ኢሳያስን ከሥልጣን ለማውረድ ያቀደው'#ይአክል' (ይበቃል) የተሰኘው የኤርትራውያን እንቅስቃሴ

ይበቃል ዘመቻ በአሜሪካ Image copyright Girmay Andom

በሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ለአስርት አመታት በስልጣን ላይ የቆዩትን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ለመጣል ዘመቻ ጀምረዋል።

ለሰላሳ አመታት በስልጣን ላይ የቆዩት የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር ከስልጣን መውረድ ተከትሎ ለብዙዎች ተስፋን ሰንቋል።

በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በትግርኛ፣ አረብኛ፣ ቢለንና ሌሎችም የኤርትራ ቋንቋዎችን በመጠቀም 'ይአክል' (ይበቃል)ን ሃሽታግ በመጠቀም ዳያስፖራ ኤርትራውያን እንቅስቃሴውን ጀምረዋል።

የኢንተርኔቱን ባልቦላ ማን አጠፋው?

በተለያዩ ህይወት ላይ ያሉ ኤርትራውያንን አንድ ላይ ማስተባበር የቻለው የትግል ጥሪ ለኤርትራ ነፃነት የታገሉትንና እንዲሁም ታዋቂ ሙዚቀኞችን ሮቤል ሚካኤል፣ ዮሐንስ ቲካቦ ወይም በቅፅል ስሙ 'ወዲ ተካቦ'ን የመሳሰሉ ግለሰቦችን አካቷል።

Wedi Tikabo
Wedi Tikabo
Enough to division, migration and horrendous journeys. Enough to putting people without due process in dungeons. Enough to living without a constitution"
Wedi Tikabo
Eritrean music star

ከስድስት አመታት በፊት ከአገሩ ለመሰደድ የተገደደው ቲካቦ ከሰሞኑ በትግርኛ ባወጣው ቪዲዮ ላይ "መከፋፈል፣ ስደትና አሰቃቂ ጉዞ ይቁም" የሚል መልእክት አስተላልፏል።

" ሃገሪቷ ከገባችበት የቀውስ አረንቋ ልትወጣ ይገባል፣ ይበቃታል። ሰዎችን ያለ ምንም ሂደት ወደ ዘብጥያ መወርወር ይበቃል፤ ያለ ህገ መንግሥት መኖር ይበቃል" ብሏል።

'መደበቅ እናቁም!'

ዋሽንግተን ዲሲ የሚኖረው አማኑኤል ዳዋ ዘመቻውን ከጀመሩት ሰዎች መካከል አንዱ ነው፤ መፍራት ማቆም ይበቃል፤ በማለት ሰዎች በአፍሪካ ብቸኛዋ ስለሆነችው የአንድ ፓርቲ ሀገር ኤርትራ እንዲናገሩ ጥሪ አቅርቧል።

በንቅለ ተከላ ዕይታው የተመለሰለት ኢትዮጵያዊ ታዳጊ

ኢሳያስ የስልጣን መንበሩን የተቆጣጠሩት ኤርትራ ነፃነቷን ካገኘች በኋላ በ1985 ዓ.ም ነበር። ከዚያ በኋላ ኤርትራ ምርጫ አድርጋ አታውቅም፤ አንዳንድ ዲሞክራት ነን እንደሚሉ አምባገነን ሀገራት እንኳ የይስሙላ ምርጫ አይካሄድባትም።

የኢሳያስ አስተዳደር ተቃዋሚዎች እንዳይንቀሳቀሱ፣ ነፃ መገናኛ ብዙኀን እንዳይኖር ከልክሎ፤ የስርዐቱን ተቺዎች ወደ ዘብጥያ እየወረወረ ወታደራዊ አገልግሎትን በግድ አስፍኖ የስልጣን እድሜውን አርዝሟል ይላሉ ስርአቱን በቅርብ የሚከታተሉ።

ይህም በርካታ ኤርትራውያን ሀገራቸውን ጥለው ወደ አውሮጳ ለመሰደድ እንዲወስኑ ያደረገ ሲሆን በርካቶችም በሰሃራ በረሃ እንዲሁም በሜዲትራኒያን ባህር ላይ ያሰቡበት ሳይደርሱ ቀርተዋል።

አንዳንዶች በትዊተር ላይ ሳዋ በግዳጅ ብሔራዊ ወታደራዊ ማሰልጠኛ የነበራቸውን ቆይታ በማስታወስ ጽፈዋል።ሳዋ ወጣቶችና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ወታደራዊ ስልጠና የሚያገኙበት ሲሆን የስልጠናው ማብቂያው መቼ እንደሆነ አይታወቅም።

የኢትዮጵያ ፊልም ወዲያና ወዲህ

"ይህንን ዘመቻ የጀመርኩት በዚህ ትግል ውስጥ እስከመቼ ድረስ ማንነታችንን ደብቀን እንቆያለን በሚል ነው። ዋነኛ አላማው ራሳችንን በይፋ በመግለጥ ለኤርትራ ሕዝብና መንግሥት መልእክታችንን በግልፅ ማስተላለፍ ነው" በማለት ለቢቢሲ ትግርኛ የተናገረው አማኑኤል ነው።

ይህንን የነአማኑኤልን የማህበራዊ ድረገፅ ዘመቻ በእንግሊዝ የገዢው ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ መሪ የሆኑት ሲራክ ባሕሊቢ "በማህበራዊ መገናኛ ብዙኀን ላይ ከተጀመሩ ዘመቻዎች ሁሉ መጥፎው" ሲሉት የኤርትራ መንግሥት ደጋፊ የሆነው ተስፋ ኒውስ ድረገፅ ደግሞ "ይህ ዘመቻ የሕወሀት እጅ አለበት" ሲል ይከስሳል።

"በሀገር ውስጥና በባህር ማዶ ያሉ ኤርትራውያን፣ ኤርትራን ለማፈራረስ በሕወሀት እየተነዛብን ያለውን ፕሮፓጋንዳ ሊያምኑ አይገባም" ሲል አስነብቧል ተስፋ የዜና ድረገፅ።

አማኑኤል ግን #ይበቃል የሚለው ዘመቻ ላይ የሚቀርቡትን ክሶች ሁሉ ያጣጥላል።

'የማለዳ ወፍ' ነዎት ወይስ 'የሌሊት'?

'በስውር የሚበተኑ በራሪ ቅጠሎች'

በፌስ ቡክና በትዊተር የተጀመረው ዘመቻ አንድ ወዳጅን ወይንም ዝነኛ ሰውን በመምረጥ በኤርትራ ውስጥ ያለው ጭቆናን እንዲናገሩ ያደርጋል። የዚህ ሀሳብ የተወሰደው ከቡኬት ቻሌንጅ ነው።

አማኑኤል ይህንን ዘመቻ እንደ ፈር ቀዳጅ ተመልክቶታል። "ከሀገር ውጪ የሚኖሩ ኤርትራውያን የኤርትራ መንግሥትን ብተች ቤተሰቦቼ ላይ ስቃይና እንግልት ይደርሳል መሰረታዊ አገልግሎቶችንም ይነፈጋሉ ብለው መፍራት የለባቸውም" ይላል።

የኤርትራ መንግሥት አሁንም በኢንተርኔት እቀባ ላይ ጠንካራ እጆቹን እንዳሳረፈ ነው። አለም አቀፉ የሀገራትን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ይፋ የሚያደርገው ተቋም በኤርትራ ከአጠቃላይ ህዝቡ 1.3 በመቶው ብቻ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ነው ሲል ይፋ አድርጓል።

በሀገር ውስጥ ያሉ አክቲቪስቶች ሀሞታቸውን ኮስተር አድርገው የመንግሥትን ሥራ የሚቃወሙና #ይበቃል የሚል በራሪ ወረቀትን በድብቅ በመበተን ዘመቻው በሀገር ቤት ውስጥ እንዲታወቅና ስር እንዲሰድ የአቅማቸውን ጥረት እያደረጉ ነው።

Image copyright Amanuel Dawa

"በሀገር ውስጥ በህቡዕ የሚንቀሳቀስ የወጣቶች ቡድን አለ፤ እርሱ ነው #ይበቃል የሚለውን በራሪ ወረቀት በሀገር ውስጥ እንዲበተን የአንበሳውን ድርሻ የተወጣው" ብሏል አማኑኤል።

ይህ ዘመቻ ይላል ጉዳዩን ሲያብራራ "ይህ ዘመቻ የመንግሥት ተቃዋሚዎችንም ወደ አንድነት ለማምጣት ያለመ ነው።"

ኤርትራ በቤተ ክርስቲያን ስር ያሉ የጤና ተቋማትን ወሰደች

"ዜጎች በሚኖሩበት ማህበረሰብ፣ በተወለዱበት ቦታ፣ በሀይማኖታቸው፣ እና በሌሎች የሕይወት ትንንሽ ቡድኖች ተከፋፍለዋል። ይህንን መከፋፈል በማቆም ኃይላችንን ሁሉ በማስተባበር የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዲመጣ መስራት አለብን" ይላል አማኑኤል።

በርካታ ኤርትራውያን ባለፈው ዓመት ሀምሌ ወር ላይ ኢትዮጵያና ኤርትራ የሰላም ስምምነት ሲፈፅሙ በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረውንና ለሁለት አስርታት የዘለቀውን የድንበር ግጭት መቆም ተከትሎ በኤርትራ የፖለቲካው ምህዳር ሰፋ ይላል ብለው ተስፋ አድርገው ነበር።

ነገር ግን የጠበቁት ተስፋ እንደ ጉም በኖ ጠፋ፣ ፕሬዝዳንት ኢሳያስም ሁሌም በሚታወቁበት አምባገነነን አስተዳደራቸው ቀጠሉ።

Image copyright Amanuel Dawa

ከኢትዮጵያ ጋር የሰላም ስምምነቱ ከተደረገ በኋላ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አንዴ ብቻ ነው የካቢኔ ስብሰባ ያደረጉት። ኤርትራ የ26ኛ አመት የነፃነት በዓሏን ስታከብር ባደረጉት ንግግርም ምንም አይነት የስርአት ማሻሻያም ሆነ የለውጥ ፍንጭ አልሰጡም።

ይህም ተቃዋሚዎችን ሀገሪቱ በአንድ ፓርቲ አመራር ስር ብቻ ሳትሆን በአንድ ሰው አገዛዝ ስር ወድቃለች እንዲሉ አድርጓቸዋል።

በዚህ መካከል ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከኢትዮጵያ ጋር የመሰረቱትን አዲስ ወዳጅነት ተገን አድርገው በስደት ያሉ ተቃዋሚ ቡድኖችን እያፈኑ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ። ከእነዚህም መካከል በአዲስ አበባ ቢሮውን ከፍቶ ይንቀሳቀስ የነበረው የተቃዋሚ ቡድን የኤርትራ ኢምባሲ ከ20 ዓመት በኋላ መከፈቱን በመከተል የእርሱ ቢሮ ተዘግቷል።

"ተግዳሮቶችና ተስፋዎች"

የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ጥሎት የነበረውን ማእቀብ አንስቷል። ማእቀቡ መሳሪያ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት እና ወደታደራዊ መኮንኖች የሚያደርጉት ጉዞንም ያካትት ነበር።

አክቲቪስተች በሀገር ውስጥ ያለው የተቃውሞ ማእበል ቀስ በቀስ ማደጉ አይቀርም ሲሉ ተስፋ አድርገዋል። ለዚህም ምሳሌ ብለው የጠቀሱት በቅርቡ በኤርትራ የሚኖሩ የካቶሊክ ጳጰስ የፃፉትን ደብዳቤ ነው። ደብዳቤው በሀገሪቱ ውስጥ ያለው ሁኔታ ከመሻሻል ይልቅ እየባሰበት በመሄዱ በርካቶች እየፈለሱ መሆኑን የሚጠቅስ ነው።

ጳጳሱ "በሀገር ውስጥ ያለው ብልሹ ሁኔታ እስካልተቀየረ ድረስ ወደ ሰው ሀገር መሰደዱ ቀጣይ ነው የሚሆነው" ብለዋል።

ከአንድ መቶ በላይ አፍሪካውያን ደራሲዎችና አክቲቪስቶች በጋራ ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ በጻፉት ግልፅ ደብዳቤ "ኤርትራ በአህጉራችን በጣም ዝግ ከሆኑ ሀገራት መካከል ነች" ስለዚህም ፕሬዝዳንቱ "ኤርትራ ከሌሎች አፍሪካ ሀገራት ጎን" እንደትቆም ተገቢውን ማሻሻያ መውሰድ አለባቸው ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ በደራሲያኑና ታዋቂ ሰዎቹ ሀሳብ ይስማሙ ወይንም በሱዳን እንደታየው ህዝባዊ እንቢተኝነት ተከስቶ ከስልጣን መወገድን ይስጉ ምን አይነት ፍንጭ የለም።

የአክሱም ሙስሊሞች ጥያቄ መቼ ምላሽ ያገኝ ይሆን?

በሱዳን የተቀሰቀሰው ህዝባዊ እንቢተኝነት ከወታደራዊ ኃይሉ ጥቃት ቢደርስበትም ኤርትራውያን አክቲቪስቶች ግን ከተቃውሞው በጎ ነገር ለመቅሰም አሰፍስፈዋል።

" በሱዳን ውስጥ የተከናወነው ያሳዝናል የደረሰውን በቃላት ማስቀመጥ ይቸግረኛል። ነገር ግን የሱዳን ህዝቦች በአንድነት በመሆን አምባገነኑን ስርዓት ተጋፍጠውታል። ያ ለእኔ እና በመላ ዓለም ለምንገኘው ኤርትራውያን አነሳሽ ነው" ብላለች ስውዲን ውስጥ ነዋሪነቷን ያደረገችው ጋዜጠኛና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ ሜሮን እስጢፋኖስ።

"የሱዳን ሕዝቦች ሰላማዊ ትግል መርጠዋል ያ ደግሞ ለኛም ሕዝብ ይሰራል ብዬ አምናለሁ። ሱዳኖች ያለባቸውን ጭቆና ተቋቁመው ካደረጉት እኛ የማናደርግበት ምክንያት የለም።" በማለት ሃሳቧን ትቋጫለች

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ