ጠቅላይ ሚነስትር ዐብይ አህመድ በአክሱም ምን ተጠየቁ?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድና ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል Image copyright Prime minister facebook page

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በትናንትናው ዕለት የአክሱም ከተማን የጎበኙ ሲሆን፤ በቆይታቸውም በአክሱም ዩኒቨርስቲ በተፈጠረው ችግር ዙሪያ፣ በአክሱም ሃውልቶች ላይ ስለተጋረጠው አደጋ ከከተማው ከተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ጋር ተወያይተዋል።

በፌደራል መንግሥቱና በትግራይ ክልል መካከል ያለው ቀዝቃዛ ግንኙነት ጋር ተያይዞ ጉብኝታቸው አነጋጋሪም ሆኖ የነበረ ሲሆን ነዋሪዎቹም በተለያየ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚንሸራሸሩ ጥያቄዎችን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርበውላቸዋል።

በ2018 ጎልተው የታዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

ከተጠየቁት ጥያቄዎች መካከልም የተወሰኑትን ጥያቄዎች የመለሱ ሲሆን ለአንዳንዶቹም ምላሽ እንዳልሰጡ ቢቢሲ ያናገራቸው የውይይቱ ተሳታፊዎች ገልፀዋል።

የመሰረተ-ልማት ችግሮች

አክሱም ከተማ የቱሪስት መናኸሪያ እንደመሆኗ መጠን የውሃ ችግር በተደጋጋሚ ያጠቃታል። ይህ የማይቀረፈው ለምንድን ነው? እሳቸውም በምላሹ ይህ የፌደራል መንግሥት እንደማይመለከተውና ለዚህ ምላሽ መስጠት ያለበት ክልሉ ነው ብለዋል።

ኢትዮ-ኤርትራ ድንበር መዘጋት

ለዓመታት ተፋጠው የነበሩት ኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላም መፈጠር መልካም ሆኖ እርቁ ግን ያልተጠናና መሰረታዊ ሂደት ያልነበረበት ይመስላል ተብለው የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኤርትራ ውስጥ አዳዲስ ክስተቶች እየታዩ ስለሆነ እነዚህ ጉዳዮች እስኪስተካከሉ ከኤርትራ መንግሥት በኩል የተወሰደ እርምጃ እንደሆነ ተናግረዋል።

ቀጣዩ ምርጫ

ምርጫው የሚራዘምና የማይካሄድ ከሆነ የእርስዎ ተቀባይነት ስለሚያበቃ ምንድነው እያሰቡ ያሉት፤ ይህስ ነገር አገሪቷን አደጋ ውስጥ አይከትም ወይ የተባሉ ሲሆን እሳቸውም እንደ ግንባር ምርጫው እንዲካሄድ ፍላጎት ቢኖርም፤ በምርጫው ላይ የጋራ መግባባት ላይ መደረስ ስላለበት ከሁሉም ፓርቲዎች ጋር በጋራ መመመከር አለበት ብለዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የምርጫ ቦርዱ እንደ አዲስ እየተዋረ ሲሆን ከምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ኃላፊነት የምርጫ ቦርድ ነው ብለዋል።

የኢህአዴግ ፓርቲ ቀጣይነት

ሃገሪቱ ውስጥ እየተከናወኑ ባሉ ውሳኔዎች ላይ ኢህአዴግ እንደ ግንባር እየተንቀሳቀሰ አይመስልም። በእውነቱ ኢህአዴግ አለ ወይ? የሚል ጥያቄ የተወረወረላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢህአዴግ ፓርቲ እስካሁን አለ። "በቀጣይም አብረን ተያይተን የምናደርገው ይሆናል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ኢህአዴግ ባይኖር እዚህ አንመጣም ነበር፤ ስላለንም ነው የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደብረፅዮንም እየተቀበለኝ ያለው" ብለዋል።

አንድ ብሔር ላይ ያነጣጠረጥቃት

ለውጡን ተከትሎ የትግራይ ብሔር ተወላጆች ብቻ እስር ቤት የሚገኙና በክስ ላይ የሚገኙ ሲሆን እነዚህ ሰዎች ታሪክ የሰሩ፤ ለዚች ሃገር ባለውለታ የሆኑ አሉና ይህንን ነገር እንዴት ነው የሚያዩት? ተብለዋል። ይህ ጉዳይ ህግ የያዘው ስለሆነ በህግ አግባብ የሚታይ ይሆናል ብለዋል።

ግንቦት 20 በአገራዊ ሁኔታ ለምን አይከበርም?

ኢህአዴግ የደርግ ሠራዊት ያሸነፈበት ዕለት ግንቦት 20 በዘንድሮው ዕለት አልተከበረም። አንዳንድ ጉዳዮች ሲታዩም ደርግ እንደገና ያንሰራራበት ሁኔታም ይታያል። ተብለው የተጠየቁት ጠቅላዩ ምላሽ አልሰጡም።

"ማንም ቢሆን ኢትዮጵያን ለብቻዬ ሰራኋት ሊል አይቻለውም" ጠ/ሚ ዐብይ

ከዚህም በተጨማሪ ነዋሪዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄያቸውን ተቀብለው ሐውልቱን በማደስ ዙሪያ ለመነጋገር መፍቀዳቸውና ወደስፍራው በመምጣታቸ ያላቸውን አድናቆትም ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአክሱምን ሃውልት የጎበኙ ሲሆን፤ ከእሳቸው በተጨማሪም የመከላከያ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንን አብረዋቸው ወደ ስፍራው አቅንተው ነበር።