የአለም ተፈናቃዮች ቁጥር ከ70 ሚሊዮን በላይ ደርሷል

ተፈናቃዮች Image copyright SOPA/Getty Images

በባለፈው የፈረንጆች ዓመት በዓለም ዙሪያ አዲስ ከተፈናቀሉ ሰዎች መካከል ኢትዮጵያዊያን ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያወጣው መረጃ አመለከተ።

የተፈናቃዮቹ ቁጥር 1.5 ሚሊዮን ሲሆን ከእነዚህም መካከል 98 በመቶዎቹ እዚያው ሃገር ውስጥ የተፈናቀሉ ናቸው። ይህ አሃዝ ቀደም ሲል ከነበረው ከእጥፍ በሚበልጥ ቁጥር የጨመረ ሲሆን ከዚያም በኋላ ቁጥሩ ጨምሯል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ተፈናቃዮች ለችግር ተዳረግን አሉ

የጌዲዮ ተፈናቃዮች የከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አጋጥሟቸዋል

ለዚህ መጠኑ ከፍተኛ ለሆነው የሃገር ውስጥ መፈናቀል ተጎራብተው በሚኖሩ የተለያዩ ማኅበረሰቦች መካከል ባለፈው ዓመት ባጋጠሙ ግጭቶች ምክንያት እንደሆነ ተጠቅሷል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስር የስደተኞችን ጉዳይ የሚከታተለው አካል በዓለም ዙሪያ በግጭቶች ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር በታሪክ ካጋጠመው ከፍተኛ ቁጥር ላይ መድረሱንም አስታወቋል።

ድርጅቱ በየዓመቱ በሚያወጣው የስደተኞች ሁኔታ ሪፖርቱ ላይ እንዳመለከተው በአሁኑ ወቅት የተፈናቃዮቹ ቁጥር ከ70 ሚሊዮን በላይ ደርሷል።

በጦርነቶችና ጥቃቶችን በመሸሽ ከቀያቸውና ከቤታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ የተነሳ መጠጊያና መፍትሄ ለመስጠት አዳጋች እንደሆነ ድርጅቱ አመልክቷል።

አምስት ነጥቦች ስለጌዲዮ ተፈናቃዮች

የጌዲዮ ተፈናቃዮች ሁኔታ በፎቶ

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጥገኝነት ጠያቂዎች የወጡባት ሃገር ቬንዙዌላ ናት።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት ፊሊፖ ግራንዴ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የተከሰተውን አሳሳቢ የስደተኞች ጫና ተሸክመው የሚገኙት ደሃ ሃገራት ሲሆኑ ባለጸጋዎቹ ሃገራት እገዛ ለማድረግ የበለጠ መስራት አለባቸው።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ መሰረት በዓለም ዙሪያ ካሉ ስደተኞች መካከል ከሁለት ሦስተኛው የሚበልጡት የመጡት ከአምስት ሃገራት ነው። እነሱም ሶሪያ (6.7 ሚሊዮን)፣ አፍጋኒስታን (2.7 ሚሊዮን)፣ ደቡብ ሱዳን (2.3 ሚሊዮን) ማይናማር (1.1 ሚሊዮን) እና ሶማሊያ (900 ሺህ) ናቸው።