የመንግሥት ድርጅቶችን 'ፕራይቬታይዝ' ጉዳይ እጅግ አከራካሪ ሆኗል

የኢትዮቴሌኮም እና አየር መንገድ አርማ Image copyright Ethiotelecom/ET

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን የመጡ ሰሞን ነበር ከኤርትራ ጋር ሰላም እንደሚያሰፍኑ፤ በመንግሥት ስር ያሉ ግዙፍ የኢኮኖሚ ተቋማት ሙሉ በሙሉም ሆነ በከፊል ወደ ግል እንዲሸጋጋሩ ለማድረግ እንደሚሰሩ ይፋ አደረጉ።

በወቅቱ ሁለቱም አበይት ጉዳዮች አነጋጋሪ ነበሩ። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀዳሚ ሥራ የነበረው ግን የኤርትራ ጉዳይ ነበር። 'የፕራይቬታይዜሽኑ' ጉዳይ በይደር ተቀምጦ ቆይቷል።

ጉዳዩ ለሕዝብ ጆሮ ከደረሰ ከአንድ ዓመት በኋላ አሁን እንደ አዲስ ተነስቶ መናጋገሪያ ሆኗል።

ሐሙስ እለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዉጭ ኩባንያዎች በቴሌኮሙኑኬሽን ዘርፍ መዋዕለ ነዋይ እንዲያፈሱ የሚፈቅድ ረቂቅ ሕግ አፅድቋል።

ምክር ቤቱ ገለልተኛ የኮሙዩኒኬሽን ባለስልጣን መስሪያ ቤትን ለማቋቋም የሚያስችል አዋጅም እንዳጸደቀ የተከበሩ ዶ/ር ሙሉጌታ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ባለስልጣኑ የቴሌኮም ዋጋ ትመናን፣ የኮምኒኬሽን ፖሊሲዎችን ማስፈጸምና የኮምኒኬሽን ድርጅቶችን፣ ኢንተርኔትንና የሬዲዮ ሞገዶችን ይቆጣጠራል ሲሉም ያብራራሉ።

«አማካሪ አያስፈልገኝም ብሎ የሚያስብ መሪ አልገባውም ማለት ነው» ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ

'ፕራይቬታይዜሽን' ወይንም የመንግሥት ድርጅቶችን ለግል ይዞታነት የማዞር ጉዳይ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎችንና ፖለቲከኞችን በሦስት ጎራ ከፋፍሏል።

አንደኛው ጎራ 'አዎ መሸጥ አለባቸው፤ እኒህ ድርጅቶች ገበያውን በሞኖፖል ይዘውት እስከመቼ?' የሚል ሃሳብ የሚያነሱ ግለሰቦች ስብስብ ነው። ሁለተኛው ደግሞ 'ይህ ሃገር ከመሸጥ አይተናነስም፤ የመወዳደር አቅም ሳይኖረን እንዴት ሃብታሞች ሃገራችን እንዲገቡ እንፈቅዳለን?' ሲሉ ይሞግታሉ። ሦስተኛው 'መሸጥ ያለባቸው እና የለሌባቸው አሉ' ሲሉ የሚመክሩ ናቸው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ ከሁለቱ ፅንፍ ሃሳቦች መሃል ላይ ናቸው።

«ይህንን ፖሊሲ የሚያስፈፅሙ ሰዎች ሁሉም ነገር ፕራይቬታይዝ ይደረጋል ብለው ማሰብ የለባቸውም። መደረግ ያለባቸው አሉ፤ መደረግ የሌለባቸው አሉ። ለምሳሌ በምንም መሥፈርት የኢትዮጵያ አየር መንገድ መደረግ የለበትም። በፖለቲካም በኢኮኖሚም መሥፈርት መደረግ የለበትም። ከሃገር ጥቅምም አንፃር መደረግ የሌለበት ነው" በማለት አጥብቀው ይከራከራሉ።

ነገር ግን ይላሉ ፕሮፌሰር አለማየሁ «ሌሎቹን ለምሳሌ ስኳር ፋብሪካን ፕራቬታይዝ ብታደርገው፤ ብትሸጠው አዋጭ ነው። ኢትዮ-ቴሌኮም ላይ ስትመጣ ደግሞ አብዛኛውን ድርሻ እኛ ይዘነው ለምሳሌ 70 በመቶውን ከያዝነው በኋላ ሌላውን መሸጥ አዋጭ ነው። ቀሪውን ድርሻ የሚይዘው ደግሞ አፍሪካዊ ድርጅት ቢሆን ይመረጣል፤ በዚያውም የቀጠናውን ጥምረት ለማጠናከር።»

ኢትዮ ቴሌኮም... ወዴት? ወዴት?

መሸጡ የግድ ቢሆን እንኳ 'ሬጉላቶሪ ቦዲ' [ተቆጣጣሪ አካል] ማቋቋም ሊውል ሊያድር የሚገባው ጉዳይ እንዳልሆነ ፕሮፌሰሩ ያስረዳሉ።

«ለምሳሌ መንግሥት 60 በመቶ ገቢ ያገኘው ከቴሌ ነው። ሌላው 30 በመቶ ከንግድ ባንክ ነው። ስለዚህ ንግድ ባንክን፤ ቴሌን ሸጥክ ማለት ባዶ እጅህን ነው አራት ኪሎ ቁጭ የምትለው። ስለዚህ ምጣኔ ሃብታዊ ውሳኔ ለመወሰን ምንም ዓይነት 'ኢንቨስትመንት' የለህም ማለት ነው። አሁን መንግሥት ማድረግ ያለበት፤ በተለይ እንደ ቴሌ ላሉት የተወሰነውን ሽጦ ሲያበቃ የመቆጣጠር አቅሙ ሲጎለብት ለሌሎች ክፍት ማድረግ ነው።»

የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ አባል የነበሩት ፖለቲከኛው ዮናታን ተስፋዬ የመንግሥትን 'ፕራቬታይዜሽን' ዕቅድ ከሚደግፉት መካከል አንዱ ናቸው።

«ፕራቬታይዝ የማድረጉ አንደኛ ጥቅም 'ሞኖፖሊ' እንዳይኖር ማድረጉ ነው። ሁለተኛ የፉክክር ገበያ ይኖራል፤ ይህ ደግሞ ሕብረተሰቡ የተሻለ ምርትና አገልግሎት እንዲያገኝ ያደርጋል።»

ምጣኔ ሃብታዊውን ትንታኔ ለባለሙያዎች ልትወው፤ የሚሉት አቶ ዮናታን «የመንግሥት ድርጅቶች በመንግሥት ቁጥጥር ሥር መሆን አምባገነንነትን ያበረታታል» ባይ ናቸው።

«'እኔ ነኝ አሳቢ፤ እኔ የተሻለ ለማሕበረሰቡ እጨነቃለሁ' የሚል ሥነ-ልቡናን እያሳደረ ነው የሚሄደው። ይህ አስተሳሰብ ደግሞ ሥር በሰደደ ቁጥር ሌሎች ተፎካካሪ ኃይሎችን እንደ ሥልጣን ተቀናቃኝ ነው የሚያየው፤ ምክንያቱም ራሱ ነጋዴው መንግሥት እየሆነ ስለሚመጣ። ስለዚህ ፖለቲካዊ ብልሽትን ይፈጥራል፤ ነፃ ገበያ እና ፉክክር የሌለበት፤ አንድ ወገን ብቻ እሴት የሚጨምርበት በጣም ደካማ የገበያ ሥርዓት እንዲኖር ነው የሚያደርገው።»

ኢትዮጵያ ኢንትርኔትን ስታቋርጥ በየቀኑ 4.5 ሚሊዮን ዶላር ታጣለች

የሕዝብ ይሁንታ

የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች 'ዘ ቢግ ፋይቭ' ይሏቸዋል፤ አየር መንገድ፣ ቴሌኮም፣ ባንክ፣ ባቡር እና ስኳር ፋብሪካዎች። መንግሥት እነዚህን ድርጅቶች ለግል ባለሃብቶች ሲሸጥ ሕዝብን ማማከር አለበት የሚሉ ሃሳቦች በአለፍ ገደም እያሉ ይደመጣሉ።

አቶ ዮናታን «ይሄ እኮ የኢኮኖሚ ጉዳይ ነው. . .» ይላሉ። «ይሄ የኢኮኖሚ ጉዳይ ነው። የኢኮኖሚ ጉዳይ ደግሞ በባለሙያዎች ጥናት ተደርጎ፤ በዚያ ጥናት ላይ ተመርኩዞ፤ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ይሄ ያዋጣል ብለን የምንወስነው ነገር ነው እንጂ ልክ እንደባንዲራ ጉዳይ ወይም የክልል እንሁን ጥያቄ ሕዝበ-ውሳኔ የሚደረግበት አይደለም። በየትኛውም ዓለም ላይ ሕዝብ በእንደዚህ ዓይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ቀጥተኛ የሆነ ውሳኔ ማሳለፍ አይችልም።»

መሰል የፖሊሲ ለውጦች የሕዝብ ቀጥተኛ ተሳትፎ ባይኖራቸው እንኳ ምርጫ እስኪመጣ መጠበቅ አይቻልም ወይ? በርካቶች የሚያነሱት ጥያቄ ነው።

እርግጥ ነው አቶ ዮናታን በዚህ ጉዳይ ይስማማል። ግን እሱ አልሆነም፤ አሁን ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ለሃገሪቱ ይጠቅማል የሚለውን ፖሊሲ የማፅደቅ መብት አለው ይላል።

«አሁን ባለንበት ወቅት ኢኮኖሚው እየወደቀ ነው። ለዚህ ደግሞ አንድ ትልቅ ድርሻ የሚወስዱት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ናቸው። እነዚህ የልማት ድርጅቶች መወዳደር የሚችሉ ስላልሆኑ አሁን ያለው የኢኮኖሚ ሁኔታ ምንም ሊቋቋመው የሚችለው አይደለም። የውጭ ባለሃብቶችን መሳብ የሚቻለው ደግሞ የኢኮኖሚ ፖሊሲውን መቀየር ሲቻል ነው።»

ነዋሪነቱን እንግሊዝ ያደረገው የምጣኔ ሃብት ምሁሩ እዮብ ባልቻ፤ አዲሱ የፕራቬታይዜሽን አጀንዳ በግለሰቦች የሚመራ ነው ሲል ይሞግታል።

እንደ እዮብ ትንተና አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩን በምጣኔ ሃብት ጉዳይ የሚያማክሩ ግለሰቦች ከዓለም ባንክና እና ዓለም አቀፉ ገንዘብ ድርጅት ጋር በቀጥታም ሆነ ተዘዋዋሪ ቁርኝት ያላቸው ናቸው። ምንም እንኳ የእዮብ ትንታኔ ግለሰቦቹ ላሳኩት ግብ ምስጋና ቢሰጥም በፕራቬታይዜሽን ጉዳይ ላይ ያላቸው አቋም አያስተማምንም ይላል።

ፕሮፌሰር አለማየሁም ቢሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሥር ጫና እንዳሉና ያንን ጫና ለመቋቋም የሚያስችል የምጣኔ ሃብት አቅም የላቸውም ባይ ናቸው።

ትክክለኛው ጊዜ ላይ እንሆን?

ለፕሮፌሰሩ የመንግሥት ድርጅቶችን ለገበያ የማቅረብ ጊዜው አሁን አይደለም። ትርፉ ከመንግሥት ሞኖፖሊ ወደ ግለሰብ ሞኖፖሊ መሸጋገር ነው ይላሉ።

ወሳኝ ምጣኔ ሃብታዊ እርምጃዎች በ100 ቀናት

«ለምሳሌ ቴሌን በ5 ወይም 10 ቢሊዮን ዶላር ሸጥነው እንበል። ነገ ያ ድርጅት የሚያተርፈውን አትርፎ የቀረውን ይዞ ሹልክ ይላል። በኢትዮጵያ ሕግ ደግሞ ያተረፍከውን ገንዘብ 'እክስፓትረየት' [ይዘህ መውጣት] ማድረግ ትችላለህ፤ የፈለግከውን። መሰል ስትራቴጂክ ነገሮችን ስታስብ መንግሥት ለፕራቬታይዜሽን መጣደፍ የለበትም። መንግሥትም ስለጨነቀውና ዶላር ስላጠረው እንጂ ፈልጎት አይመስለኝም» ይላሉ።

ታድያ ትክክለኛው ጊዜ መቼ ነው?

ለአቶ ዮናታን ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው። መከራከሪያው ደግሞ ኢኮኖሚያችን እየደቀቀ ነው የሚል። ፕሮፌሰር አለማየሁ ደግሞ ጉዳዩን በሁለት ከፍለው ያዩታል።

«አንደኛው ፖለቲካዊ ነው፤ ማለት አንድ መንግሥት ይህንን ፖሊሲ አስተዋውቆ የሕዝቡን ይሁንታ ካገኘ ሊያስፈፅመው ይችላል። ምክንያቱም እነዚህ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ የሚቆጣጠሩ ተቋማት ናቸው» ይላሉ።

የስኳር ፋብሪካዎችን ለግል ባለሃብቶች የመስጠት ፋይዳና ፈተናዎቹ

ስለዚህ ትክክለኛው ጊዜ መንግሥት የሕዝቡን ፖለቲካዊ ውክልና ባገኘበት ጊዜ መሆን እንዳለበት የሚጠቅሱት ፕሮፌሰር አለማየሁ «በኢኮኖሚ መነፅር ስናየው ግን አሁን ባለው ሁኔታ በእኔ ግምት ትክክል አይደለም። ምክንያቱም መንግሥትም አልተረጋጋም፤ ሃገሩም አልተረጋጋም። ግን ደግሞ መንግሥት ብር የለውም። ከጀርባቸው ጠንካራ ኃይሎች ካልሸጣችሁ እይሏቸው ይሆናል። ስለዚህ ያለው አማራጭ ቅድም ያነሳሁት ሃሳብ ነው። የተወሰነውን ፕራይቬታይዝ ማድረግ።»