ኤርትራ የደብረቢዘን ገዳም መነኮሳትን አሰረች

የኤርትራ የፓትርያርኩ ፅህፈት ቤት Image copyright LISANTEWAHDO
አጭር የምስል መግለጫ ከፓትርያርክነታቸው እንዲወርዱ የተደረጉት አባ እንጦንዮስ ለረጅም ዓመታት የቤት ውስጥ እስረኛ ናቸው።

የኤርትራ ጸጥታ ሃይል አባላት ከሰሞኑ አምስት የደብረቢዘን መነኮሳትን አስረዋል

የገዳሙ ቆሞስ የነበሩና በአሁኑ ጊዜ በስደት እስራኤል የሚገኙት አባ ሰመረ ፍሰሃዬ ለቢቢሲ እንደገለፁት "ይህ እርምጃ መንግሥት በቤተ ክርስትያኒቱ የሚያደርገው ጣልቃ ገብነት ማሳያ ነው"

መነኮሳቱ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ የቁም እስርና በህይወት እያሉ እሳቸውን መተካት የመሳሰሉ የመንግሥትን ጣልቃ ገብነትን ሲቃወሙ እንደነበር የሚናገሩት አባ ሰመረ በዚህም ምክንያት ብዙ ችግሮች ይገጥማቸው ነበር።

የ "ጥርስ አልባው" ማዕቀብ መነሳት ፖለቲካ?

ኢሳያስን ለመጣል'#ይበቃል' የተሰኘው የኤርትራውያን እንቅስቃሴ

በእንግሊዝ ነዋሪነታቸውን ያደረጉት አባ ሺኖዳ ሃይለ በበኩላቸው መነኮሳቱ የቀድሞ ፓትርያርክ አቡነ እንጦንዮስ ከስልጣን እንዲወርዱ ያደረገውን ሲኖዶሱም ጭምር ሲቃወሙ መቆየታቸውን እና በቅርቡ ያለፉት የሰሜን እና ደቡብ ቀይ ባህር ዞን ሃገረ ስብከት ጳጳስ የነበሩት አቡነ አትናቴዎስም በገዳሙ መቀበር እንደሌለባቸው ተቃውሞ ማሰማታቸውን ገልጸዋል።

"የደብረቢዘን ገዳም ስርዓቱ በቤተክርስትያን ጉዳዮች እጅ ማስገባትን ስትቃወም የቆየች ገዳም ናት" በማለት አባ ሺኖዳ ይናገራሉ።

''ኤርትራ የእምነት ነፃነት የምታከብር ሃገር ነች'' አቶ የማነ ገብረ-መስቀል

ከስልጣናቸው እንዲወርዱ የተደረጉት አቡነ እንጦንዮስ ከ10 ዓመታት በላይ የቤት ውስጥ እስረኛ ሆነው እንዲቆዩ ተደርጓል።

ይሁን እንጂ የሲኖዶሱ ዋና ጸሃፊ አቡነ ሉቃስ የቀድሞው ፓትርያርክ በመንግሥት ውሳኔ ሳይሆን በግል ፍላጎታቸው ቤት ውስጥ መቆየታቸውን ይናገራሉ።

መስመር ያልያዘው የኢትዮ-ኤርትራ የንግድ ግንኙነት ወዴት ያመራል?

ከገዳሙ ብቻ ሳይሆን በበርካታ የመብት ተሟጋቾች ዘንድ የኤርትራ መንግሥት በቤተ ክርስቲያኒቱ የውስጥ ጉዳዮች ዘንድ ጣልቃ ይገባል የሚል ተደጋጋሚ ውንጀላ ይቀርብበታል።

የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን በሁለት ቡድን ተከፋፍላ የምትገኝ ሲሆን ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ሁለቱንም ወገኖች ለማስታረቅ ቃል ገብተው ነበር።

ከኤርትራው ከፓትርያርኩ ፅህፈት ቤት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ሊሳካልን አልቻልም።

መንግሥትም መነኮሳቱ ስለመታሰራቸው በይፋ የሰጠው መግለጫ የለም።