የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች የቀብር ሥነ ሥርዓት ተፈፀመ

የከፍተኛ አመራሮች አስክሬን ሽኝት Image copyright Amhara TV

ባሳለፍነው ቅዳሜ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ተፈፀመ በተባለው 'መፈንቅለ መንግሥት' የተገደሉት የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች የአስክሬን ሽኝት ሥነ ስርዓት በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ተደርጎላቸዋል።

ሥርዓተ ቀብራቸውም በበባህር ዳር አባይ ማዶ ቅዱስ ገብርዔል ቤተክርስቲያን ወዳጅ ዘመድ፣ ከፍተኛ የፌደራልና የክልል ባለሥልጣናት እና ነዋሪዎች በተገኙበት ተፈፅሟል።

ዶ/ር አምባቸው በሚያውቋቸው አንደበት

"በዚህ መንገድ መገደላቸው ከፍተኛ የፀጥታ ችግር መኖሩን ያሳያል" ጄነራል ፃድቃን

ለክብራቸው ሲባልም በቀብር ስነ ሥርዓተራቸው 17 ጊዜ መድፍ ተተኩሷል።

በአስክሬን ሽኝት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንንና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የክልልና የፌደራል ባለስልጣናት ተገኝተዋል።

በሥነ ሥርዓቱ የሱዳንና የኤርትራ የልዑክ ቡድን አባላትም መገኘታቸው ተገልጿል።

ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የአዴፓ ሊቀመንበር ደመቀ መኮንን ከእምባ ሳጋቸው ጋር እየተጋሉ ንግግር አድርገዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግራቸውን የጀመሩት "በሰኔ ወር አጋማሽ ለሥራ ወደ ውጭ አገር ከመድረሴ በመጀመሪያ የተቀበልኩት የስልክ ጥሪ ለማመን የሚከብድ፤ ሰውነትን በድንጋጤ የሚያርድ፤ ልብን የሚሰብር መጥፎ መልዕክት የያዘ ነበር" በማለት ነበር።

ለሥራ ወደ ውጭ አገር ከመሄዳቸው ከሰዓታት በፊት ከሦስቱም አመራሮች ጋር በተከታታይ ደውለው በውጭ ቆይታቸው ስለሚሰሯቸው ጉዳዮችና ምክር ሃሳቦቻቸውን አውርተው እንደነበር አስታውሰዋል።

"ልጅነታቸውን ሳይጨርሱ ለህዝብ አገልግሎት ራሳቸውን የሰጡ፤ ለለውጡ ዋጋ ከፍለው፤ ለመጭው ዘመን ብርቱ ክንድ ሆነው በተሰለፉ፤ እንዲህ ዓይነት መርዶ እጅግ ልብ ሚነካ ነው" ሲሉ የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልፀዋል።

ክስተቱ ከሥልጣን ጋር በተያያዘ የነበረውን መጠፋፋት ወደኋላ የመለሰ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ከስሜታዊነት፣ ከጀብደኝነት፣ ከግለኝነት በፀዳ መልኩ መስራት እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።

"ከክህደትና ከእናት ጡት ነካሽነት ውጭ ምን ይባላል" ሲሉ ድርጊቱን የኮነኑት አቶ ደመቀ በባህርዳርና በክልሉ ሌላ የባሰ ችግር እንዳይከሰት የክልሉ ህዝብ የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም ባለስልጣናት ያደረጉትን አስተዋፅኦ አመስግነዋል።

በአገርና በክልል የተያዘውን የለውጥ አጀንዳ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የተሰውትን አመራሮች ሕልምና ትግልም ለማስቀጠል ጠንክሮ መስራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

በመጨረሻም ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ " እነዚህ አመራሮች ለቤተሰቦቻቸው በቂ ጊዜ ሳይሰጡ ለህዝብ ሲሉ ተሰውተዋል፤ በመሆኑም የእነርሱ ልጆችና ቤተሰቦች ሊጨልምባቸው አይገባም፤ መንግሥት ከእነርሱ ጎን ይቆማል" ሲሉም ተደምጠዋል።

"የሥራ ባልደረቦቹን 'ወንድም ዓለም' እያለ ነበር የሚጠራቸው" መዓዛ አምባቸው

በአስክሬን ሽኝት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የሦስቱ አመራሮች ልጆች ስለ አባቶቻቸው ንግግር አድርገዋል።

የዶክተር አምባቸው ልጅ መዓዛ አምባቸው "አባቴ የዋህና ቅን አሳቢ፤ ሰው ሲጣራ ወንድም ዓለም እያለ ነው የሚጠራቸው፣ መከፋፈል አያውቅ፣ ሁሉንም በአንድ የሚያይ፤ የሚፈራው እግዚያብሔርን ብቻ ነው፤ ደሙ ውስጥ ያለው ኢትዮጵያ ብቻ ነው" ብላለች።

ራሱን አጥፍቷል የተባለው የጄነራል ሰዓረ ጠባቂ ሆስፒታል እንደሚገኝ ተገለፀ

"ደሙን ብታዩት ኢትዮጵያ ብቻ ናት፤ ኢትዮጵያን ነው ያፈሰሷት። እኛ ውስጥ ያለውን የሞቀውንና የደመቀውን ቤትህን ትተህ አትሂድ፤ ተው ይቅርብህ ስንለው ለህዝቤ ልኑር፤ አገሬን እስከ እድሜ ልኬ አገለግላለሁ ብሎ ነው... ጥይት በግንባሬ እንዳለ ይሄው አሁን ልንቀብረው ነው" ስትል በለቅሶ ለአባቷ ያላትን ስሜት ተናግራለች።

"ባህር ዛፍ ቢቆረጥ ያበቅላል ቁጥቋጦ፣

ከዛም እየቆየ ለምልሞና አጊጦ፣

አምሳሉን ይተካል አይቀርም ተቆርጦ" በማለትም ተተኪ እንዳላቸው በግጥም መልዕክት አስተላልፋለች።

የአቶ እዘዝ ዋሴ ልጅ ፍቅሬ እዘዝም "ለእነርሱ ይሄ አይገባም ነበር፤ አንድ ቀን እንደ ልጅ ሳያጫውቱን ነው ያለፉት፤ ሙሉ ጊዜያቸውን ለድርጅታቸውና ለአገራቸው ሲሰሩ ነው ያለፉት፤ ጀግና ናቸው፤ እንደሞቱ አንቆጥረውም" ሲል ስለአባቱ የሥራ ባልደረቦች ምስክርነቱን ተናግሯል።

"አባቴ ለእኔ መስተዋቴ ነው። የእኔ ብቻ አይደለም የሁሉም ኢትዮጵያ ነው" ስትል የተናገረችው ደግሞ የአቶ ምግባሩ ከበደ ልጅ ሥነ ምግባሩ ናት። እርሷም እንዲሁ በለቅሶ ነበር ስሜቷን የገለፀችው።

/ር አምባቸው መኮንን

ደቡብ ጎንደር ጋይንት ያደጉት ዶ/ር አምባቸው መኮነን ሲሳይ የ48 ዓመት ጎልማሳ ነበሩ።

በልጅነታቸው የፊዚክስና የሒሳብ ትምህርቶችን አብልጠው ይወዱ እንደነበር የሚነገርላቸው ዶ/ር አምባቸው ሕልማቸው መምህር መሆን ነበር።

የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በወቅቱ በነበረው ጦርነት ምክንያት ለማቋረጥ ተገደዋል። ከዚያም ትግሉን ከተቀላቀሉ ከ5 ዓመታት በኋላ ያቋረጡትን ትምህርት በርቀት አጠናቀዋል።

የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ያገኙት ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ነው። የድኅረ ምረቃ ትምህርታቸውን ደግሞ ደቡብ ኮሪያ በሚገኘው ኬዲአይ የፐብሊክ ፖሊሲና አስተዳደር ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።

በቅድመ ምረቃም ሆነ በድኅረ ምረቃ ያጠኑት የትምህርት ዘርፍ ምጣኔ ሐብትን ነው።

ከኮሪያ ተመልሰው ለ11 ዓመታት በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች ካገለገሉ በኋላ ለሦስተኛ ዲግሪ ትምህርት ወደ እንግሊዝ አቅንተዋል።

ሦስተኛ ዲግሪያቸውንም እንዲሁ በምጣኔ ሐብት ዙርያ ከእንግሊዙ ኬንት ዩኒቨርስቲ ነው ያገኙት።

በበጀት እጥረት ምክንያት ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ለማቋረጥ ጫና እንደነበረባቸው፤ ጓደኞቻቸው ገንዘብ በማዋጣት ጭምር ያግዟቸው እንደነበር ከዚህ ቀደም ካፒታል ለተሰኘው ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።

ዶ/ር አምባቸው ከትጥቅት ትግሉ በኋላ ከወረዳ ጀምሮ አስተዳደራዊ አገልግሎት ሰጥተዋል። በዋናነት ከሚጠቀሱት መካከል በአማራ ክልል የሥራ አመራር ኢንስቲቲዩት ዳይሬክተር፣ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ የአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም የኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊነቶች ይገኙባቸዋል።

በፌዴራል ደረጃ ደግሞ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር ኾነው ለአንድ ዓመት ያህል አገልግለዋል።ከዚያ በኋላም የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር በመሆን ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል ጊዜ ሰርተዋል።

“የኢህአፓና መኢሶን ነገር አማራ ክልል ላይ ሊከሰት ይችላል ብዬ ነበር”

ከግንቦት 2010 ዓ.ም ጀምሮ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው ለአጭር ጊዜ ያገለገሉ ሲሆን፣ ከሕዳር 2011 ዓ.ም ጀምሮ የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ሆነው እስከ ተሾሙበት የካቲት 29/2011 ዓ.ም ድረስም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ት ቤት የመሠረተ ልማት አማካሪ ሚኒስትር ኾነው አገልግለዋል።

ዶ/ር አምባቸው ከለውጡ በኋላ ለርዕሰ ብሔርነት ታጭተው እንደነበርና ሕዝቡም ሆነ ፓርቲያቸው በፖለቲካው ተሳትፏቸው እንዲቀጥሉ በመፈለጋቸው ሐሳባቸውን መቀየራቸው ሲነገር ነበር።

አቶ ምግባሩ ከበደ

አቶ ምግባሩ ከበደ በደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ በ1966 ዓ.ም የተወለዱ ሲሆን ሥራ የጀመሩት የወረዳና ዞን ዐቃቢ ህግ በመሆን ነበር።

የምስራቅ ጎጃም ዞን አቅም ግንባታ መምሪያ ኃላፊ፣ የደብረ ማርቆስ ከንቲባ፣ የምስራቅ ጎጃም ዞን አስተዳዳሪ፣ የአዴፓ የገጠር ፖለቲካና አደረጃጃት አማካሪ፣ የአደፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት ኃላፊ፣ የርዕሰ መስተዳድሩ አማካሪ፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ደረጃ የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ኃላፊ በመሆን ሕይወታቸው አስካለፈበት ጊዜ ድረስ አገልግለዋል።

አቶ ምግባሩ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ተፈፀመ በተባለው መፈንቅለ መንግስት ጥቃት ደርሶባቸው ጉዳት ካጋጠማቸው በኋላ በህክምና ሲረዱ ቆይተው ሰኔ 17/2011 ዓ.ም ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።

አቶ ምግባሩ የሦስት ወንድና የሁለት ሴት ልጆች አባት ነበሩ።

አቶ እዘዝ ዋሴ

አቶ እዘዝ ዋሴ በ1957 ዓ.ም በደቡብ ጎንደር አስቴ ወረዳ ዲስጎ አበርጎት አካባቢ ተወለዱ።

አቶ እዘዝ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሥራ አመራር ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ተከታትለዋል።

በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊነቶች ላይ ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን ሕይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ የአማራ ክልል የርዕሰ መስተዳድሩ የህዝብ አደረጃጀት አማካሪ በመሆን አገልግለዋል።

አቶ እዘዝ የሦስት ወንድና የሁለት ሴት ልጆች አባት ነበሩ።

ተያያዥ ርዕሶች