የካፍ ፕሬዝደንት አሕመድ በፈረንሳይ ፖሊስ ለምን ታገቱ?

የካፍ ፕሬዝደንት አሕመድ

የአፍሪቃ እግር ኳስ አስተዳዳሪ ካፍ ፕሬዝደንት የሆኑት አሕመድ አሕመድ ለስብሰባ ወደ ፈረንሳይ በሄዱበት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉት ባለፈው ሳምንት ነበር።

ምንም እንኳ የፈረንሳይ ፖሊስ ፕሬዝደንቱን አይሠሯቸው፤ አይክሰሷቸው እንጂ እንዲሁ በዋዛ አልነበረም በቁጥጥር ሥር የዋሉት።

ከዚህ ሽኩቻ ጀርባ አንድ መቀመጫውን ፈረንሳይ ያደረገ ኩባንያ አለ፤ 'ታክቲካል ስቲል' የተሰኘ። ይህ ድርጅት የዘንድሮውን የአፍሪካ ዋንጫ ጨምሮ ለካፍ በርካታ ቁሳቁሶችን በማቅረብ ይታወቃል።

«የኔ ትውልድ ታሪክ እንደሚሠራ እምነት አለኝ» ሎዛ አበራ

ነገር ግን ወደዚህ ኩባንያ ድረ-ገፅ ብታቀኑ ምንም ዓይነት የእግር ኳስ ቁሶች አታገኙም። ታድያ እንዴት ሆኖ ነው ድርጅቱ የኳስ ቁስ አቅራቢ ሆኖ የተገኘው?

የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ነበር አሕመድ ወደ የካፍን መንበረ-ሥልጣን አዲስ አበባ ላይ በተደረገ ምርጫ የተቆናጠጡት። ካፍም ከዚህ ድርጅት ጋር ውል የፈረመው በዚሁ ዓመት ነበር።

ታድያ የአሕመድ ካፍ ይህን ያደረገው ከታዋቂው የስፖርት ዕቃዎች አምራች ኩባንያ 'ፑማ' ጋር የነበረውን የ248 ሚሊዮን ዶላር ውል በማፍረስ ከታክቲካል ስቲል ጋር የ1 ቢሊዮን ዶላር ውል ገብተዋል። በነገራችን ላይ ከፑማ ጋር የገቡት ውል 60 በመቶ ቅናሽ ነበረው።

ይሄኔ ነው በርካቶች 'ጠርጥር. . .' ማለት የጀመሩት። ካፍን ከራስ ፀጉሩ ጀምሮ የሚያውቁትም ቢሆኑ ውሉ ብዙም ስሜት አልጣቸውም። ምክንያቱም ካፍ በደላላ [በሦስተኛ ወገን] በኩል ውል ፈፅሞ አያውቅምና።

ባለፈው ጥር ወር ሞሮኮ ላይ ተካሂዶ የነበረው የቻን ውድድር ጥቅም ላይ የዋሉት አልባሳት እና ኳሶች ተመሳሳይ ናቸው የሚል ዘገባ ወጣ። የቢቢሲ ምርመራ ቡድን ግን ይህን ዘገባ ትክክል አለመሆኑን አረጋገጠ።

''ብሔርተኝነት'' እያጠላበት ያለው እግር ኳስ

አሕመድ ከፑማ ጋር የነበራቸውን ውል አፍረስው ከታክቲካል ሰቲል ጋር አዲስ ውል በመፈፀም ለቻን 2018 ቁሶችን አዘው ይሆን ወይ ሲል ቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ጥያቄ ያቀረበላቸው አሕመድ በሕዝብ ግንኙነት ኃላፊያቸው በኩል ምላሽ ሰጡ።

«ወቀሳው ሃሰት ነው። ሆን ተብሎ ስም ለማጥፋት ነው የተከወነው» የሚል ምላሽ ተሰማ። የአሕመድ አፈ-ቀላጤ ይህ የእርሳቸው ብቻ ሥራ አይደለም፤ የካፍ እንጂ ሲሉም ምላሽ ሰጡ።

አፈ-ቀላጤው አክለው ከታክቲካል ጋር የነበረው ውል ፀሐይ የሞቀው ነው ቢሉም የካፍ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑ ሰው ግን ሂደቱ ጤናማ አልነበረም ሲሉ ይወቅሳሉ።

Image copyright Tacticalsteel.com

'ታክቲካል ስቲል'

መቀመጫውን በደቡባዊ ፈረንሳይ ቱሎ ያደረገው ይህ ድርጅት የጂምናዚየም ዕቃዎችን በማምረት ይታወቃል፤ ከ2016 ጀምሮ ነው ገበያውን የተቀላቀለው።

ድርጅቱ ከካፍ ጋር ስላለው ውል የሚጠቁም ምንም ዓይነት መረጃ ድረ-ገፁ ላይ አላሰፈረም፤ አክሎም ምንም ዓይነት እግር ኳስ ነክ ቁስ ገፁ ላይ አይገኝም።

ነገር ግን አሕመድ ከተመረጡ ከሰባት ወራት በኋላ በተካሄደው የቻን 2017 ዋንጫ ላይ ቁስ አቅራቢ ሆኖ ተገኘ።

እግር ኳስ ተጫዋቹ ወንድወሰን ዮሐንስ እንዴት ተገደለ?

የአሕመድ ቀኝ እጅ የሆኑት ሎይክ ጄሮ [የማዳጋስካር ፓርላማ አባልም ናቸው] አንድ ወዳጅ አሏቸው፤ ሮሙዋልድ ሴሊዬ የተባሉ፤ እኚህ ሰው ታድያ ልጥጥ ናቸው፤ ኧረ እንደውም የታክቲካል ስቲል ባለቤት ናቸው።

ስለዚህ ጉዳይ ጥያቄ የተሰነዘረላቸው አሕመድ «ምንም ዓይነት የጥቅም ግጭት የለም» ሲሉ ነው ምላሽ የሰጡት።

ቢቢሲ ለጄሮም ሆነ ለሴሊዬ እስቲ ማብራሪያ ቢጤ ስጡን የሚል ደብዳቤ ከላከ ወራት ተቆጥረዋል፤ ምላሽ ግን የለም።

የማጣራት ሂደቱን ያላቋረጠው ቢቢሲ አንድ መረጃ ማግኘት ቻለ። አንድ ሌላ ኩባንያ አለ፤ የታክቲካል ስቲል አጋር ነው። ይህም ድርጅት ለካፍ ቁስ ያቀርባል። ለዚህ አቅርቦቱ ደግሞ ካፍ ዱባይ በሚገኝ ባንክ አማካይነት ክፍያ ፈፅሟል። ነገር ግን ይህ ገንዘብ ፈረንሳይ ወደሚገኘው የታክቲካል ስቲል ባንክ አካውንት ይዛወራል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ነው ታድያ የካፍ ፕሬዝደንት አሕመድ ወደ ፈረንሳይ ያቀኑት፤ በሃገሪቱ ፖሊስ ቁጥጥር ሥርም የዋሉት።

ሴት እግር ኳሰኞች እና ቡድኖች ስንት ይከፈላቸው ይሆን?

የፈረንሳይ ፖሊስ ሰውዬውን የያዝናቸው «በሙስና እና መሰል ጉዳዮች ስለምንፈልጋቸው ነው» የሚል መግለጫ አወጣ። ፖሊስ ሰውዬውን ከመረመረ በኋላ ለቀቃቸው፤ ክስም እሥርም አልነበረም።

የቀድሞው የማዳጋስካር ዓሳ ሚኒስትር እና የሃገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊ፤ የወቅቱ የአፍሪካ እግር ኳስ አስተዳዳሪ አሕመድ አሁን ወደ ማዳጋስካር እንደተመለሱ ተነግሯል።

ለቢቢሲ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠው የአሕመድ ሕዝብ ግንኙነት ቡድን «አሕመድ ታክቲካል ስቲልን የመረጡት አማራጭ ባለመኖሩ እንጅ . . » ሲሉ መለሱ። አክለውም ቱሎ ለሞሮኮ ቅርብ በመሆኗ ከኩባንያው የሚመጡ ዕቃዎች በቀላሉ እንዲገቡ ያግዛል ሲሉ ይተንትናሉ።

ካፍ የፃፈውና ቢቢሲ ያገኘው አንድ ኢሜይል ፑማ የካፍ ብቸኛ የስፖርት አቅራቢ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፤ ምንም እንኳ ውሉ ቢፈርስም።

ቢቢሲ ያገኛቸው ሦስት ወሳኝ የኢሜይል ልውውጦች ፕሬዝደንቱ ራሳቸው የፑማ ውል ተሰርዞ የታክቲካል ስቲል ውል እንዲፀድቅ እንዳዘዙ የሚጠቁሙ ናቸው።

ትኩረት እየሳበ የመጣው የሴቶች እግር ኳስ የዓለም ዋንጫ

አሕመድ ግን ተጠያቂው ዋና ፀሐፊ ግብፃዊው ፋህሚ ናቸው ይላሉ፤ የቻን ቁስ አቅራቢዎችን ጉዳይ በጊዜ አላስፈፀሙም በማለት። ፋህሚን ቢቢሲ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ የተሳካ አልሆነም።

ባለፈው ዓመት ጥር ገደማ ካፍ በእጅ የተሰፉና የካፍ ሎጎ ያለባቸውን 60 ሺስ ኳሶች ከታክቲካል ስቲል አዟል። ለ54ቱ የፌዴሬሽኑ አባላት እንዲከፋፈሉ በማሰብ።

ይህ ስምምነት 1.7 ቢሊዮን ዶላር ነው፤ ለአንድ ኳስ 30 ዶላር [870 ብር ገደማ] ማለት ነው። የትራንስፖርት ወጭው ደግሞ 738 ሺህ ዶላር።

ፊፋ፤ ካፍና ታክቲካል ስቲል ያላቸውን ግንኙነት ለማጣራት ምርመራ መጀመሩን ሰምተናል። አሕመድ ግን ወጥረት ላይ ያሉ ይመስላሉ። በሚቀጥለው ሳምንት ደግሞ ትልቁን የአህጉሪቱን ዋንጫ ሊያዘጋጁ ዱብ ዱብ እያሉ ነው።