"ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብተናል" ምክትል ኢታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላ

የጄነራል ሰዓረ ቤተሰቦች Image copyright ETV

ቅዳሜ ዕለት አዲስ አበባ ውስጥ የተገደሉትን ሁለት ጄነራሎች ለመሸኘት በሚሊኒየም አዳራሽ ውስጥ በተደረገው ሥነ ሥርዓት ላይ የሃገሪቱን ፕሬዝዳንታና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የሃገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከባለስልጣኖቻቸው ጋር ከፊት መስመር ላይ ተቀምጠው እያለቀሱ በሃዘን ውስጥ ሆነው በተደጋጋሚ በቴሌቪዥን መስኮት ላይ ቢታዩም በሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር አላደረጉም።

ስለመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውና ስለግድያው እስካሁን የምናውቀው

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የሟቾቹ ጄነራሎች ልጆች እንዲሁም የጄነራል ሰዓረ ምክትል የሆኑት ጄነራል ብርሃኑ ጁላና የቅርብ ጓደኛቸው ጄነራል አበባው ታደሰ በእንባና በሃዘን የታጀበ ጠንካራ ንግርር አድርገዋል።

"ሠራዊታችንን ለመገንባት ሞዴል የሆኑን የጦር መሪ ናቸው።"

ምክትል ኤታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላ፤ የጄነራል ሰዓረ በ17 ዓመት የነበራቸው አጠቃላይ የትግል እንቅስቃሴ፣ ሠራዊታችንን ለመገንባት እንደ ሞዴል የተጠቀምንበት ታሪክ ነው ብለዋል።

በሠራዊት ግንባታ፣ በውጊያ ዝግጅት፣ በውጊያ አመራር፣ በጀግንነት፣ ችግሮችን ጥሶ በማለፍ፣ ፅናት የተላበሰ የሠራዊት ጄነራል ናቸው ሲሉ ገልፀዋቸዋል።

በሃየሎም ይምሉ የነበሩት ጄነራል ሰዓረ መኮንን ማን ናቸው?

"እንደ እሳቸው ዓይነት ወታደራዊ አመራሮች የሚያንፀባርቁት፣ የሚያሳዩትና የሚውሉበት ውሎ ትውልድን የሚቀርፅ ነው" ያሉት ምክትል ኤታማዦር ሹሙ፤ ጄነራል ሰዓረን የመሰሉ ሌሎች ጀግኖች እንደ ሞዴል እየወሰድን ሠራዊታችንን ሀገሩን መከላከል የሚችልና ለሌሎች የሚተርፍ ጀግና ሠራዊት ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ ዋነኛ ምሳሌ እንደነበሩ ተናግረዋል።

ጄነራል ገዛኢንም አንስተው ለዚህች ሀገር የለፉ ሰው ናቸው በማለት ከሕገ-መንግሥት ምስረታ በኋላ የመከላከያ ሠራዊት አባል ሆነው ትልልቅ ሥራ ሰርተዋል ሲሉ መስክረዋል።

ጄነራል ገዛኢ የመከላከያን ሎጀስቲክ ያደራጁና ባህሉን የገነቡ ናቸው ያሉት ጄነራል ብርሀኑ "የሎጀስቲክ መሀንዲስ ብለን ነው የምናውቃቸው" ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

"ፈጥኖ መዘጋጀት የሚችል ከፍተኛ ኃይል በአንድ ጊዜ ማንቀሳቀስ የሚችል ለሎጀስቲክ የተፈጠረ በሳል መሪ ነበሩረው" ሲሉም አወድሰዋቸዋል።

የሥራ ኃላፊነታቸውን "ከባድና የሚያስጨንቅ... ነው" ያሉት ዶ/ር አምባቸው ማን ነበሩ?

ከጄነራል ሰዓረ ጋር በቅርብ አልሰራሁም ያሉት ምክትል ኢታማዦር ሹሙ እርሳቸው ማዕከላዊ ዕዝ ሆነው ጄነራል ሰዓረ በሌሎች ዕዞች ውስጥ ሆነው እንደሚተዋወቁ ጠቁመው፤ "ጄነራሉ በግል ባህሪያቸው የተረጋጉ፣ ሌላውንም የሚያረጋጉ፣ ሰው አክባሪ ናቸው" በማለትም ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

እንደዚህ በ30 እና በ40 ዓመት የሚፈጠሩ ጄነራሎችም ይሁን የሀገር መሪዎችን ማጣት ያማል ያሉት ጄነራል ብርሀኑ አሟሟታቸውን በማንሳት ቁጭታቸውን ከእንባቸው ጋር እየታገሉ ገልፀዋል።

"ለሀገር እየሰራ፣ ሁሉንም እያቻቻለ፣ ሁሉንም እያገለገለ፣ ሁሉንም እየሰማ፣ ሁሉንም እያስተናገደ ባለበት ወቅት፤ ምን በድሎ ነው የሚገደለው የሚል ጥያቄ ሳነሳ እንደ ግለሰብ ያመኛል" ብለዋል።

ጄነራል ሰዓረ የሥልጣን ጥምና ሩጫ የላቸውም ያሉት ምክትል ኢታማዦር ሹሙ ሰው እንዳይሞት፣ የተፈናቀለ እንዲመለስ ነው እየሰሩ የነበረው ሲሉ ገልፀዋቸዋል።

"እኛ ይኼ ነገር በጣም ቆጭቶናል፤ በጣም አናዶናል፤ ግን ጄነራል ሰዓረ ሲሰራቸው የነበሩ ዓላማዎችን በማሳካት የጄነራሉን ገዳዮች በማሳፈር የእነርሱ ፍላጎት እንዳይሳካ ለማድረግ ቆርጠን እንታገላለን" ብለዋል።

መፈንቅለ መንግሥቱና የግድያ ሙከራዎች

ሠራዊታችን አንድነቱን ጠብቆ የጄነራል ሰዓረን አርማና ፅናትን ይዞ ኢትዮጵያ ሀገሩን ለመጠበቅ በፅናት እንዲቆምም ጥሪ አቅርበዋል።

በጄነራሎቹ ላይ የተፈጸመው ግድያ አላማው "እኛን መበተን ነው" ያሉት ጄነራል ብርሃኑ "በዘር ተከፋፍለን እንድንባላ፣ መንግሥት እንዳይረጋጋና እንዲፈርስ ነው። ሳይረጋጋ ሲቀር በሽግግር ስም ወደ ስልጣን ለመምጣት የሚደረግ ሩጫ ነው" በማለት ይህ እንደማይሳካና እንደሚታገሉት ገልፀዋል።

"በኦሮምኛ አንድ ተረት አለ የማይረባ ሰው ጀግናን ያበላሻል ይባላል። እንደዛ አይነት ነገር ነው ያጋጠመን። ስለሆነም ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብተናል። የክልል አመራር ስብሰባ አዳራሽ ውስጥ የሚረሽኑ የስልጣን ጥመኞች ችግር ፈጥረውብናል፤ እንቁ መሪዎቻችንን አጥተናል፤ ከፍተኛ የሀዘን ድባብ ውስጥ እንገኛለን ግን እናሸንፋለን" ሲሉ ሳግ እየተናነቃቸው ተናግረዋል።

የኤታማዦር ሹም ጄነራል ሰዓረ መኮንን ልጅ መዓሾ ሰዓረ "አባቴ በአንድነት፣ በመቻቻል፣ አብሮ በመስራት የሚያምን፣ ፍፁም ኢትዮጵያዊ ነበር። ጄኔራል ሰዓረ ስለሞተ አገር ይፈርሳል ማለት አይደለም እኛ ጠንክረን ከቆምን ኢትዮጵያን አንድ እናደርጋታለን" ሲል በአባቱ ሞት የተሰማውን ሃዘን የገለፀ ሲሆን ጄኔራል ገዛኢም ይህ እንዳማይገባቸው ከእንባው ጋር እየታገለ ተናግሯል።

የጄነራል ሰዓረ ቀብር አዲስ አበባ ሳይሆን መቀሌ ይፈጸማል

በዚሁ ሥነ ስርዓት ላይ የተገኘው የጄኔራል ገዛኢ አበራ ልጅም ክብሮም ገዛኢ "ገዛኢ ፍቅሩ፣ ዘመን ተሻጋሪ ምክሮቹ፣ በቃላት ተነግሮ የማይገለፅ አባት ሲሆን ለውድ ባለቤቱ ፍፁም የልብና የፍቅር ሰው ነበር። ስብዕናውም ሩህሩህ፣ ሰውን አክባሪ፣ ሰውን በሰውነት ብቻ የሚያከብር፣ ቁጥብ፣ ታጋሽ፣ ብልህ፣ አስተዋይ፣ አርቆ አሳቢ ነበር" ሲል አባቱ ጄኔራል ገዛኢ የነበራቸውን ምግባር በሃዘን ገልጿል።

ጀኔራል ገዛዒ ጡረታ ከወጡ በኋላም ለአገራቸውና ለህዝባቸው ሕይወታቸው እስካለፈበት ቀን ድረስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በሃገርና በህዝብ ጉዳይ የተጠመዱ አባት እንደነበሩም ክብሮም አክሏል።

"ከሰውም በላይ፤ ከሰውም በታች እንዳትሆኑ" እያሉም ይመክሯቸው እንደነበር ክብሮም አስታውሷል። "ጀግኖች ናቸው ፤ ጀግኖች ህያው ናቸው፤ ይሄ ደማቸውም ፈሶ አይቀርም፤ ቃላቸውን እንጠብቃለን" በማለት ተናግሯል።

በዕለቱ ንግግር ያደረጉት የጄነራል ሰዓረ የቅርብ ጓደኛ የሆኑት ጀኔራል አበባው ታደሰ በበኩላቸው "ጀኔራል ሰዓረ በአላማው ፅኑ የሆነ፣ ለህዝብ ጥቅም ራሱን አሳልፎ የሰጠ ፣ ከህዝብ በላይ ራሱን የማያይ፣ ከልጅነቱ ጀምሮ አንድ ቀን ሳይንቀባረር ሕይወቱን ሙሉ ለህዝብ የሰጠ ጀኔራል ነበር" ሲሉ ጀኔራል ሰዓረን አስታውሰዋል።

ጀኔራል ሰዓረ ጀግና ማፍራት የሚችሉ፣ ለችግር መፍትሄ የሚያበጁ ከመሆን አልፈው የሚኳቸውን በርካቶች ማፍራታቸውን ጠቅሰዋል። "በሥራው ምስጉን፣ ጦርነትን በሚገባ የሚያውቅ፣ ጦርነትን በሚገባ የሚያዘጋጅ፣ ብልህ፣ ጠንቃቃ፣ የጀግና የጀግና ምሳሌ ነበር" ብለዋል።

አክለውም ጄኔራል ሰዓረ ኃይማኖት፣ ዘርና ብሔር የማይለዩ፤ በኢትዮጵያዊነታቸው የማይደራደሩ ፍፁም ኢትዮጵያዊ መሆናቸውንም ጀኔራል አበባው መስክረዋል።

ራሱን አጥፍቷል የተባለው የጄነራል ሰዓረ ጠባቂ ሆስፒታል እንደሚገኝ ተገለፀ

ጀኔራል አበባው በንግግራቸው ማሃል "አንድ ነገር ልንገራችሁ... ከፈለገም ይፈንዳ ... " በማለት ለውጡ ከመጣ በኋላ ሰዓረ በጥቂት ቡድኖች እንደ ከሃዲ መቆጠራቸውን ተናግረዋል።

ጄኔራል ሰዓረ ኢትዮጵያዊነቱን አሳልፎ እንዲሰጥም ከፍተኛ ተፅዕኖ ይደርስበት እንደነበርና 'ቤተሰቤ ይበተናል እንጂ፤ ኢትዮጵያዊነቴን አሳልፌ አልሰጥም' ሲሉ ይነግሯቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

"ማንም ይምጣ ማን አስከምሞት ድረስ በኢትዮጵያዊነቴ ሳልደራደር እሰራለሁ" ማለታቸውንም ጨምረው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ አንድን ጦርነት ከሚያሸንፉና ወሳኝ ተብለው ከሚጠሩ ወሳኝ ሥራዎች ከኋላ የሚሰራ የሎጂስቲክ ሥራ መሆኑን ያነሱት ጀኔራል አበባው "ጀኔራል ገዛኢን የሚያክል ሎጂስቲክስ አለ ብዬ አላምንም" ብለዋል።

"ሃሳብ ያመነጫል፣ አስተዋይ ነው፣ አርቆ ያስባል፤ አሁን ላለው ሰላም መሰረት የጣለ ብልህ መሪ ነበር" ሲሉ መስክረዋል።

በጀኔራሎቹ ሞት የተሰማቸውን መሪር ሃዘን ገለፁት ጄኔራሉ ይበልጥ ሃዘኑን ያበረታባቸው ሕይወታቸው በማለፉ ሳይሆን የሞቱበት አግባብ ሁለተኛ ሞት በመሆኑ ነው ብለዋል።

በመጨረሻም ጀኔራሉ "ከዚህ በኋላ ቆም ብለን ብናስብ፤ ጣት ባንጠቋቆም፤ በሃሳብ መማር ካልቻልን በደም አንማርም" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ተያያዥ ርዕሶች