የቬኔዝዌላ ቀውስ፡ ስደተኞች ወደ ፔሩ ድንበር አመሩ

ቱምቤስ በተሰኘችው የፔሩ ጠረፍ ከተማ በኢሚግሬሽን ቢሮ የተሰለፉ ቬኔዝዌላውያን Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ ቱምቤስ በተሰኘችው የፔሩ ጠረፍ ከተማ በኢሚግሬሽን ቢሮ የተሰለፉ ቬኔዝዌላውያን

የፔሩ መንግሥት የስደተኞችን ፍልሰት ለመቆጣጠር በማሰብ ቪዛን የሚጠይቅ ሕግ ይፋ ከማድረጉ በፊት ለመቅደም ያሰቡ በሺህዎች የሚቆጠሩ ቬኔዝዌላውያን ወደ ፔሩ ተመሙ።

በትናንትናው ዕለት ከሌሊቱ 6 ሰዓት አንስቶ ቬኔዝዌላውያን ቀኑ ያላለፈበት ፓስፖርትና ቪዛ እንዲኖራቸው ግዴታ ሆኗል።

የአዲሱ ሕግ ጭምጭምታ ለዓመታት የቆየውን የቬኔዝዌላውያን ቀውስ ሽሽት ወደ ፔሩ ድንበር ብዙ ቬኔዝዌላውያንን አንቀሳቅሷል።

እ.አ.አ ከ2015 ጀምሮ ወደ አራት ሚሊየን ሰዎች ከቬኔዝዌላ መሰደዳቸውን የተባበሩት መንግሥታት ገልጧል።

የሃገሪቱ ምጣኔ ወደ ውስጥ ሲፈርስ ከፍተኛ የሥራ እና የምግብ እጥረት ከማስከተሉም ባሻገር መድሃኒትም እንደልብ ለማግኘት አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል። በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችም ሰብዓዊ እርዳታ እየተደረገላቸው ነው።

ባለፈው ቅዳሜ ከወጣው ሕግ በፊት የቬኔዝዌላ ነዋሪዎች ወደ ፔሩ ለመግባት መታወቂያ ብቻ ነበር የሚያስፈልጋቸው።

ወደ 6ሺህ ቬኔዝዌላውያን ሐሙስ ዕለት ወደ ቱምቤስ ከተማ ማቅናታቸውን የተናገሩት የድንበሩ ኃላፊዎች ከሌላው ጊዜ የሰው ፍልሰት በሦስት እጥፍ መጨመሩን አክለው ተናግረዋል።

Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ አብዛኞቹ ቬኔዝዌላውያን የሚጠየቁትን ለማሟላት አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል

ማሪያኒ ሉዛርዶ የተሰኘች ቬኔዝዌላዊት ከሁለት ሴት ልጆቿ ጋር ወደ ፔሩ ድንበር እየሄደች "ቬኔዝዌላ ውስጥ ፓስፖርት ማውጣት አይቻልም" ስትል ለአሶስዬትድ ፕሬስ በማለት "ፔሩ በፍጥነት መግባት አለብን" ስትል ተናግራለች።

የፔሩ ፕሬዚዳንት የሆኑት ማርቲን ቪዝካራ ባለፈው ሐሙስ የጠበቀውን የኢሚግሬሽን ሕግ ተከላክለዋል።

ፒውራ በተሰኘች ከተማ በተደረገ ዝግጅት ወቅት "ሃገራችን እጆቿን ለ800 ሺህ ቬኔዝዌላውያን ዘርግታለች" ሲሉም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። አክለውም "ቪዛ በመጠየቅ ወደ ሃገራችን የሚገቡትን መቆጣጠራችን ትርጉም የሚሰጥ ነገር ነው" ብለዋል።

የሰሜን አሜሪካ ሃገራት በብዛት ከቬኔዝዌላ የመጡ ስደተኞችን ተቀብለዋል። ኮሎምብያ ብቻዋን 1.3 ሚሊየን ቬኔዝዌላውያንን አስተናግዳለች። ፔሩ ደግሞ ወደ 768 ሺህ ቬኔዝዌላውያንን ተቀብላለች ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ቁጥሮች ያመላክታሉ።

ቬኔዝዌላ ምን እየተፈጠረ ነው?

በኒኮላስ ማዱሮ አመራር ስር የሃገሪቱ ኢኮኖሚ አሽቆልቁሏል። የመድሃኒትና የምግብ እጥረትም ሃገሪቷን ማጥ ውስጥ ከትቷል።

ለዓለም ገበያ ነዳጅ እያቀረበች በሃገሪቷ አንዳንድ ክፍሎች ነዳጅ የማይገኝበት ወቅት አለ። ሹፌሮች ለቀናት በመሰለፍ ነዳጅ የሚያገኙባቸውም ጊዜያቶች በርካታ ናቸው። መብራትም በተደጋጋሚ ይጠፋል።

መንግሥት እነዚህን ክስተቶች በአሜሪካ እገዳ ምክንያት የመጣባቸው መሆኑን ያስረዳል። የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በበኩላቸው ደግሞ ቬንዝዌላን በተከታታይ ያስተዳደሩትና የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም የሚከተሉ መንግሥታቶች ገንዘብ በማባከናቸውና በሙስና ምክንያት የመጣ ነው ይላሉ።

በታህሳስ ወር አካባቢ የፓርላማ ተወካይ የነበረው ሁዋን ጓይዶ እራሱን ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት አድርጎ በመሾሙ የቬንዝዌላ ቀውስ ተባባሰ። ያቀረበውም ምክንያት የማዱሮ ሹመት "ሕጋዊ አልነበረም" የሚል ነው።

ከዚያን ጊዜ አንስቶም ሁዋን ከ50 በላይ ሃገራትን እውቅና ያገኘ ሲሆን ከእነርሱም መካከል አሜሪካ እና አብዛኛዎቹ የደቡብ አሜሪካ ሃገራት ይገኙበታል። እስካሁን ግን የሃገሪቱ ወታደራዊ ኃይል እና ቻይና እና ሩስያ ለኒኮላስ ማዱሮ ታማኝነታቸውን አልነፈጓቸውም።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ