በሶማሌ ክልል ቀብሪደሃር ውስጥ ቺኩንግዋኛ ፊቨር ተከሰተ

ፓራሳይቱን ተሸካሚ የሆነች አስተላለፊ ቢምቢ Image copyright Getty Images

ባለፉት ጥቂት ቀናት በሶማሌ ክልል ቀብሪደሃር ከተማ ነዋሪዎችን ከፍተኛ የጤና ስጋት ላይ የጣለ ምንነቱ ያልታወቀ ወረርሽኝ ገብቶ በርካታ ሰዎች መታመማቸውን ተነግሯል።

የበሽታውን ምንነት በተመለከተ የሶማሌ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዩሱፍ ሕመሙ ቺኩንግዋኛ ፊቨር ይባላል ያሉ ሲሆን በወባ ትንኝ የሚተላለፍና በቺኩንግዋ ቫይረስ የሚከሰት መሆኑን ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በንቅለ ተከላ ዕይታው የተመለሰለት ኢትዮጵያዊ ታዳጊ

አተት እና ኮሌራ ምን እና ምን ናቸው?

የበሽታውን ምልክቶች ሲዘረዝሩም የመጀመሪያዎቹ ሁለትና ሦስት ቀናት ኃይለኛ ትኩሳትና የራስ ምታት እንዲሁም ቁርጥማት ያለው መሆኑን ገልፀው ታማሚዎችም በቀብሪ ደሃር ሆስፒታል ታክመው እየተመለሱ ነው ብለዋል።

"እስካሁን ድረስ ባለን ሪፖርት" አሉ ኃላፊው "63 ሰዎች በዚህ ቫይረስ ተጠቅተው ወደ ህክምና ተቋማት በመምጣት ህክምና አግኝተዋል።"

በአሁኑ ሰዓት ሀገር አቀፍ ፈተና እየተሰጠ በመሆኑ በዚህ ቫይረስ የተጠቁ ተማሪዎች ማስታገሻ ተሰጥቷቸው ወደ ፈተና ክፍል መግባታቸውን አረጋግጠዋል።

ዓለማችን የኩፍኝ ወረርሽኝ ያሰጋታል

ከዚህ በሽታ ጋር የተገናኘ ምንም አይነት ሞት አለመከሰቱን አስታውሰው ታማሚዎቹ በአጠቃላይ ሕክምና አገኝተው ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን ዶክትር ዩሱፍ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህ በሽታ በወባ ትንኝ አማካኝነት ከታማሚው ወደ ጤነኛ ሰዎች የሚተላለፍ ሲሆን የአካባቢው ባለስልጣናት የወባ ትንኝ መከሰቻ ስፍራዎችን ለማጥፋት እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ተመሳሳይ ወረርሽኝ በዶሎ አዱና ዶሎ ባያ አካባቢ የዛሬ ዓመት ተከስቶ እንደነበር ዶ/ር ዩሱፍ ጨምረው ነግረውናል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ