ግብፅ በቀድሞው ፕሬዚዳንት ሞሀመድ ሞርሲ ሞት ውርጅብኝ እያሰተናገደች ነው

የቀድሞ የግብፅ ፕሬዚዳንት Image copyright EPA

የቀድሞው የግብፅ ፕሬዚዳንት ሞሀመድ ሞርሲ በትናንትናው ዕለት ፍርድ ቤት ተዝለፍልፈው ወድቀው ህይወታቸው ማለፉን ተከትሎ የግብፅ ባለስልጣናት ከፍተኛ ትችት እየደረሰባቸው ነው።

በአውሮፓውያኑ 2013 ከስልጣን የተወገዱት የ67 አመቱ ሞሀመድ ሞርሲ እስከ እለተ ህልፈታቸው ድረስ በግብፅ ባለስልጣናት ቁጥጥር ስር ነበሩ።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት አምነስቲ አሟሟታቸው በገለልተኛ ቡድን እንዲጣራ የጠየቀ ሲሆን የግብፅ ባለስልጣናት በበኩላቸው በልብ ህመም ነው የሞቱት ብለዋል።

ሞሐመድ ሙርሲ ፍርድ ቤት ውስጥ ሞቱ

አምነስቲ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ለውጥ እንዲደረግበት ጠየቀ

በኬንያ ከኢቦላ ጋር የሚመሳሰሉ ምልክቶች ያለባት ታማሚ ተገኘች

የቀሞው ፕሬዚዳንት ቤተሰቦችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በበኩላቸው ለብቻቸው ተገልለው በታሰሩበት ወቅት በአያያዛቸው ምክንያት የጤና ሁኔታቸው አሽቆልቁሎ ነበር በማለትም እየተናገሩ ነው።

ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ሞሀመድ ሙርሲ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ጥዋት ከቤተሰቦቻቸው ጋር አንድ ላይ ታይተዋል ተብሏል።

ልጃቸው አብዱላህ ሞሀመድ ሞርሲ ለሮይተርስ እንደተናገረው የአባቱን አስከሬን ወስደው ለህዝብ ክፍት በሆነ የቀብር ስርአትን ማከናወን ቢፈልጉም የግብፅ ባለስልጣናት እንደከለከሏቸው ነው።

በሙስሊም ብራዘር ሁድ ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ ያላቸው ሞሀመድ ሙርሲ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተመርጠው ያሸነፉ የመጀመሪያው መሪ ናቸው።

ከፍተኛ የህዝብ ተቃውሞን ተከትሎ በመፈንቅለ መንግሥት ከስልጣን የተወገዱት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ከአመት በኋላም በወታደሩ ቁጥጥር ስር ውለዋል።

በወቅቱ የጦሩ መሪ የነበሩት አብዱል ፋታህ አል ሲሲ ከጎርጎሳውያኑ 2014 ጀምሮ በስልጣን ላይ ነበሩ።

የፕሬዚዳንቱን ከስልጣን መወገድ ተከትሎ ባለስልጣናቱ በደጋፊዎቻቸው ላይና ሌሎችም ሰላማዊ ዜጎችን ማንገላታትየቀጠሉ ሲሆን ከአስር ሺዎችም በላይ ለእስር ተዳርገዋል።

ሙስሊም ብራዘርሁድና የቱርኩ ፕሬዚዳንት ጣይብ ኤርዶጋን ለቀድሞው ፕሬዚዳንት ሞት የግብፅ አመራሮችን ወንጅለዋል።

በስለላና ከፓለስታይን እስላማዊ ቡድን ሀማስ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል በትናንትናው ዕለት ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር።

ባለስልጣናቱ እንደገለፁት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ከተከለሉበት ቦታ ሆነው ዳኞቹን ለአምስት ደቂቃ ያህል አዋርተዋል።

የፍርድ ሂደቱ እረፍት ላይ እራሳቸውን ስተው ተዝለፍልፈው እንደወቀዱ ተገልጿል።

ሆስፒታል አፋፍሰው ቢወስዷቸውም ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ እንደሞቱ የግብፅ አቃቤ ህግ ገልጿል።

በአሟሟታቸው ዙሪያ ምርመራዎች የቀጠሉ ሲሆን ሰውነታቸውም ላይ የሚታይ ጉዳት እንደሌለ ተገልጿል።

የኃገሪቱ ሚዲያ እንደዘገበው የሞታቸው ምክንያት የልብ ህመም ነው ብሏል።

ሞሀመድ ሞርሲ ከዚህ በፊት በነበረው ፍርድ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ሲሆን በኋላም ውሳኔው ተቀይሯል።

ተያያዥ ርዕሶች