"ሌሎችንም ከፍተኛ ባለስልጣናት የመግደል ዕቅድ ነበረ" የፀጥታና ፍትህ የጋራ ግብረ ኃይል

የኢትዮጵያ ባንዲራ

ባህር ዳርና አዲስ አበባ ውስጥ ባለፈው ቅዳሜ ካጋጠመው ግድያ በተጨማሪ የድርጊቱ ፈጻሚዎች ሌሎች የከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናትን የመግደል ዕቅድ እንደነበራቸው ተገለጸ።

ከተለያዩ የመንግሥት አካላት ተወጣጥቶ ተፈጸመ የተባለውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራና ግድያዎችን ክስተት እየተከታተለ ያለው የፀጥታና ፍትህ የጋራ ግብረ ኃይል ሐሙስ ምሽት ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው የድርጊቱ ፈጻሚዎች "ተከታታይ ግድያ በሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ላይ ጭምር ለመውሰድ አቅደው ነበር።"

ግብረ ኃይሉ አክሎም ከመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውና ከግድያዎቹ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ ሁለት መቶ ሃምሳ አምስት ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ያስታወቀ ሲሆን፤ እነዚህም 212 ሰዎች በአማራ ክልል እንዲሁም 43 ሰዎች ደግሞ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ መያዛቸውንና በተጨማሪም በርካታ መጠን ያላቸው የጦር መሳሪያዎችና ጥይቶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አመልክቷል።

ራሱን አጥፍቷል የተባለው የጄነራል ሰዓረ ጠባቂ ሆስፒታል እንደሚገኝ ተገለፀ

የጦር እና ሲቪል መሪዎቹ ግድያ፡ ከቅዳሜ እሰከ ዛሬ ምን ተከሰተ?

ከቅዳሜው ክስተት ጋር በተያያዘም ሌሎች ጥቃቶችን ለመፈጸም የሚያስችሉ ዕቅዶችና ሰነዶች በጸጥታ ኃይሎች ተይዘው ምርመራ እየተደረገ መሆኑን የፀጥታና ፍትህ የጋራ ግብረ ኃይል አሳውቋል።

በባህር ዳር በክልሉ መስተዳደር ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ ግድያ በመፈጸም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መደረጉ ከተገለፀ ሁለት ቀናት በኋላ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ እንደተገደሉ የተነገረው ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌና ግብረ አበሮቻቸው ድርጊቱን እንደፈጸሙ በተጨባጭ መረጃዎች ማረጋገጡን ጠቅሶ "ስልጣንን በኃይልና በመሳሪያ አፈሙዝ ለመያዝ የተደረገ" ያለውን ሙከራንም ግለሰቡ ማቀነባብራቸውን ግብረ ኃይሉ አመልክቷል።

በተጨማሪም ግብረ ኃይሉ በመግለጫው ላይ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነውና ግብረ አበሮቻቸው "የመንግሥትን ይቅር ባይነትና ሆደ ሰፊነት ወደ ጎን በመተው፤ ክህደት በመፈጸም እና ከዚህ አልፎ ሕዝብ ከሕዝብ ጋር በማጋጨት፣ ሥልጣን በኃይል እና በአቋራጭ ለመያዝ፣ ሐገራችንን እና ሕዝቦቿን ለመበታተን ተንቀሳቅሰዋል" ሲል ከሷቸዋል።

ግብረ ኃይሉ በመግለጫው «ማናቸውም የሽብር እንቅስቃሴዎችን አንታገስም» ሲል አስጠንቅቋል።

የጦር እና ሲቪል መሪዎቹ ግድያ፡ ከቅዳሜ እሰከ ዛሬ ምን ተከሰተ?

“የኢህአፓና መኢሶን ነገር አማራ ክልል ላይ ሊከሰት ይችላል ብዬ ነበር”

ከዚህ በተጨማሪም ግብረ ኃይሉ አዲስ አበባ ውስጥ በቤታቸው ውስጥ ግድያ የተፈጸመባቸውን የሃገሪቱን ጦር ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ሰዓረ መኮንንና ባልደረባቸውን ሜጀር ጄነራል ገዛኢ አበራን ገድሏል ተብሎ የተጠረጠረውን የጄነራሉን የግል ጠባቂ ማንነት ይፋ አድርጓል።

በዚህም መሰረት ግብረ ኃይሉ በመግለጫው አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ መኮንን ሁለቱን ጄነራሎች በመግደል መጠርጠሩን ከፎቶ ግራፍ ጋር አቅርቧል። አክሎም ተጠርጣሪው ጥቃቱን ከፈጸመ በኋላ ቆስሎ በቁጥጥር ስር እንደሚገኝ አመልክቷል።

ግብረ ኃይሉ አክሎም በባህር ዳሩ ከፍተኛ አመራሮች ግድያና በአዲስ አበባው የከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ግድያ መካከል ያለውን ግንኙነት እያጣራ መሆኑን ገልጿል

ባለፈው ቅዳሜ ስለተሞከረው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራና የከፍተኛ ሲቪልና ወታደራዊ ባለስልጣናት ግድያን በተመለከተ እስካሁን አገኘሁ ያለውን መግለጫ የሰጠው የፀጸጥታና ፍትህ የጋራ ግብረ ኃይል የሃገር መከላከያ ሠራዊትን፣ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጽህፈት ቤትን፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን እንዲሁም የፌደራል ፖሊስን ያካተተ መሆኑ ተነግሯል።

ተያያዥ ርዕሶች