ኢራን የአሜሪካ የቅኝት ድሮንን መትታ ጣለች

የአሜሪካ ድሮን Image copyright US NAVY/KELLY SCHINDLER

የአሜሪካ ወታደራዊ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) በአወዛጋቢው የሆርሙዝ ሰርጥ ላይ በሚገኝ ዓለም አቀፍ የአየር ክልል ውስጥ ከምድር ወደ አየር በተተኮሰ የኢራን ሚሳዔል ተመትቶ መውደቁን የአሜሪካ ባለስልጣናት ተናገሩ።

የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ግን ድሮኗን መትቶ የጣለው ሆርሞዝጋን በተባለው የሃገሪቱ ደቡባዊ ግዛት ውስጥ በሚገኝ የአየር ክልል ውስጥ መሆኑን ገልጿል።

አሜሪካ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ተጨማሪ ወታደር ልትልክ ነው

ትራምፕ በነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ለተፈፀሙት ጥቃቶች ኢራንን ከሰሱ

የአብዮታዊው ዘብ አዛዥ የሆኑት ሜጀር ጄነራል ሆሲን ሳላሚ ለሃገሪቱ መንግሥት መገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት ክስተቱ "ለአሜሪካ ግልጽ መልዕክት" አስተላልፏል ብለዋል።

ይፋዊው የኢራን ዜና ወኪል ኢርና እንደዘገበው እስላማዊው አብዮታዊ ዘብ የአሜሪካንን የቅኝት ድሮን መትቶ የጣለው ትናንት ጠዋት ላይ የኢራንን አየር ክልል ጥሶ ከገባ በኋላ ነው ብሏል።

አብዮታዊ ዘብ ጨምሮም ተመትቶ የወደቀው የአሜሪካ ድሮን አርኪው-4 ግሎባል ሃውክ የተባለ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን አንድ የአሜሪካ ወታደራዊ ባለስልጣን ግን ድሮኑ የአሜሪካ ባሕር ኃይል ኤምኪው-4ሲ ትሪተን የተባለ እንደሆነ ለሮይተርስ ገልጿል።

ይህ ሁኔታ የተከሰተው በኢራንና በአሜሪካ መካከል ያለው ውጥረት እየተባባሰ ባለበት ጊዜ ነው።

ሰኞ እለት የአሜሪካ የመከላከያ መስሪያ ቤት የኢራን ኃይሎች በባሕረ ሰላጤው አካባቢ እያሳዩ ላለው "የጠብ አጫሪነት ባህሪ" ምላሽ ለመስጠት ተጨማሪ 1ሺህ ወታደሮችን እያሰማራ መሆኑን ገልጾ ነበር።

አሜሪካ ባለፈው ሳምንት በኦማን ባሕረ ሰላጤ ውስጥ በሚገኘው የሆርሙዝ ሰርጥ ላይ በፈንጂ ለተመቱት ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ኢራንን ተጠያቂ በማደረግ ብትከስም ኢራን ውድቅ አድርጋዋለች።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
የዓለም የነዳጅ ዋጋ እንዲጨምር ምክንያት የሆነው አሜሪካና ኢራን የተፋጠጡበት የሆርሙዝ ሰርጥ