የቄለም ወለጋ ዞን ባለስልጣን የተገደሉት ታጣቂዎች ናቸው ብለዋል

ደምቢ ዶሎ

በቄለም ወለጋ ዞን በጋዎ ቄቤ ወረዳ ሽመላ ቀበሌ ውስጥ በመከላከያ ሠራዊት አምስት ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የቄለም ወለጋ ዞን የጸጥታና ህዝብ ደህንነት ኃላፊ አቶ ሃብታሙ ታምሩ በበኩላቸው አምስት ሰዎች በመከላከያ ኃይል መገደላቸውን አረጋግጠዋል።

ነገር ግን እሳቸው እንደሚሉት የተገደሉት ሰዎች ንጹሃን ሳይሆኑ የታጠቁ ሃይሎች ናቸው ብለዋል።

"የመከላከያ ሰራዊት እርምጃ የወሰደው በንጹሃን ዜጎች ላይ ሳይሆን በታጠቁ እና በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ሽፍቶች ላይ ነው" ብለዋል።

በኦነግ እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል በምዕራብ ኦሮሚያ ግጭት እንደነበር ተነገረ

«ኦነግ ሀገር ለመገንጠል ነው የምሠራው ብሎ አያውቅም» ሽጉጥ ገለታ (ዶ/ር)

በምዕራብ ኦሮሚያ የኦነግ ጦር አዛዥ ስለወቅታዊው ሁኔታ ምን ይላል?

የሽመላ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዮሃንስ ወጋ ለቢቢሲ እንደገለፁት "ማክሰኞ ጠዋት የመከላከያ ሰራዊት ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ ህዝቡ ላይ ተኩስ ከፍቶ ነበር" ብለዋል።

በዚህ መካከል አምስት አባወራዎችና ወጣቶች መገደላቸውን አቶ ዮሃንስ ይናገራሉ።

ከተገደሉት ሰዎች መካከል አንዱ የአካባቢው ወጣቶች (ቄሮ) ሃላፊ ነው ብለዋል።

የደህንነታቸው ሁኔታ ስጋት ውስጥ መግባቱን የሚናገሩት አቶ ዮሃንስ ለስደት እንደተዳረጉ ገልፀው "የአካባቢው ነዋሪ አስከሬን እንቅበር ብለው ቢጠይቁም ተከልክለዋል። የአካባቢው ማህበረሰብ ትልቅ ችግር ውስጥ ነው ያለው" ብለዋል።

ሌላኛው የሽመላ ቀበሌ ነዋሪ አቶ መሃመድ የቀበሌው ነዋሪዎች ኦነግን እየደገፋችሁ ነው በማለት ስቃይ እየደረሰባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የተገደሉት ሰዎችን የኦነግ ወታደራዊ ልብስ በማልበስ የኦነግ ወታደሮችን ገድለናል ማለታቸውንም አቶ መሃመድ ገልጸዋል።

አቶ ሃብታሙ በበኩላቸው በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን የተገደሉትም ሆነ የታሰሩት ንጹሃን ዜጎች እንደሆኑ ተደርጎ የሚናፈሰው ወሬ መሰረተ ቢስ ነው ይላሉ።

ከቀድሞው የኦነግ ሰራዊት አባላት መካከል ጫካ የቀሩት ሽፍታ መሆናቸውን አቶ ሃብታሙ ይናገራሉ።

"ከኦነግ ሰራዊት የተነጠሉ ናቸው። ሌላ ስምም የላቸውም። ስማቸውም ከሽፍታ የተለየ ሊሆን አይችልም" ብለዋል አቶ ሃብታሙ።

ኦነግ በቅርቡ በሰጠው መግለጫ በኃይል የታጠቀ ምንም አይነት ወታደር የለኝም ማለቱ የሚታወስ ሲሆን የታጠቀው ሰራዊትም በእኔ የሚመራ አይደለምም ማለቱ የሚታወስ ነው።

በምዕራብ ኦሮሚያ ከሚንቀሳቀሰው የመንግሥት ወታደር ጋር በሚያጋጥሙ ግጭት ምክንያት የግለሰቦች ህይወት እንደሚቀጠፍ የሚወጡ ሪፖርቶች ያሳያሉ።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ