቅም ተመሳሳይ ነው። እኛ ችግራችን ኳስ አለመቻል አይደለም፤ ችግራችን ፊትነስ ነው» በስዊድኖች የቀናሁት በዚህ ነው ትላለች ሎዛ።

ሎዛ ከስዊድኑ ክለብ በፊት ለአንድ ወር ሙከራ ልምምድ ወደ ቱርኩ አንታልያስፖር ማቅናቷ የሚዘነጋ አይደለም። የቱርኩ ክለብ ያቀረበላት ክፍያ ግን፤ እንደ ሎዛ አገላለፅ 'ከኢትዮጵያም ያነሰ' ነበር።

ሉሲ

የሎዛ የብሔራዊ ቡድን ጉዞ ከክለብ ቀድሞ የሚመጣ ነው።

«ወቅቱ የሴቶቸ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪቃ ዋንጫ ያለፈበት ነበር። 'ሉሲ ተስፋ' ተብሎ 70 ገደማ ታዳጊዎች ለአንድ ወር ያክል ሥልጠና እንድናደርግ ተጠራን። ከመሃከላችን 8 ልጆች ለብሔራዊ ቡድን ተመረጡ። እኔ አንዷ ነበርኩ። ይህ የሆነው ገና ለሐዋሳ መጫወት ከመጀመሬ በፊት በነበረው ክረምት ላይ ነው።»

ሎዛ ለብሔራዊ ቡድን እንደተመረጠች ከቡድኑ ተቀንሳ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ገና ልጅ ነሽ በመባሏ ነበር። ከአንድ ዓመት በኋላ ግን በአሠልጣኝ ስዩም ከበድ ቡድን ውስጥ መካተት ቻለች።

23 የብሔራዊ ቡድን ጎሎች በዓለም አቀፍ መድረክ! ሎዛ ይህን በማሳካት የምንጊዜም የሉሲ ከፍተኛ ጎል አግቢነቱን ተቆጣጥራዋለች።

ምንም እንኳ ሎዛ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ዋንጫ ባትበላም፤ ሜዳልያ ባታጠልቅም፤ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጋር የነበራትን ቆይታ አትዘነጋውም። ከ20 ዓመት በታች ሉሲ ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ሶስቱን ማጣሪያዎች ካለፈች በኋላ ማለፍ ሳትችል ብትቀርም ሎዛ ራሴን የፈተሽኩበት የማልረሳው ውድድር ነው ትላለች።

የአውሮፓን እግር ኳስ የሚዘውረው ሃብታሙ 'ደላላ'

ካፍ የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ድጋሚ እንዲካሄድ አዘዘ

እንደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማልያን ለብሶ ደጋፊ ፊት መጫወት ምን ዓይነት ስሜት ይሰጥ ይሆን?

«በጣም ደስ....የሚል ስሜት አለው። ሕልሜም ነበር ይህንን ማሳካት። ስታድዬም ገብቶ ሃገርን ወክሎ መጫት። የመጀመሪያ ጊዜ በጣም ደስ የሚል ስሜት ነው የተሰማኝ። በቃ ይሄ በቃላት የማትገልፀው ዓይነት ስሜት አለ አይደል?. . . ጎል ማስቆጠር ደግሞ ሌላ ደስታ በቃ።»

ሎዛ የእሷ ትውልድ ብሔራዊ ቡድን ታሪክ ይሠራል የሚል እምነት አላት። «ሁሌም የማስበው ነገር ነው። ዓላማዬ ሃገሬን ወክዬ የአፍሪካ ዋንጫ መጫወት፤ የሴካፋ ሻምፒዮን መሆን ነው። እንደ ሃገር በምንጫወትባቸው መድረኮች ላይ የኔ ትውልድ ትልቅ ውጤት እንደሚያመጣ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ። ከእግዚአብሔር ጋር ይሳካል የሚል እምነት አለኝ።»

Image copyright Twitter/Loza Abera

ክፍያ

አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚያበሉ ሥራዎች ውስጥ አንዱ እግር ኳስ ነው አሉ [የወንዶቹ ማለት ነወ]። የሴቶቹስ? የእነ ሎዛ ክፍያ ልከ እንደወንዶቹ አፍን በመዳፍ የሚያስከድን ይሆን?

«ኧረ በፍፁም አይገናኝም። ሰማይ እና ምድር ነው። እርግጥ እግዚአብሔር ይመስገን ክፍያችን ከቀድሞው የተሻለ ነው። ከጊዜ ጊዜም እየተሻሻለ መጥቷል። ግን ከወንዶች ጋር ስናነፃፅረው በፍፁም አይገናኝም። በፍፁ....ም ማለት ነው። በፊት የፊርማ ተብሎ ነበር የሚሠጠን፤ አሁን ግን በወር ተከፋፍሎ በደሞዝ መልክ ነው ምናገኘው። ይህ የገንዘቡን መጠን ያነሰ ያደርግብናል። ስለክፍያ ብዙ ጊዜ ተብሏል። እንደውም የሴቶች እግር ኳስ ክፍያ እየወረደ እንዳይሄድ ነው ስጋታችን።»

ሎዛ ዘንድሮ ከአዳማ ጋር ዋንጫ ማንሳት ችላለች። ምንም እንኳ ሊጉን ዘግየት ብላ ብትቀላቀልም [ስዊድን በመጓዟ ምክንያት] ኮከብ ጎል አስቆጣሪነቱን ሁለተኛ በመሆን አጠናቃለች።

ከሌሊሶ ሜዳ እስከ ስዊድን

ሎዛ በዙሪያዋ የነበሩ ሰዎች አሁን ለደረሰችበት ደረጃ ያላቸው ሚና ትልቅ እንደሆነ ተናግራ የምትጠግብ አትመስልም። ከቤተሰቦቿ እስከ ወፍዬ አሠልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ፤ ከደደቢት አጋሮቿ እስከ ስዩም ከበደ...ብቻ ስማቸውን ዘርዝራ የማትጨርሳቸው ሰዎች ምስጋና ይገባቸዋል ትላለች።

ከሠፈሯ 'ሌሊሶ' ሜዳ አሁን ያለችበት ትደርሳለች ብለው ብዙዎች ባይገምቱም እሷ ግን ልጅ እያለሁ እንኳ የሚታየኝ በእግር ኳስ ሃገሬን ወክዬ ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ስጫወት ነው ትላለች።

«ከምንም ነገር በፊት ፍላጎት ይቀድማል። እግር ኳስ መጫወት ከሆነ ፍላጎታችን፤ ያንን ፍላጎታችንን ለማሳካት ሳይደክሙ መሥራት። ሌላም ከሆነ እንደዚሁ። ተስፋ ሳይቆርጡ እድርሳለሁ ያሉበት ቦታ እንደሚደረስ ሁሌም ለአእምሮ መናገር፤ ራስን ማሳመን፤ ሥራን ማክበር ማለትም አንድ ሙያ የሚጠይቀውን ዲሲፕሊን መከተል ያስፈልጋል» የሎዛ መልዕክት ነው።

እኛም የሷ ትውልድ ሉሲ፤ ድል አምጥታ ከመቀመጫችን ተነስተን የምንቦርቅበት ጊዜ በጉጉት ከመጠበቅ እና ከመመኘት ወደኋላ አንልም።

ፌዴሬሽኑ፡ «የቡና እና መቀለ ደጋፊዎች ባሉበት ጨዋታ ሊካሄድ አይችልም»