የቀድሞ የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር አል-በሽር ከወራት በኋላ ታዩ

ኦማር አል-ባሽር ከወራት በኋላ ታዩ Image copyright Reuters

ከሥልጣን የተወገዱት የሱዳኑ ኦማር ሃሰን አል-በሽር ከወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አደባባይ ታይተዋል።

በሽር ከታሠሩበት ሥፍራ በመኪና ወደ ሱዳን መዲና ካርቱም የመጡበት ምክንያት በሙስና ወንጀል የተከሰሱበትን ክስ ለመስማት ነው።

በጥበቃ ኃይሎች ተከበው የነበሩት የ75 ዓመቱ በሽር ባሕላዊ ነጭ ኩታቸውን ደርበው ከጭንቅላታቸው በማይለየው ጥምጣም ደምቀው ነበር ብቅ ያሉት።

በደቡብ ሱዳን የምሽት ክለቦች ታገዱ

ከሳሾቻቸው በሽር ከሥልጣን በተወገዱበት ወቅት በርከት ያለ ጥሬ ገንዘብ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ተገኝቷል ይላሉ።

እሁድ ዕለት ክሳቸውን ለመስማት ካርቱም የተገኙት አል-በሽር ከመኪናቸው እስከ አቃቤ ሕጉ ቢሮ እስኪደርሱ ድረስ ከሌላው ጊዜ በተለየ ጠደፍ ጠደፍ ሲሉ ተስተውለዋል። ከደቂቃዎች በኋላ ሲመለሱ ደግሞ ንዴት ቢጤ ፊታቸው ላይ ይታይ ነበር ይላል በሥፍራው የነበረው የሮይተርስ ወኪል።

ዓለም አቀፉ የወጀለኞች ፍርድ ቤትም [አይሲሲ] በሽርን በፅኑ ይፈልጋቸዋል፤ በዳርፉር ግዛት ለተፈፀመው የጦር ወንጀል ተጠያቂ ናቸው በማለት።

በሌላ በኩል የጊዜያዊው ወታደራዊ አገዛዝ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ሞሐመድ ሐማድ 'ሄሜቲ' በቅርቡ የሲቪል ነፍስ ያጠፉ ሰዎችን ለሕግ አቅርባለሁ ሲሉ ተደምጠዋል።

አልበሽር በማህበራዊ ሚዲያ የተቀሰቀሰባቸውን ተቃውሞ ተቹ

ተቃዋሚዎች በሰኔ ወር መባቻ ላይ ብቻ 100 ሰዎች በወታደሮች ተገድለዋል ሲሉ የሃገሪቱን ወታደራዊ ኃይል ይኮንናሉ።

ሄሜቲ 'ጃንጃዊድ' በተሰኘ ቅፅል ስም የሚታወቀውን ልዩ ኃይል አድንቀዋል፤ ምንም እንኳ ልዩ ኃይሉ ከዳርፉር ጀምሮ እስከ አሁኑ አመፅ በፈፀማቸው ግፎች ቢወቀስም።

የበሽርን ከሥልጣን መወገድ ተከትሎ መንበሩን የተረከበው ወታደራዊ ኃይል ሰላማዊ ሰዎች ላይ ኃይል በመጠቀሙ እየተወቀሰ ይገኛል፤ ሱዳንም ለጊዜው ከአፍሪቃ ሕብረት አባልነቷ ተሰርዛለች።

ኦማር አል-በሽር: ከየት ወደየት?

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ