በ10ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና 28 ተማሪዎች መውለዳቸው ተገለፀ

ወልደው በፈተና ላይ ያሉ እናቶች Image copyright Ministry of Education

ትናንት በተጠናቀቀው የዘንድሮው 10ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ የአገር አቀፍ ፈተና 28 ሴቶች በፈተና ላይ ሳሉ መውለዳቸውን የትምህርት ሚኒስቴር ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሃረጓ ማሞ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ዳይሬክተሯ እንዳሉት ተማሪዎቹ በምን ሁኔታ ጋብቻ ፈፀሙ? ያለ ዕድሜ ጋብቻ ነበር ወይ? የሚለው በጥናት የሚታወቅ ቢሆንም አሁን ባላቸው መረጃ ሁሉም በትዳር ላይ የነበሩ ሴቶች ናቸው።

የ29 ዓመቷ የህክምና ዶክተርና ኢንጅነር ዕልልታ ጉዞ

ከእነዚህም መካከል 27ቱ የመደበኛ ትምህርት ተማሪዎች ሲሆኑ እንዷ የግል ተፈታኝ መሆኗም ታውቋል።

በአገሪቷ የተለያዩ ቦታዎች በሚገኙ የመፈተኛ ጣቢያዎች ማለትም በደቡብ 11፣ በትግራይ 4፣ በአማራ 2፣ በኦሮሚያ 6፣ በቤኒሻንጉል 1፣ በአዲስ አበባ 1 እና በጋምቤላ 3 ሴት ተማሪዎች በፈተና ወቅት መውለዳቸው ሪፖርት እንደደረሳቸው ዳይሬክተሯ አስረድተዋል።

"በዓለማችን ካሉ ህመሞች የከፋ ሕመም ምጥ ነው" የሚሉት ወ/ሮ ሃረጓ ተማሪዎቹ በአስቸጋሪና ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ፈተናውን ማጠናቀቃቸውን አድንቀዋል።

"በወለደች በ30 ደቂቃ ገብታ የተፈተነችው ተማሪ ዜና በጣም አስገራሚ ሆኖ ነው ያገኘነው፤ ሌላም እንዲሁ ፈተናው ከጀመረበት ሰኞ ቀን አንስቶ እስከተጠናቀቀበት ረቡዕ ድረስ በምጥ ላይ እያለች ፈተናውን ሳታቋርጥ የተፈተነችው ተማሪ ለብዙዎች ግርምትን የፈጠረ ነበር" ሲሉ ምሳሌ ያነሳሉ።

ሴቶች በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆነው ትምህርት ምን ያህል አስፈላጊና በመማር ራስን ለመለወጥ የተዘጋጀ ምዘና ግድ እንደሆነ ግንዛቤ መኖሩን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በበጎ መልኩ ተመልክቶታል ብለዋል።

ታሪክ እየቀየሩ ያሉት ሴቶች

ትምህርትን ማጠናቀቅ ብቻ ሳይሆን ውጤቱም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፤ ታዲያ እነዚህ ተማሪዎች በእንዲህ ዓይነት ጊዜ የማይሰጥ ህመም ውስጥ ሆነው ምን ያህል ውጤታማ ይሆናሉ? ስንል ለዳይሬክተሯ ጥያቄ ሰንዝረን ነበር።

እርሳቸውም "እነዚህ ሴቶች በእርግዝና ወቅት ተምረዋል፣ አጥንተዋል፣ በመሆኑም በፈተና ወቅት ባጋጠማቸው ምጥና ወሊድ ምክንያት አንድ ዓመት ወደኋላ እንቀርም ብለው ለፈተና መቅረባቸው ጥንካሬያቸውን ያሳያል" ሲሉ ምላሽ ሰጥተውናል።

አክለውም በወሊድ ምክንያት በሚፈጠረው ህመም ምክንያት በትክክል ፈተናውን ለመውሰድ የማይችሉ ከሆነ በሚቀጥለው ጊዜ እንዲፈተኑ ሃሳብ ቀርቦላቸውም ነበር ብለዋል።

ትምህርት ዕድሜን እንደሚያስረዝም በጥናት ተረጋገጠ

"ተማሪዎቹ አጥንተናል፣ ተዘጋጅተናል፣ መፈተን እንፈልጋለን እያሉ መከልከልም መብትን መጋፋት ነው" ሲሉ በተማሪዎቹ ፍላጎት ላይ ተመስርተው ባሉበት እንዲፈተኑ መደረጉን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ትዳር ላይ በመሆናቸው ከትምህርት የሚቀሩ ተማሪዎች በርካታ እንደነበሩ የሚጠቅሱት ወ/ሮ ሃረጓ ከእርግዝና ባሻገር በወሊድ ላይ ሆነው የመጡበትን አላማ ከግብ ለማድረስ ጥረት በማድረጋቸው እነዚህ ሴቶች አርአያ ናቸው ብለዋል።

ዳይሬክተሯ እንደሚሉት ባለፈው ዓመትም ሆነ ከዚያ በፊት እንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች የነበሩ ሲሆን የዘንድሮው ግን ቁጥሩ ጨምሯል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በፈተና ወቅት ሊከሰቱ ይችላሉ በማለት ቅድመ ዝግጅት ከሚያደርግባቸው አጋጣሚዎች አንዱ ወሊድ (ምጥ) ነው። በመሆኑም ምጥና ድንገተኛ ህመሞች ሲያጋጥሙ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ከቀይ መስቀል ጋር በመሆን ቅድመ ዝግጅት አድርገው እንደነበርም ተናግረዋል።

በዘንድሮው የ10ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና 1.2 ሚሊየን የሚደርሱ ተማሪዎች ለፈተና የተቀመጡ ሲሆን ግምሽ ያህሉ ሴቶች መሆናቸውንም ገልፀውልናል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ