ለብቻ ልጆችን ማሳደግ፡ የኢትዮጵያውያን ላጤ እናቶች ምርጫና ተግዳሮት

እናትና ልጅ Image copyright Getty Images

ሴቶች በተለያዩ ምክንያቶች ልጆቻቸውን ብቻቸውን የሚያሳድጉ ላጤ እናት (Single Mother) ይሆናሉ። ከአጋራቸው ጋር በሞት አሊያም በፍቺ ሲለያዩ፣ በተፈፀመባቸው ጥቃት ሳቢያ የልጅ እናት ለመሆን ሲገደዱ፤ እንዲሁም የጀመሩት ግንኙነት እንዳሰቡት አልሰምር ሲላቸው ልጃቸውን (ልጆቻቸውን) ብቻቸውን የማሳደግ ውሳኔ ላይ ከሚደርሱባቸው ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ።

ነገር ግን ፈልገውና አቅደው፤ ልጅ ብቻ እንዲኖራቸው በማለም ላጤ እናት (Single Mother) የሚሆኑ ሴቶችም አሉ።

ያለ እናት የመጀመሪያው የእናቶች ቀን

እናት አልባዎቹ መንደሮች

በተለያዩ አገራት የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በተለያየ ምክንያት ልጃቸውን ብቻቸውን የሚያሳድጉ እናቶች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። በአፍሪካ በተለይ በኬንያና በደቡብ አፍሪካ ላጤ እናት የመሆኑ ልማድ እንግዳ አይደለም።

ምንም እንኳን የተሰሩ ጥናቶች ባለመኖራቸው ቁጥራቸውና የጉዳዩ ስፋት ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ ባይቻልም በኢትዮጵያ በተለይ በከተሞች አካባቢ ላጤ እናትነት አንዱ የሕይወት ዘይቤ መሆኑ ይነገራል።

ሴቶች አስበውና አቅደው ለምን ላጤ እናት ይሆናሉ?

"በሕይወቴ ያሰመርኩት ቀይ መስመር ነበር፤ እርሱን ማለፍ ስለማልችል ላጤ እናት ሆኛለሁ" የምትለው የአዲስ አበባ ነዋሪ ናት። ስሟን ያልጠቀስናት የይህች እናት ለትዳር ግን ክብር እንዳላት አልሸሸገችም።

በሕይወቷ የምታስበውና የምታልመው ስላልሆነ የግድ በትዳር መታሰር የለብኝም የሚል አቋም ላይ እንደደረሰች ትናገራለች። ይሁን እንጂ ላጤ እናት መሆን በርካታ ተግዳሮቶች እንዳሉበት ታነሳለች።

እያንዳንዷ ሴት በሰውነቷ ላይ እንዲሁም በምትመሰርተው ቤተሰብ ላይ ውሳኔዎችን ትወስናለች፤ ውሳኔዋም እንደምትኖረው ሕይወት የተለያየ ነው የሚሆነው" የምትለው ደግሞ የሴቶች መብት ተሟጋቿ አክሊል ሰለሞን ናት።

ይሁን እንጂ ሴቶች ፈልገውና አቅደው ላጤ እናት የሚሆኑባቸውን ምክንያቶችንም ትጠቅሳለች። በማህበረሰቡ የሴት ልጅ ሕይወት በጊዜ የተገደበ እንደሆነና እስከተወሰነ ዕድሜያቸው ድረስ ማግባትና መውለድ ካልቻሉ ሕይወታቸው እንደተመሳቀለ ተደርጎ መወሰዱ ለእንዲህ ዓይነት ውሳኔ ከሚገፏቸው ምክንያቶች አንዱ እንደሆነ ትናገራለች ።

አክሊል እንደምትለው በቀደመው ጊዜ አንዲት ሴት ሳታገባ ብትወልድ ለልጁ 'ዲቃላ' የሚል ስያሜ በመስጠት እናትየዋ ትወገዝ ነበር። አሁን ላይ ግን ይህ ልማድ በትንሹም ቢሆን እየቀረ በመሆኑ ሴቶች እንዲህ ዓይነት ውሳኔ እንዲያሳልፉ አደፋፍሯቸዋል።

"ከዚህ ቀደም ሴቶች ሥራ በማይሰሩበትና የኢኮኖሚ ጥገኛ በሆኑበት ጊዜ ልጅ ወልደው ለብቻቸው ማሳደግ የማይታሰብ ነበር" የምትለው አክሊል የሴቶች የኢኮኖሚ አቅም ማደግም ሌላኛው የላጤ እናትነት ምክንያት ነው ትላለች።

እንደ የመብት ተሟጋቿ ከሆነ አንዲት ሴት በሕይወት ያየችው የትዳር ሕይወት እኩልነት የሌለበት፣ ሴቷ ጥገኛ የሆነችበት፣ ጥቃት የሚፈፀምበት፣ የኃይል ሚዛኑ እኩል ያልሆነበት፣ ሁኔታዎች በሙሉ ለሴት የማይመቹ ከነበሩ፤ ይህን ባለመፈለግ ላጤ እናት ልትሆን ትችላለች።

ቢሆንም ግን እኩልነትን እያዩ ያደጉትም ሌሎች ምክንያቶች ወደ ውሳኔው ሊያንደረድሯቸው ይችላል።

በተለያየ መልኩ የሴቶች አቅም እየጎለበተ ቢመጣም ሴቶች አቅማቸውንና የትዳር ሕይወታቸውን ማጣጣም ተስኗቸዋል የሚሉ እንዳሉ ያነሳንላት አክሊል "የሴቶች አቅም እየጎለበተ በመጣ ቁጥር ኃላፊነት እየተደራረበባቸው ነው የመጣው፤ የቤቱን ሳንቀንስ ነው የውጪውን የጨመርንባቸው" ስትል ትሞግታለች።

ማጣጣም ተስኗቸዋል፤ አልተሳናቸውም ለማለት መጀመሪያ ያለባቸው ጫና ሊቀርላቸው ይገባል ትላለች። በተጨማሪም ላጤ እናት መሆንም ይህንን ጫና አያስቀረውም ብላለች።

የልጃቸውን ደፋሪ የገደሉት እናት ነጻ ወጡ

ልጁን ጡት ያጠባው አባት

በአሃ የሥነ ልቦና አገልግሎት አማካሪ የሆኑት አቶ ሞገስ ገ/ማሪያም በበኩላቸው "ይህ ሁኔታ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በከተሞች አካባቢ የሚታይ ልማድ ሆኗል" ይላሉ። የምክር አገልግሎት ፈልገው ወደ እርሳቸው የሚመጡ ላጤ እናቶች መኖራቸውንም ይገልፃሉ።

ባለሙያው እንደሚሉት ጉዳዩ ከሥልጣኔ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው። የኢኮኖሚና በራስ የመተማመን አቅም ሲያድግ የባልና የሚስት ግንኙነት ወደ ጎን ተትቶ ግንኙነቱ ኢኮኖሚ ላይ ብቻ የተመሠረተ ሊሆን ይችላል።

በዚህም ምክንያት ሌሎች ማህበራዊ፣ አካላዊ፣ መንፈሳዊ እሴት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንደማያስፈልግ አሊያም እንደ ሁለተኛ ደረጃ ተወስዶ ሴቶች ላጤ እናትነትን በፍላጎት ይመርጣሉ።

ለንግግራቸው "እኔ በኢኮኖሚ ጥሩ ደረጃ ስለደረስኩኝ፤ ከመጀመሪያውም ጀምሮ የወሰንኩት ሳላገባ ልጅ ለመውለድ ነው" ያለቻቸውን ደንበኛቸውን በምሳሌነት ያጣቅሳሉ።

እንዲህ ዓይነት ሃሳቦች የባልን (የትዳር አጋርን) ሚናና ትርጉም ከማዛባት ጋር የተያያዘም ነው ይላሉ- አቶ ሞገስ።

ባለሙያው እንደሚያስረዱት ላጤ እናትነትን ከኢኮኖሚ ጋር ብቻ ማያያዝ አይቻልም። ጉዳዩ ከራስ ስሜትና አስተሳሰብ ጋር እንዲሁም ካለፈ ታሪክ ጋር የሚያያዝም ነው። በመሆኑም ተፅዕኖውን ውስጣዊና ውጫዊ በማለት ይለዩታል።

Image copyright Getty Images

ውስጣዊ ተፅዕኖ

ለአንድ ውሳኔ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የውስጥ ሁኔታ ነው ይላሉ- የሥነ ልቦና ባለሙያው አቶ ሞገስ። ይህ የውስጥ ሁኔታ የውጫዊ ተፅዕኖ ነፀብራቅም ይሆናል። ለምሳሌ የውስጥ ፍላጎት፣ አመለካከት፣ ቤተሰብ፣ ጎረቤት ወይም አካባባቢ የሚያሳድረው ተፅዕኖ የውስጥ ውሳኔ ላይ ያደርሳል።

"ለራሳችን ያለን የጠነከረ አስተሳሰብና (Ego) ለራስ የምንሰጠው ግምት ከመጠን ያለፈ ሲሆን (Super Ego) ነገሮችን ሁሉ እኔ ማድረግ እችላለሁ፤ እኔ ማድረግ የምችል ከሆነ ሌላ አያስፈልገኝም የሚል ስሜት ይመጣል። በመሆኑም ይህንን ሚዛናዊ ማድረግ ካልተቻለ እዚህ ውሳኔ ላይ በቀላሉ ይደረሳል" ይላሉ።

ውጫዊ ተፅ

እንደ አቶ ሞገስ ከሆነ ፆታን መሠረት ያደረጉ የህብረተሰብ አመለካከትም ለላጤ እናትነት ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድራሉ። የሚፈጸሙ ጥቃቶች፣ የሚደርስባቸው ጫና፣ ሚዛናዊ ያልሆነ ሚና፣ የወንዶች የበላይነትን በመጥላትና በመፍራት፣ አካባቢያችን ያሉ ወይም በሚዲያ የምንሰማቸውና የምናያቸው አርአያዎች በሚፈጥሩት ተፅዕኖ ሴቶች እዚህ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ ያደርጋቸዋል።

በሌላ በኩል ማህበረሰቡ በጉዳዩ ላይ ያለው አቋም ጠንካራ ካልሆነ ሴቶች ውስጣቸው የሚጠይቃቸውን ለማድረግ ዕድሉን ያገኛሉ። የራስ ማንነት እያሸነፈ ሲመጣ፤ አይሆንም የምንላቸው ነገሮች እየበዙ ይመጣሉ። ፍላጎታችንን ማስቀደም ይቀናናል። ስለዚህም ላጤ እናትነት የማህበረሰቡ እሴት እንደተሸረሸረ አንዱ ማሳያ ሊሆን እንደሚችልም ያክላሉ።

ላጤ እናቶች ላይ የሚደርስ ጫና

ያነጋገርናት እናት እንደምትለው ልጆችን ለብቻ ማሳደግ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚና የሃሳብ ጫና አለው። ከማህበረሰቡ፣ ከቅርብ ቤተሰብ እንዲሁም ከልጆች የሚደርሰው ጫናም ቀላል አይደለም።

"ልጆቸ ራስ ምታት እንኳን ሲያማቸው የማካፍለው ሰው አለመኖሩ በጣም ከባድ እንደሆነ ተመልክቸዋለሁ፤ ግን የራሴ መርህ ስላለና እርሱን መታገስና እንደ እናቶቻችን መቻል ስለማልችል ውሳኔውን ወስኛለሁ" ትላለች።

ይህች እናት አዘውትረው ከሚጠቀሱት ጫናዎች በዘለለ የወሲብ ሕይወትን ማጣትም ላጤ እናትነትን ይፈትናል ትላለች። ምንም እንኳን እያንዳንዱ ሰው የየራሱ ወሲባዊ ሕይወት ቢኖረውም እርሷ ግን ከሕይወት አጋር ውጪ ወሲብ መፈፀም እንደማትፈልግ ትናገራለች።

የመብት ተሟጋቿ አክሊል እንደምትለው ውሳኔው የሚያሳፍር ድርጊት ነው ተብሎ በሚቆጠርበት ማህበረሰብ ውስጥ በፍላጎት ላጤ እናት መሆን ማህበራዊ ጫናው ከፍተኛ ነው። እነዚህን እናቶች የሚያግዝ አሠራር ከሌለ በስተቀር ሁሉም ነገር በአንድ ሰው ትከሻ ላይ ብቻ ስለሚወድቅ ኃላፊነቱ ከባድ ይሆናል።

በመሆኑም የኢኮኖሚ ጫናውም ቀላል አይሆንም፤ ይህንን ለማስተካከል ሥራ መስራትና ጊዜን ሥራ ላይ ማጥፋት ይጠይቃል።

"የልጆች ኃላፊነት መደረብም ሁኔታውን ከባድ ያደርገዋል" የምትለው አክሊል በዚህ ሂደት ውስጥ እናትየዋ ለእረፍት ማጣት ስለምትጋለጥ በተለያየ መልኩ ልትጎዳ እንደምትችል ታስረዳለች።

ይህንን የተመለከቱ ጥናቶች በአፍሪካ ብዙም የሉም የሚሉት የሥነ ልቦና ባለሙያው ጉዳቱ ከፍ ያለ ነው ይላሉ። ጫናው ከአካላዊ፣ ማህበራዊ መንፈሳዊና ኢኮኖሚያዊ ደህንነት (wellbeing) ይጀምራል።

በመሆኑም ላጤ እናቶች ካገቡት ይልቅ ለተለያዩ ቀውሶች ሊዳረጉ ይችላሉ። ከእነዚህም መካከል፡

• ኢኮኖሚያዊ ጫና ይበረታባቸዋል

• አካላዊ ጤንነታቸው፤ ከጭንቀትን መቋቋምና ከበሽታ መከላከል አንፃር ይዳከማል

• የስሜት ጥንካሬና መረጋጋት አይኖራቸውም

• ማህበራዊና መንፈሳዊ ድጋፋቸውም የላላ ይሆናል

ከሥነ ልቦና አንፃር ብቸኝነት፣ ድባቴ፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ዋጋ የለኝም ማለት፣ በራስ መተማመን ማጣትና ለማንነት ችግር እንደሚጋለጡም ባለሙያው በዝርዝር ያስረዳሉ።

የልጆቹ አባቶችም ከሴቶቹ ባልተለየ መልኩ የችግሮቹ ተጋሪ ይሆናሉ። የስሜት ጫና፣ ድባቴ፣ ማህበራዊ ጫና ፣ የጥፋተኝነት ስሜት፣ ምቾት ማጣት፣ የፀፀት ስሜት (ልጄን በሚገባው መልኩ ድጋፍና ክትትል እያደረኩለት አይደለም) የሚሉ ሥነ ልቦናዊ ስሜቶች ይታያሉ።

የሴቶችና ወንዶች የኢኮኖሚ እኩልነት እንዴት ይስፈን?

ወንዶች፤ ልጆቻቸውን ሙሉ ለሙሉ ከአጠገባቸው ማጣት ብቻም ሳይሆን በሥነ ልቦና አገልግሎት ውስጥ ገና ለገና እንፋታለን ብለው ሲያስቡ ሚዛናቸውን መሳትና ከፍ ወዳለ የሥነ ልቦና ቀውስ ውስጥ እንደሚገቡም ባለሙያው ያክላሉ።

በልጆች ላይ ምን ተፅሳድራል?

"በተለይ ልጆች እድሜያቸው ከፍ እያለ ሲሄድ ለብቻ ማስተዳደር ፈታኝ ነው" የምትለው ይህች እናት በቤት ውስጥ ኃላፊነትን በማከፋፈል በሕይወታቸው ውስጥ ሚና እንዲኖራቸው በማድረግ ፈተናውን መቋቋም ችላለች።

"ቤታችን ፓርላማ ይመስላል፤ ልጆቼ ተነጋግረው ወስነው እኔ ጋር የሚመጡት ለማፅደቅ ነው፤ በሁሉም ነገር ተሳታፊ ናቸው" ትላለች።

ይህም እነርሱን እንደውም ይበልጥ ጠንካራ እንዳደረጋቸውና ሴት ብቻዋን ልጆች ማሳደግ ትችላለች፤ በማለት እርሷን እንደ አርአያ ማየት እንደጀመሩ ታስረዳለች። በተለይ ወንድ ልጇ በእርሷ መኩራት እንደሚሰማው ትናገራላች።

የምታስማማበት ጉዳይ በትዳር ውስጥ ሆኖ ልጆችን በተገቢው መንገድ ማሳደግ መተኪያ እንደሌለው ነው፤ ነገር ግን ትዳር ለመያዝ ተብሎ አሊያም ያልሆነ ትዳር ይዞ ሕይወትን መግፋት ደግሞ የማታምንበት ጉዳይ።

የሴቶች መብት ተሟጋቿ አክሊል ቤተሰብ የሚባለው ትርጓሜ ከድሮው በተሻለ ተቀይሯል ትላለች። በመሆኑም ልጆች የአባትና የእናትን ሚና ካለማግኘት በበለጠ ማህበረሰቡ የሚያደርስባቸው ጉዳት ያይላል ትላለች።

በተቃራኒው አቶ ሞገስ ልጆች የአባታቸውንና የእናታቸውን ሚና እያዩ ባለማደጋቸው ለተለያዩ የሥነ ልቦና ችግሮች ይዳረጋሉ ይላሉ። በመሆኑም ክሊኒካል (ድብርትና ጭንቀት) እና ባህሪያዊ የሥነ ልቦና ችግሮች ይታዩባቸዋል ይላሉ።

እንደ ባለሙያው ገለፃ ከወንዶች ይልቅ ሴቶች በብዛት ለእንዲህ ዓይነት የሥነ ልቦና ችግር የሚዳረጉ ሲሆን የሚያጋጥማቸውም 'ክሊኒካል' የሚባለው የሥነ ልቦና ችግር ነው።

ወንዶች ደግሞ ባህሪያዊ ችግር ያጋጥማቸዋል፤ ከሁኔታዎች ጋር ተስማምቶ መኖር ይቸግራቸዋል። ችግሮቹ እንደ እናቶቹ ባህሪ የሚወሰን ቢሆንም በትምህርት፣ በሥራና በማህበራዊ ስኬቶቻቸው ላይ ተፅዕኖ ያሳድርባቸዋል ብለዋል።

አቶ ሞገስ ላጤ እናቶች ሁለት ባህሪ አላቸው ይላሉ። አንደኛው ልጆቻቸው ሕይወት ውስጥ ጥሩ ድርሻ ያላቸው፣ ፍቅርና እንክብካቤ በጥሩ ሁኔታ የሚሰጡ (Involved) ሲሆኑ ሌላኛው ደግሞ ልጆቻቸውን ችላ የሚሉና በልጆቻቸው ሕይወት ውስጥ የማይገቡ (Rejecting) ናቸው።

ይሁን እንጂ በሁለቱ የተለያየ ባህሪ የሚያድጉ ልጆች ለተለያዩ ሥነ ልቦና ችግሮች መዳረጋቸው አይቀርም። ጥሩ ድርሻ ያላቸው እናቶች እንክብካቤና ፍቅራቸው ከልክ ያለፈ ስለሚሆን ልጆች ለጥገኝነት መንፈስ ይጋለጣሉ።

በሌላ በኩል ግድ የለሽ በሆኑት እናቶች የሚያድጉት ደግሞ ማግኘት ያለባቸውን የስሜት ደህንነት ስለማያገኙ ቀደም ብለው ለተጠቀሱት የሥነ ልቦና ችግሮች ይዳረጋሉ።

ለምክር አገልግሎት ወደ እርሳቸው ቢሮ ጎራ ከሚሉት ላጤ እናቶች አብዛኞቹ ስሜታቸው ተመሳሳይ መሆኑንና ልጆቻቸው ላይም የድብርት ስሜት ማየት እንደቻሉም ባለሙያው አካፍለውናል።

የሚገጥማቸውን ተግዳሮቶች እንዴት ይፍቱት?

በተለያየ ምክንያት ልጆቻቸውን ብቻቸውን የሚያሳድጉ እናቶች የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች እንዴት ሊቋቋሟቸው እንደሚችሉ የሥነ ልቦና ባለሙያው ይመክራሉ።

• ጤናማ ስሜትና ጤናማ አካል እንዳላቸው ማረጋጋጥ፣

• ከውስጥ ግጭት ነፃ መሆን፤ ፍርሃት ካላቸው ለልጆቻቸው እንዳያስተላልፉ መጠንቀቅ

• ከልጆች ጋር ደረጃ በደረጃ፤ እንደ ዕድሜያቸው ሁኔታ ያለውን ሁኔታ በግልፅ ማሳየት እና

• ልጆች ከአባታቸው ጋር ግንኙነት ሊያስፈልግ እንደሚችል በማመን ከአባታቸው ጋር እንዲገናኙ እድል ማመቻቸት የእነርሱንም ሆነ የልጆቻቸውን ሕይወት በተወሰነ መልኩም ቢሆን ቀላል ያደርገዋል።

በመጨረሻም...

ብዙ ጊዜ ላጤ እናቶች በኢኮኖሚ፣ በአስተሳሰብ፣ በትምህርት የተሻሉ ናቸው ይባላል። ይህንንኑ ጥያቄ ለሴቶች መብት ተሟጋቿ አክሊል አንስተን ነበር።

"ለብቃት (Empowerment) ሰፊ ትርጓሜ በመኖሩ እነዚህ ሴቶች ብቁ ናቸው አይደሉም ማለት አልችልም" ትላለች። ይሁን እንጂ ሰዎች የሚወስኑበት መንገድ ቢለያይም 'ልጅ ካልወለድኩ ሴት አይደለሁም፤ ስለዚህ ጊዜዬ ሳያልፍ ልጅ መውለድ አለብኝ' የምትል ሴት ብቁ (Empowered) እንደሆነች አላምንም፤ ምርጫ ግን ነው" ስትልም ታብራራለች።

ምንም እንኳን ውሳኔው ላይ በምን ምክንያት ተደረሰ የሚለው ወሳኝ ቢሆንም የአንድ ሰው ዋጋው የሚለካው በልጅ መኖርና አለመኖር አይደለም። በመሆኑም ሴትነቷ የሚለካው ልጅ በመውለድ አቅምና ላጤ እናት በመሆን አለመሆኑን በመግለፅ የግል አስተያየቷን ሰጥታለች።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ