የብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌ የቀብር ሥነ ሥርዓት ተፈፀመ

ብ/ጀኔራል አሳምነዉ ፅጌ

የብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ፅጌ የቀብር ሥነ ሥርዓት ዛሬ ሰኔ 19 ቀን 2011 ዓ.ም በላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት በቤተ ጊዎርጊስ የቀብር ቦታ መፈፀሙን የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ማንደፍሮ ታደሰ ለቢቢሲ ገለፁ።

የብርጋዴር ጄነራል አሳምነው አስክሬን ላሊበላ ገባ

ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ መገደላቸው ተገለጸ

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች የብርጋዴር ጄነራሉ ሕልፈት ከተሰማ አንስቶ በሁሉም የአካባቢው ነዋሪዎች ሃዘንና ድንጋጤ እንደነገሰ ነው ብለዋል።

ትናንት የብርጋዴር ጄነራሉን አስክሬን አውሮፕላን ማረፊያ ድረስ በመገኘት አቀባበል ማድረጋቸውን የሚናገሩት የከተማው ነዋሪና የቀብር ሥነስርዓት አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል፤ አባይ ወዳጀ አስክሬኑ የእርሳቸው መሆኑን ሳጥናቸውን ከፍተው እንዳረጋገጡ ገልፀውልናል።

አቶ አባይ የብርጋዴር ጄነራሉን አስክሬን አጅቦ የመጣ የመንግሥት አካል እንዳልነበርም አክለዋል።

አስክሬኑ ከአውሮፕላን ማረፊያ ወደ ተዘጋጀለት ማረፊያ - አደባባይ ተብሎ በሚጠራ ሥፍራ ያረፈ ሲሆን ሌሊቱን ሙሉ ፀሎተ ፍትሃት ሲደረግላቸው፤ ነዋሪዎችም ሃዘናቸውን ሲገልፁ አድረዋል።

ዛሬም ከተለያዩ አካባቢዎች በመኪና የመጡ ወጣቶችን ጨምሮ ፖሊስና ሚሊሻ፣ ከተማ አስተዳደሩ፣ ነዋሪዎች በጋራ በመሆን በደማቅ ሁኔታ ሥነ ስርዓቱን ለመፈፀም የተለያዩ ዝግጅቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል።

"ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በተኩስ ከተማዋ ተናውጣለች [በሃዘን ወቅት በሚተኮስ ተኩስ]፤ ሁሉም ሃዘንተኛ ነው" የሚሉት አባይ፤ " 'አሳምነው ፅጌ እንዲህ ዓይነት ድርጊት አይፈፅምም፤ ይጣራልን. . . አማራ ክልል አንድነት እንዳይኖረው ተደረገ ሴራ ነውየታሰሩት እነ ጀኔራል ተፈራ ማሞ ይፈቱልን' " የሚሉ መፈክሮች ሲሰሙ መዋላቸውን ነግረውናል።

ስለ'መፈንቅለ መንግሥት' ሙከራው እስካሁን የማናውቃቸው ነገሮች

በአካባቢው እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች ይነሱ እንጂ በከተማው የተፈጠረ የፀጥታ ችግር አለመኖሩን አክለዋል።

"ትናንት ከሰዓት ጀምሮ ዛሬም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዝግ ነበሩ" ያለችን ደግሞ ስሟ እንዲገለፅ ያልፈለገች የከተማው ነዋሪ ናት።

እርሷ እንደምትለው የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ደማቅ የነበረ ሲሆን የተለያዩ ጥያቄዎችም በህብረተሰቡ ይነሱ እንደነበር ነግራናለች።

"ጄነራል አሳምነው ባለፈው ዓመት ለአሸንድዬ በዓል አከባበር ላሊበላ ተገኝተው ንግግር ሲያደርጉ 'ከዚህ በኋላ የምኖረው ለአማራ ህዝብ ነው' ብሎ ስለተናገረ 'አማራን ለማፋት የተደረገ ሴራ ነው' እያሉ ነዋሪዎች መንግሥትን እየኮነኑ፣ ጥይት እየተተኮሱ፤ በፉከራና ቀረርቶ ታጅቦ ሥነ ሥርዓቱ ተከናውኗል'' በማለት የነበረውን ድባብ ገልፃልናለች።

ተያያዥ ርዕሶች