የቦትስዋና ፍርድ ቤት የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ወንጀል አለመሆኑን ወሰነ

የመብት አቀንቃኞች የቀስተ ደመና ሰንደቅ አላማ ይዘው ነበር Image copyright Getty Images

የቦትስዋናው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተመሳሳይ ፆታዎች መካከል ያለ ፍቅርን ወንጀል አለመሆኑን በትናንትናው ዕለት ብይን አሳልፏል።

ፍርድ ቤቱ በተመሳሳይ ፆታዎች መካከል የሚደረግ ወሲባዊ ግንኙነት እስከ ሰባት ዓመታት ድረስ የሚያሳስረው የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ህጋዊ አይደለም በሚል ነው ውሳኔውን ያስተላለፈው።

በባለፈው የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትን ወንጀል መሆኑ ይቀጥላል የሚለው ውሳኔ የመብት አቀንቃኞቹን ያሳዘነ ክስተተት ቢሆንም ይህ ውሳኔ ለተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት መብት አቀንቃኞች ከፍተኛ ድል ሆኖ እንደተመዘገበ ተገልጿል።

''ወደ ኢትዮጵያ የምናደርገውን ጉዞ አንሰርዝም''

ኬንያዊው ፀሀፊ ቢንያንቫንጋ ዋይናይና ሲታወስ

አክቲቭስቶች ይህንን ውሳኔ ለአፍሪካ ተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት መብት ጥሩ ዜና ነው ብለውታል።

ሶስቱም ዳኞች ያለምንም ተቃውሞ ባሳለፉት ብይን የከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኛ ማይክል ኤልቡሩ "የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትን ወንጀል ማድረግ ጨቋኝና አግላይ ነው፤ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ፋሽን ሳይሆን የሰው ልጅ ተፈጥሮ ነው" ብለዋል።

ታንዛኒያ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎችን አድና ልታስር ነው

ህጉ በእንግሊዝ ቅኝ ገዥዎች የተደነገገ ሲሆን ይህንንም ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤቱ ያመጡት ተማሪዎች የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ተቀባይነት በማህበረሰቡ ዘንድ መቀየሩን እንደ መከራከሪያነት በማቅረብ ነው።

በአፍሪካ ውስጥ 31 ሃገራት የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትን ወንጀል የሚያደርጉ ህግጋት አሏቸው።

በናይጀሪያ፣ ሱዳንና ሞሪታንያ እስከ ሞት ቅጣት የሚደርስ ሲሆን በታንዛንያ የዕድሜ ልክ እስራት ያስቀጣል።

በቅርብ አመታት ውስጥ ሞዛምቢክና ሲሸልስ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትን ወንጀል የሚያደርጉ ህግጋት ቀይረዋል።