ህንድ ውስጥ ህፃኗን ደፍረው የገደሉ በእድሜ ልክ እስራት ተቀጡ

ብዙዎች በጉዳዩ ከፍተኛ ሀዘን ተሰምቷቸዋል Image copyright Getty Images

በህንድ በምትተዳደረው ካሽሚር ግዛት ውስጥ የስምንት አመት ልጅ ደፍረው፣ አሰቃይተው የገደሏት ሶስት ግለሰቦች የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ መረጃ አደባብሰው አጥፍተዋል የተባሉ ሶስት ፖሊሶች በአምስት አመት እስር እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ ወስኗል።

ከአርብቶ አደር ቤተሰብ የተወለደችው ህፃኗ ካቱዋ ከተማ አካባቢ በሚገኝ ጫካ ውስጥ ተገድላ የተገኘችው ባለፈው አመት ነበር።

የልጅቷ መገደል በከፍተኛ ሁኔታ የሚዲያ ሽፋን ያገኘው የሂንዱ ቀኝ ክንፍ አክራሪዎች በወንጀሉ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን እስር ተቃውመው ሰልፍ በማድረጋቸው ነበር።

የተደፈረችው የ3 ዓመት ህፃን በአስጊ ሁኔታ ትገኛለች

የመንግሥት የቀድሞ ኃላፊን ጨምሮ አራት ፖሊሶችና አንድ እድሜው ያልደረሰ ህፃን ልጅ በአጠቃላይ ስምንት ግለሰቦች ተጠርጥረው ተይዘው ነበር። አንደኛው ግለሰብ በነፃ ሲለቀቅ የህፃኑ ጉዳይ ለብቻ እንደሚታይ ተዘግቧል።

ሁሉም ከወንጀሉ ነፃ እንደሆኑ ክደው ነበር።

ደሴ፡ የሰባት ዓመት ህፃን ገድሏል በተባለው የእንጀራ አባት ምክንያት ቁጣ ተቀሰቀሰ

የልጅቷ ጉዳይ በከፍተኛ ሁኔታ ሽፋን ከማግኘቱ አንፃር አገሪቷንም ከአስራ ሁለት አመት በታች ለሚደፈሩ ህፃናት የሞት ፍርድን የሚደነግግ አዲስ ህግ እንድታሳልፍ አድርጓቷል።

ነገር ግን የሞት ፍርዱ የመጨረሻ ውሳኔ የሚወሰነው በዳኞቹ ይሆናል።

በባለፈው አመት ጥር ወር ላይ የጠፋችው የስምንት አመቷ ህፃን ከሶስት ሳምንት በኋላ ስትገኝ ሰውነቷ በማይሆን ሁኔታ ነበር።

እንደ ወንጀል መርማሪዎች ከሆነ ህፃኗ በአካባቢው በሚገኝ የእምነት ቦታ ላይ በሚገኝ ቦታ ማደንዘዣ እየተሰጣት እንደቆየች ነው። ክሱ እንደሚያሳየው ለቀናት የተደፈረች ሲሆን፤ ከመገደሏም በፊት በከፍተኛ ሁኔታ አካላዊ ድብደባ እንደደረሰባት ነው።

ህፃኗ ኢላማ የተደረገችው በአካባቢው የሚገኙ የጉጃር ጎሳዎችን ከአካባቢው ለቀው እንዲወጡ ለማሰገደድ እንደሆነም ተገልጿል።

የተነጠቀ ልጅነት

"በወንድሜ ለአምስት ዓመታት ተደፍሬአለሁ"

በህንድ በየደቂቃው አስራ አምስት ሴቶች እንደሚደፈሩ ከሶስት አመት በፊት የወጣ መረጃ የሚያሳይ ሲሆን በተለይም በህፃናት ላይ የሚደርስ ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው።

የቢቢሲ ጊታ ፓንዲ ከደልሂ እንደገለፀችው ህንድ በአለም ላይ በህፃናት በሚደርስ ወሲባዊ ጥቃት አንደኛ ብትሆንም ጉዳዩ ችላ የተባለና ሪፖርት የማይደረጉ ጥቃቶችም ከፍተኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው።

Image copyright Getty Images

የቢቢሲዋ ዘጋቢ ዲቭያ አርያ የህፃኗን እናት ባናገረችበት ወቅት

የህፃኗን እናት ሳገኛት ከትልቋ ልጇና ከሌሎች ቤተሰቦች ጋር ተሰባስባ ነው።

ፍየልና በጎቻቸው በአካባቢያቸው የሚገኘውን ሳር እየጋጡ የነበረ ሲሆን እኔ ሳገኛቸው ፍርዱን አልሰሙም ነበር።

የስድስቱንም የፍርድ ውሳኔ ለእናቷ ስነግራት ምርር ብላ አልቅሳ ይህንን የምስራች ስላበሰርኳት መረቀችኝ።

ፍርድ ቤቱ የሚገኝበት ቦታ ለመሄድ አቅማቸው ስለማይፈቅድ ባሉበት ቦታ በተስፋ እየጠበቁ ነበር።

"በፍትህ የማምን ሰው ነኝ እናም አምላክም ጥንካሬውን ስጠኝ" ብላለች

በተለይም ለልጃቸው ህይወት በዋነኝነት ተጠያቂ ያሏቸውን ሁለቱን ግለሰቦች የሞት ፍርድ ካልተፈረደባቸው ይግባኝ እንደሚሉ ተናግራ ነበር "ለልጃችን ፍትህ እስከምናገኝ እኔም ሆነ ባለቤቴ እህልም ሆነ ውሃ አንቀምስም" ብላለች

የ15 አመቷ የህፃኗ ታላቅ እህት በበኩሏ እሷም ሆነ የእድሜ እኩዮቿ የሂንዱ እምነት ተከታይ ወንዶችን በመፍራት ከትልቅ ሰው ጋር ካልሆኑ ብቻቸውን የትም እንደማይሄዱ ተናግራለች።