ስለ 'መፈንቅለ መንግሥት' ሙከራው እስካሁን የማናውቃቸው ነገሮች

ጄ. ሰዓረ፣ ዶ/ር አምባቸው፤ አዲስ አበባ፣ ባህር ዳር

ቅዳሜ ዕለት አመሻሽ ላይ ባህር ዳር ከተማ በአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ውስጥ እንዲሁም አዲስ አበባ ውስጥ በአገሪቱ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ቤት ውስጥ የተፈጸሙት ጥቃቶች ስላስከተሉት ጉዳት በስፋት ተነግሯል።

የባህር ዳሩ ጥቃት የክልሉን ርዕሰ መስተዳደርንና የአማካሪያቸውን ሕይወት መቅጠፉ በይፋ ቢነገርም የተጨማሪ ሰዎች ሕይወት እንደጠፋበት ለክልሉ አስተዳደር ቅርብ የሆኑ ሰዎች ይናገራሉ።

በቅዳሜው ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸው አቶ ምግባሩ ከበደ አረፉ

በአዲስ አበባው ጥቃት ደግሞ በሥራ ላይ የነበሩና በጡረታ የተገለሉ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ተገድለዋል።

ባህር ዳር ከተማ በቀዳሚነት በክልሉ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት የጀመረው ተኩስ ቁልፍ ከሚባሉት የክልሉ አመራር ክፍሎች መካከል በሚመደቡት የጸጥታ ጽህፈት ቤት፣ የፖሊስ ኮሚሽን እና የክልሉ ገዢ ፓርቲ ጽህፈት ቤት ላይም ጥቃት እንደተፈጸመ ተነግሯል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪ በቴሌቪዥን ቀርበው ባህር ዳር ውስጥ ያጋጠመው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እንደሆነ ይፋ ሲያደርጉ በበርካቶች ዘንድ ጥያቄ አጭሮ ነበር። አሁንም ድረስ ድርጊቱ በባለስልጣናት ላይ የተፈጸመ ጥቃት ነው? ወይስ እንደተባለው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ? የሚለው ዝርዝር ምላሽ ያላገኘ ዋነኛ ጉዳት እንደሆነ አለ።

ታስሯል የተባለው የጄነራል ሰዓረ ጠባቂ ራሱን ማጥፋቱ ተገለፀ

ከዚህ በተጨማሪ ባህር ዳርና አዲስ አበባ ውስጥ ካጋጠመው ክስተት ጋር ተያይዞ በርካታ እያነጋገሩ ያሉና አሁንም ድረስ ግልጽ መልስ ያላገኙ ነገሮች አሉ። ከቅዳሜው ጥቃት ጋር በተያያዘ ያላወቅናቸው ነገሮች የትኞቹ ናቸው?

በከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ የተፈጸመጥቃት ነው? ወይስ የመንግሥት ግልበጣ?

የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እንደሆነ የተገለጸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቃባይ በኩል ሲሆን፤ በርካቶች ክስተቱን የመንግሥት ግልበጣ ብሎ ለመጥራት የሚያበቁ ሁኔታዎች የሉም በሚል ይከራከራሉ። የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሊያስብሉ የሚችሉ ቁልፍ ጉዳዮች በሌሉበትና በሉአላዊ አገር ስር በሚገኝ ግዛት ውስጥ መሆኑ ጥያቄን እያስነሳ ነው።

በጥቃት ፈጻሚዎቹና በክልሉ ባለስልጣናት መካከል እስከ ግድያ የሚያደርስ ቀደም ያለ አለመግባባት ነበር?

ቅዳሜ ዕለት ከነበረው ክስተት ቀደም ብሎ የጥቃቱ መሪ እንደሆኑ የተነገረላቸው ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ፅጌ ምንም እንኳን በተለያዩ አጋጣሚዎች በሚያደርጉት ንግግር ከሌሎች የክልሉ ባለስልጣናት በተለየ አነጋጋሪ ጉዳዮችን አንደሚያነሱ የታወቀ ቢሆንም አለመግባባት እንዳለ በግልጽ የሚያሳዩ ነገሮች አልታዩም ነበር።

ጥቃቱ/የመንግሥት ግልበጣው ምን ውጤት ለማምጣት ያለመ ነበር?

ጥቃቱ ወይም የመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራው ቢሳካ ምን ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል ግልጽ ያለ ነገር የለም። ቢሳካ የፌደራል መንግሥቱ በቦታው እያለ የድርጊቱ ፈጻሚዎች ክልሉን ተቆጣጥረው አላማቸውን የማሳካት ዕድላቸው በጣም ጠባብ ነው።

የሥራ ኃላፊነታቸውን "ከባድና የሚያስጨንቅ... ነው" ያሉት ዶ/ር አምባቸው ማን ነበሩ?

በርዕሰ መስተዳደሩ ጽህፈት ቤት ውስጥ በጥቃቱ ወቅት ምን ተከሰተ?

ጥቃቱ የተፈጸመው የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ስብሰባ በሚያደርጉበት ጊዜ እንደሆነ ተገልጿል። ጥቃት ፈጻሚዎቹ ስብሰባ ላይ በነበሩት የክልሉ አመራሮች ላይ ተኩስ ስለመክፈታቸውና ለግድያ ስለመምጣታቸው ከመነገሩ ወጪ የነበሩ ሁኔታዎችና ስለ ጥቃት ፈጻሚዎቹ ዝርዝር መረጃ አልተሰጠም።

በባህር ዳርና በአዲስ አበባ ከተማ የተፈጸሙት ጥቃቶች አላቸው የተባለው ግንኙነትት ግልጽ ያለመሆን

አዲስ አበባ ውስጥ በጄነራሎቹ ላይ የተፈጸመው ግድያ ባህር ዳር ውስጥ ከተፈጸመው ጥቃት ጋር የሚያገናኘው ነገር እንዳለ በተደጋጋሚ የተገለጸ ቢሆንም በውጤት ረገድ የሁለቱ ክስተቶች ትስስርን በተመለከተ በግልጽ የተቀመጠ ማስረጃ አልተገኘም።

የተገደሉ ባለስልጣናትና ጄኔራሎችን ለመዘከር የሃዘን ቀን ታወጀ

ከከፍተኛ ባለስልጣናትና ጄነራሎች ባሻገር ሌሎች የሞቱ ሰዎች ይኖሩ ይሆን?

የተለያዩ ምንጮች በጥቃቱ የሞቱት ሰዎች አምስት ብቻ ሳይሆኑ ቁጥሩ ከዚያ ከፍ እንደሚል እየተናገሩ ቢሆንም ይፋዊ የክልልና የማዕከላዊ መንግሥት ምንጮች ግን ያሉት ነገር የለም።

ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው ስለተያዙ ሰዎች

ጥቃቱ ተፈጽሞ የመከላከያ ሠራዊት በባህር ዳርና በዙያዋ ከተሰማራ በኋላ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደርን ጨምሮ ለሦስት ሰዎች ሞት ምክንያት ከሆነው ጥቃት ጋር በተያያዘ በክልሉ የተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች የነበሩ ሰዎችና ሌሎችም እንደታሰሩ ይነገራል። ነገር ግን እስካሁን እነማንና ምን ያህል ሰዎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ በይፋ የታወቀ ነገር የለም።

የጥቃቱ መሪ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ጉዳይ?

የአማራ ክልል የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ብርጋዴረ ጄነራል አሳምነው ፅጌ "የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው" መሪ እንደሆኑ ጥቃቱ ከተፈጸመ ከሰዓታት በኋላ ተነግሯል። ነገር ግን ጄነራሉ ይህንን ድርጊት ፈጽመዋል የተባሉት ከነማን ጋር እንደሁነ፣ ክስተቱ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ እንዴት እንዳመመለጡ፣ የት እንደሚገኙና አሁን ስላሉበት ሁኔታ የተለያዩ መረጃዎች እየወጡ ነው። ሰኞ ከሰዓት በኋላ ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ባህር ዳር አቅራቢያ በጸጥታ ኃይሎች ተመትተው መገደላቸው ታውቋል።

ተያያዥ ርዕሶች