የጦር እና ሲቪል መሪዎቹ ግድያ፡ ከቅዳሜ እሰከ ዛሬ ምን ተከሰተ?

የጄነራሎቹ የቀብር ስነ-ስርዓት Image copyright MICHAEL TEWELDE

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ሥልጣን መያዝ በኋላ በርካታ ሰበር ዜናዎችን ሰምተናል፤ ገሚሱ አስደሳች ገሚሱ ደግሞ አሳዛኝ። የሰሞኑ ግድያ እና መዘዙን የመሠለ ግን ያለ አይመስልም።

አሁንም በርካቶች ከብረት የከበደ ጥያቄ ውስጣቸው እንዳዘለ አሉ። ምንድነው እየተከሰተ ያለው?

እኛ ምላሽ ባይኖረንም ክስተቶቹን በጊዜ ከፋፍለን ለማየት ሞክረናል።

ስለ'መፈንቅለ መንግሥት' ሙከራው እስካሁን የማናውቃቸው ነገሮች

ቅዳሜ

ቅዳሜ ሰኔ 15/2011፤ ከሰዓት 10፡00 ላይ ሰባቱ የአማራ ክልል ባለሥልጣናት ለስብሰባ ተቀመጡ። እነሱም የአማራ ክልል አስተዳዳሪ አቶ አምባቸው መኮንን [ዶ/ር] እና ምክትላቸው አቶ ላቀ አያሌው፣ የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ምግባሩ ከበደ፣ የአስተዳዳሪው አማካሪ አቶ እዘዝ ዋሴ፣ አቶ ዮሃንስ ቧያለው፣ አቶ መላኩ አለበል እና አቶ አብራሃም አለኸኝ ናቸው።

11 ሰዓት ገደማ [ስብሰባው አንድ ሰዓት ያክል ከሄደ በኋላ] ወታደሮች የስብሰባ አዳራሹን ከበቡት። ከግድያው ከተረፉት አራት ባለሥልጣናት ሶስቱ ኋላ ላይ በቴሌቪዥን ቀርበው እንደተናገሩት ከሆነ፤ ወታደሮቹ የስብሰባ አዳራሹን በር ጥሰው ለመግባት ሙከራ ማድረግ ያዙ። ነገር ግን አቶ እዘዝ ዋሴ በሩን እንዳይከፈት አድርገው በመያዛቸው የተቀሩቱ ባለሥልጣናት ሌላ መውጫ ፈልገው ሲወጡ ታጣቂዎቹ አገኟቸው፤ ገደሏቸውም።

ምሽት 1 ሰዓት ከሩብ ገደማ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት ቃል አቀባይ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣብያ ቀርበው 'በአማራ ክልል መንግሥት ላይ መፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ ተድርጓል' ሲሉ ዜናውን ሰበሩ።

ቅዳሜ ምሽት በግምት 3፡00 ገደማ የኢትዮጵያ ጦር ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ሰዓረ መኮንን በገዛ ጠባቂያቸው መኖሪያ ቤታቸው ሳሉ በጥይት መመታታቸው ተነገረ። ጄነራሉ በገዛ ጠባቂያቸው በጥይት ሲመቱ አብረዋቸው የነበሩት ጄነራል ገዛዒ አበራም ጉዳት እንደደረሰባቸው ተነገረ።

ዕኩለ ለሊት ገደማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣብያ ቀርበው ቀኑን ሲነገር የቆየው የባህር ዳሩ ግርግርና የአዲስ አበባው ክስተት እውነት መሆኑን ተናግረው የቆሰሉ እና የሞቱ ሊኖሩ እንደሚችሉ አሳወቁ፤ ስም ግን አልጠቀሱም። የባህር ዳሩና የአዲስ አበባው ጥቃት ግንኙነት እንዳላቸውም ጠቆሙ።

ሰንበት

እሁድ ጠዋት 2፡45 አካባቢ ከሁሉ በፊት ድምፅ ወያኔ በቴሌቪዥን ጣቢያው ኤታማዦር ሹም ጄነራል ሰዓረ መኮንን እና ወዳጃቸው ጄነራል ገዛዒ አበራ መገደላቸውን ሰበረ።

ለጥቆ ደግሞ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያው የአማራ ክልል አስተዳዳሪ አቶ አምባቸው መኮንን እና አማካሪያቸው አቶ እዘዝ ዋሴ በደረሰባቸው ጥቃት መሞታቸውን በሰበር ዜና አሰማ። ይህ የሆነው ታድያ 3፡10 ላይ ነው።

ረፋዱ ላይ መግለጫ የሰጠው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት የተከሰተውና የተዘገበው ሁሉ 'እውነት ነው' ካለ በኋላ፤ የባህርዳሩ ጥቃት መሪ ብራጋዴር ጄነራል አሳምነው ፅጌ ናቸው፤ የአዲስ አበባው ጥቃት ደግሞ በጄነራል ሰዓረ የግል ጠባቂ መፈፀሙን ተናገሩ።

መግለጫው ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ፅጌ ይያዙ አይያዙ ባይጠቅስም የጄነራሉ የግል ጠባቂ ግን ቢቆስልም በቁጥጥር ሥር እንዳለ ነበር የሚያትተው።

ሰኞ

ሰኞ ከተሰሙ ዜናዎች ቀዳሚው የነበረው በቅዳሜ ጥቃት ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩት የአማራ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ምግባሩ ከበደ ማለፍ ነበር። ይህ ዜና የተሰማው ረፋድ 4፡00 ገደማ ነበር።

እኩለ ቀን ላይ ደግሞ ቅዳሜ በተፈፀመው የባህር ዳሩ ግድያ 'ተጠርጣሪ' ናቸው የተባሉት ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ፅጌ በፀጥታ ኃይሎች ተመትተው መገደላቸውን የክልሉን ፖሊስ ኮሚሽን ጠቅሰው ሃገር ቤት ያሉ መገናኝ ብዙሃን ዘገቡ።

ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ መገደላቸው ተገለጸ

ብርጋዴሩ የተገደሉት ከባህርዳር ወደ ጎንደር በሚወስደው መንገድ ላይ ከምትገኘው ዘንዘልማ የተሰኘች ሥፍራ መሆኑም ተነገረ።

ከሰዓቱን ብሔራዊ ቴሌቪዥን ላይ ብቅ ያሉት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር እንዳሻው ጣሰው ጄነራሎቹን ገድሏል የተባለው ጠባቂ ራሱን ማጥፋቱን ተናገሩ።

ሰኞ ምሽቱን ደግሞ ፌደራል ፖሊስ በብሔራዊው ቴሌቪዥን (ኢቢሲ) ቀደም ሲል ራሱ የሰጠውን መግለጫ አስተባብሎ ጠባቂው በሕይወት እንደሚገኝ አስታውቀ።

ራሱን አጥፍቷል የተባለው የጄነራል ሰዓረ ጠባቂ ሆስፒታል እንደሚገኝ ተገለፀ

ማክሰኞ

ማክሰኞ የነበረው ዓብይ ጉዳይ የጄነራሎቹ አስከሬን ሽኝት ነበር።

ሚሊኒየም አዳራሽ በነበረው የአስከሬን አሸኛኘት ሥነ-ሥርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድንና ፕሬዝደንት ሳህለ-ወርቅ ዘውዴ እና ሌሎች በርካት ባለሥልጣናት ተገኝተዋል።

'የመፈንቅለ መንግሥቱ' ሴራ ጠንሳሽ ናቸው የተባሉት የብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌ አስክሬንም ወደትውልድ ሥፍራቸው ላሊበላ የተላከውም ትናንት ማክሰኞ ከሰዓት ነበር። የአከባቢው ባለስልጣናት የብ/ጄነራል አሳምነው አስክሬን ወደ ትውልድ ቀያቸው የተላከው ከቤተሰቦቻቸው በቀረበው ጥያቄ መሰረት መሆኑ ተገልጿል።

የብርጋዴር ጄነራል አሳምነው አስክሬን ላሊበላ ገባ

በቅዳሜው ጥቃት ሕይወታቸው ያለፈው የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች እና በአዲስ አበባ የተገደሉት የጦር ጄነራሎች እንዲሁም የሴራው ጠንሳሽ ናቸው የተባሉት የብ/ጄነራል አሳምነው ጽጌ የቀብር ስነ-ሥርዓት በባህር ዳር፣ መቀለ እና ላሊበላ ዛሬ ተፈጽሟል።

የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች የቀብር ሥነ ሥርዓት ተፈፀመ

ተያያዥ ርዕሶች