ዶ/ር አምባቸው በሚያውቋቸው አንደበት

ዶ/ር አምባቸው መኮንን

ቅዳሜ ሰኔ 15 2011 ዓ. ም "በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ" ሕይወታቸውን ካጡት መካከል አንዱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር አምባቸው መኮንን ናቸው።

ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ሥርዓተ ቀብራቸው የሚፈጸመው ዶ/ር አምባቸው እንዲሁም አማካሪያቸው አቶ እዘዝ ዋሴና የአማራ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ምግባሩ ከበደ በሚያውቋቸው እንዴት ይታወሳሉ?

አቶ ደሴ አስሜ የአማራ ክልል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሲሆኑ አቶ ደሳለኝ አሰራደ ደግሞ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር የመሠረተ ልማት ጉዳዮች አማካሪ ናቸው።

አቶ ደሴ እና አቶ ደሳለኝ፤ ዶ/ር አምባቸው መኮንን እና በጥቃቱ ሕይወታቸውን ያጡትን ባልደረቦቻቸውን በቅርበት ያውቋቸዋል።

"ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብተናል. . . ግን እናሸንፋለን"

“የኢህአፓና መኢሶን ነገር አማራ ክልል ላይ ሊከሰት ይችላል ብዬ ነበር”

ስለ'መፈንቅለ መንግሥት' ሙከራው እስካሁን የማናውቃቸው ነገሮች

አቶ ደሴ በጥቃቱ ሕይወታቸውን ያጡት ሦስቱም አመራሮች ከልጅነታቸው ጀምሮ ለሕዝብ ለውጥ እና ልማት ለማምጣት ሲታገሉ የቆዩ ናቸው ካሉ በኋላ፤ ''የታየውን ለውጥ በዋነኛነት ከፊት ሆነው የመሩት እነሱ ነበሩ። የመጣው ለውጥ ከግብ ሳይደርስ፤ ሕዝቡ በሚፈልጋቸው ወሳኝ ሰዓት ላይ ማጣታችን ያስቆጫል'' ይላሉ።

''ዶ/ር አምባቸው እጅግ የተለየ ባህሪ ነው ያለው። አመራር ነኝ ብሎ ሳይኮራ ከትልቅ ከትንሹ ጨዋታ የሚወድ፣ ራሱን ዝቅ አድርጎ ከህብረተሰቡ ጋር የሚነጋገር እና ቅን የሆነ አመለካከት ያለው ጓዳችን ነበረ።'' ሲሉ የአማራ ክልል አራት ወራት የመሩትንና በ48 ዓመታቸው ያረፉትን የቀድሞውን የክልሉን ርዕሰ መስተዳደርን ይገልጿቸዋል።

''ሦስቱም ጓደኞቼ ነበሩ'' የሚሉት አቶ ደሴ፤ ከዶ/ር አምባቸው ጋር ይቀራረቡ እንደነበር ይናገራሉ።

''ትምህርት ቤት ሳለ እንኳ ቀዳሚ ተማሪ ነበረ። የተሻለ እውቀት እና ግንዛቤ ስለነበረው ከአገር ውጪ ሄዶ እንዲማር ሁሉ ተደርጓል'' በማለት ይናገራሉ። አቶ ደሴ ዶ/ር አምባቸው በተማሩባቸው የትምህርት ዘርፎች ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ እንደተመረቁ ጨምረው ተናግረዋል።

አቶ ደሳለኝ አሰራደ በበኩላቸው ያጣነው "አራት አመራሮች ነው" ይላሉ። ከብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ፅጌ ጋር በስተመጨረሻ የተፈጠረው ነገር እንዳለ ሆኖ ክልሉ እንዲሁም አገሪቷ አራት ሰዎችን ማጣቷን ይገልጻሉ።

''ሦስቱም አመራሮቹ ጓደኞቼም የሥራ ባልደረቦቼም ነበሩ። ሁሉም አንድ አመራር ሊኖረው የሚገባውን ሰብዕና የተላበሱ ናቸው'' ያሉ ሲሆን፤ ''አማራ ክልል ወሳኝ ሰዎች አጥቷል'' ብለዋል።

አቶ ደሳለኝ ከዶ/ር አምባቸው ጋር የሚተዋወቁት ከ1980ዎቹ ጀምሮ ነው። ''ከአምባቸው (ዶ/ር) የማይተዋወቅ ሰው ለተወሰኑ ደቂቃዎች እንኳ አብሮት ቢሆን ተዋውቆና ተሳስቆ ነው የሚለያየው። ዶ/ር አምባቸው ግልጽ፣ ሃሜት የማይወድ እና የተሰማውን የሚናገር። ለተሰጠው ኃላፊነት ተገዢ የሆነ ሰው ነበር'' ይላሉ።

''አምባቸው ደፋር ነው'' የሚሉት አቶ ደሳለኝ፤ ''ከዛሬ 15 ዓመት በፊት ለመጀመሪያ ግዜ በክልሉ የፖለቲካ ጉዞ ውስጥ በይፋ "የአማራ ህዝብ እንደ ብሄር ጨቋኝ ነው" የሚለው አስተሳሰብ ትክክል አይደለም ብሎ በይፋ የተናገረው አምባቸው ነበር። ይህንን በመናገሩም በግል ሕይወቱ ብዙ ፈተና ገጥሞት ነበር። እነዚያን ፈተናዎች በጽናት አልፎ ለዚህ ኃላፊነት የበቃ ሰው ነበር።'' ይላሉ አቶ ደሳለኝ።

ተያያዥ ርዕሶች