ኢትዮጵያ ከገባችበት የፖለቲካ ቅርቃር እንዴት ትውጣ?

አቶ የሱፍ ያሲን፣ ዶ/ር ሰማኸኝ ጋሹ እና ፕሮፌሰር ሼትል ትሮንቮል
አጭር የምስል መግለጫ አቶ የሱፍ ያሲን፣ ዶ/ር ሰማኸኝ ጋሹ እና ፕሮፌሰር ሼትል ትሮንቮል

የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እንደሆነ በመንግሥት የሚገለጸው የባህር ዳሩ አመራሮችና የአዲስ አበባ ጄነራሎች ግድያ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አስተዳደርን ፈተና ውስጥ ከከተቱ ጉዳዮች መካከል ቀዳሚው ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ይህ ክስተት ከሚኖረው ዘላቂ አንደምታ አንጻር በርካታ ትርጓሜ እየተሰጠው ነው።

በርካቶች ያልተጠበቀ ነገር እንደሆነ የሚገልጹት ይህ ሁኔታ የቀድሞው ዲፕሎማትና የፖለቲካ ተንታኝ አቶ የሱፍ ያሲንና በአሜሪካ ኤንዲኮት ኮሌጅ የሰብዓዊ መብትና ዓለም አቀፍ ህግ መምህር የሆኑት ዶ/ር ሰማኸኝ ጋሹ በሃገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ እንደዚህ ያለ አደጋ ሊፈጠር እንደሚችል የሚያሳዩ ምልክቶች እንደነበሩ ይናገራሉ።

"ሌሎችንም ከፍተኛ ባለስልጣናት የመግደል ዕቅድ ነበረ"

"ክስተቱ ያስደነግጣል ነገር ግን ያልተጠበቀ አይደለም" የሚሉት አቶ የሱፍ ከባድ ችግር ሊከሰት እንደሚችል የሚያመላክቱ በርካታ አስጊ ሁኔታዎች በአማራም ይሁን በሌሎች ክልሎች ውስጥ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ እንደታዩ ጠቅሰው "ነገር ግን በዚህ መልክ ወደ መጠፋፋት ይደርሳል የሚል ግምት አልነበረኝም" ይላሉ።

ዶ/ር ሰማኸኝም የሃገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ከፈት ባለበት የለውጥ ጊዜ ውስጥ ብሔርተኛ ኃይሎች ጉልበት አግኝተው መውጣታቸው እየተከሰቱ ላሉት ችግሮች ምክንያት እንደሆነ ያነሳሉ።

ይህ ደግሞ "በሚሊሻ፣ በቄሮ ወይም በፋኖ መልክ፤ ሁሉም ግን የራሱን መብት ለማስጠበቅ፣ ሌላውን እንደ ስጋትና እንደ ጠላት የሚያይበት ሁኔታ ተፈጥሯል" በማለት ሰኔ 15 2011 ዓ.ም የተፈጠረው ዓይነት ትልቅ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ያስታውቅ እንደነበር ያስረዳሉ።

ከአንድ ዓመት በፊት ኢትዮጵያ በአስቸጋሪና በመስቀለኛ መንገድ ላይ ናት እየተባለ ሲነገር ቆይቶ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ "በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ስጋት እየቀነሰ፣ ተስፋ እየገዘፈ እየመጣ ነበር" የሚሉት አቶ የሱፍ በቦታው የሚታዩት ይህን መሰል ግጭቶች፣ መፈናቀሎችና መጠራጠሮች የተጀመሩትን የለውጥ እርምጃዎች የሚያደናቅፍና የታየውን ተስፋ ሊያጨልም ይችላል ይላሉ።

የሥራ ኃላፊነታቸውን "ከባድና የሚያስጨንቅ... ነው" ያሉት ዶ/ር አምባቸው ማን ነበሩ?

ለዚህ ደግሞ ብሔርን መሰረት ያደረገው ፌደራሊዝም አለመተማመንና አንዱ ሌላውን እንደ ጠላት እንዲያይ ክፍተት የሚተው ነው የሚሉት ዶ/ር ሰማኽኝ፤ ባለፉት 27 ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ ደረሱ በተባሉት በደሎች ምክንያትነት የተለያዩ ሃሳቦች ተነስተዋል ሲሉ ያስረዳሉ።

የሰሞኑ ክስተትም ከዚህ ጋር እንደሚያያዝ የሚያምኑት ዶ/ር ሰማኸኝ "ምን ዓይነት ብሔርተኝነት የተሻለ የአማራን ሕዝብን ጥቅም ያስከብራል በሚለው ላይ በአማራ ልሂቃን መካከል ያለመግባባት ውጤት ነው።"

ባለፉት 27 ዓመታት ሃገሪቱን በፍጹም የበላይነት ሲያስተዳድር የነበረው ኢህአዴግ በጠንካራ ክንድ አሁን በየቦታው የሚከሰቱትን አሳሳቢ ችግሮች በአስተዳደራዊ፣ በፖለቲካዊ እንዲሁም በወታደራዊና በደኅንነት ተቋሞቹ በኃይል ተቆጣጥሮ ቢቆይም ለውጡ ያመጣው ነጻነት ችግሮቹ በየቦታው እንዲከሰቱ እንዳደረገ ይነገራል።

አንዳንዶች እንዲያውም የሚታዩት አሳሳቢ ነገሮች የቀድሞው ጠንካራ ገዢ ፓርቲን መዳከም አመላካች እንደሆነ ይጠቅሳሉ። የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርብ የሚከታተሉት ፕሮፌሰር ሼትል ትሮንቮል እንደሚሉት "የኢሕአዴግ ማዕከላዊ ጥንካሬ መፍረክረክ የጀመረው ከዚህ ክስተት ቀደም ብሎ ህወሐት ከማዕከሉ ገሸሽ ከተደረገ ጀምሮ ነው" ይላሉ።

አክለውም ሃገሪቱ ውስጥ እየተከሰቱ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በተለይ የገዢው ፓርቲ ትልልቆቹ አባላት ኦዴፓና አዴፓ በአንድነት መስራት እንዳለባቸው ይመክራሉ። "ኦዴፓ ከፍተኛ ጥንቃቄ ካላደረገ የአዴፓን ድጋፍ ሊያጣ ይችላል። የአማራና የኦሮሞ ፖለቲከኞች ጥምረት ከተዳከመ ማዕከላዊ መንግሥቱን ማዳከሙ አይቀርም" ይላሉ።

"በዚህ መንገድ መገደላቸው ከፍተኛ የፀጥታ ችግር መኖሩን ያሳያል" ጄነራል ፃድቃን

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አስተዳደር ሕግና ሥርዓትን በመላው ሃገሪቱ በማስከበር በኩል መውሰድ ያለባቸውን ያህል እርምጃ አለመውሰዳቸው መንግሥታቸውን በደካማነት እንዲታይና ይህም ወቀሳ እንዲሰነዘርባቸው አድርጓል።

አቶ የሱፍ ያሲንም "ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመጡ በኋላ መንግሥት እንደ መንግሥት ግርማ ሞገሡንና ሉዓላዊነቱን አላስከበረም በዚህም ምክንያት በመላው ሃገሪቱ ከሥርዓትና ከሕግ ውጪ ብዙ ነገሮች ሲደረጉ ቆይተዋል" ይላሉ።

"ጠንካራና ኃያል ገዢ እንጂ መሪ የሚባለው በብዙ መልኩ አይወጣልንም ወይም አይዋጥልንም" የሚሉት አቶ የሱፍ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተከሰቱ ያሉ ሁኔታዎችን "ለማስተካከልም ሆነ ጠንካራ አመራር ለመስጠት ፈርጠም ያሉ እርምጃዎችን ወደ መውሰድ መገፋፋታቸው አይቀርም" በማለት ይህ ደግሞ ቀድሞ ወደነበረው ሁኔታ ሊመልስ እንደሚችል ይሰጋሉ።

የሰሞኑ ክስተት ከፖለቲካው ባሻገር የደህንነት መዋቅሩ ያለበትን ክፍተት የሚያሳይ ነው የሚሉት ደግሞ ፕሮፌሰር ሼትል ትሮንቮል ናቸው። "ድርጊቱ የተፈጸመው በአማራ ክልል ልዩ ኃይል ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን እነሱም አጠቃላይ የሃገሪቱ የጸጥታ አካል ናቸው። የጸጥታ መዋቅሩ በዚህ ደረጃ መዳከሙ አሳሳቢ ነው። መንግሥት የጸጥታ መዋቅሩን ሊፈትሸው ይገባል" ይላሉ።

ፈታኙን ጊዜ ለማለፍ

ባለፈው አንድ ዓመት በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ያጋጠሙት አሳሳቢ ሁኔታዎች ከጊዜ ጋር እየሰከኑና መፍትሄ እያገኙ እንደሚሄዱ ሲነገር ቆይቷል። ነገር ግን ባህር ዳርና አዲስ አበባ ውስጥ ያጋጠመው ችግር ገና ብዙ መደረግ ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ የሚያመለክት ከባድ ፈተና እንደሆነ እየተነገረ ነው።

አሁን እየታዩ ያሉት ችግሮች ወደፊት ሊከሰቱ ለሚችሉ የከፉ ችግሮች የማስጠንቀቂያ ምልክቶች ናቸው፤ አቶ የሱፍ ያሲን "ሁሉም ይረጋጋ፤ ያረጋጋ የሚለውን ሃሳብ ተግባራዊ ማድረግ አለበት። ሃሳብ ከሚሰጠው ጀምሮ ስልጣን ላይ ያሉት ሰዎች በሙሉ መረጋጋትና ከስሜታዊነት በመራቅ እየተከሰቱ ያሉት ነገሮች ሃገሪቱንና ሕዝቧን ወዴት ሊወስዱት እንደሚችሉ በኃላፊነት ስሜት ለመረዳት መሞከር አለባቸው" ይላሉ።

ከዚህ በተጨማሪ ዶ/ር ሰማኽኝ ጋሹ የታሪክ ተቃርኖዎች በሚሏቸው ጉዳዮች ላይ በመነጋጋር እንደ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብና እንደ አንድ ሃገር እንዴት እንቀጥል ብሎ ተነጋግሮ ብሔራዊ እርቅ ላይ የመድረስ አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት ይሰጣሉ።

ለዚህም የገዢነትና የጭቆና ትርክቶች እንዲሁም በሥራ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥት ጨምሮ ባሉ ጉዳዮች ላይ በግልጽ በመነጋገር የጋራ መግባባት ላይ የመድረስን አስፈላጊት ይናገራሉ።

ስለዚህ እነዚህ ተቃርኖዎች እንዴት ይታረቁ? ሲሉ ይጠይቃሉ ዶ/ር ሰማኸኝ፣ ጠ/ሚ ዐብይ በንግግር ደረጃ ኢትዮጵያዊነትን በማስቀደምና እርቅን በማድረግ እነዚህ ተቃርኖዎች ለማስታረቅ ሞክረዋል።

በተግባር ግን መፍትሄ ተብለው የቀረቡ ነገሮች መሰረታዊውን ችግር የሚፈቱ እንዳልሆኑ ይናገራሉ።

አሁን ጠ/ሚ ዐብይ ሲፈልጉ እንደሚጋብዙት ዓይነት ሳይሆን ሁሉንም የፖለቲካ ሃይል የሚያሳትፍ ሁሉን አቀፍ የሽግግር ሂደት አገሪቱ የተጋረጠባትን ፈተና የምታልፍበት ሁነኛ መንገድ ነው ይላሉ።

"ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብተናል. . . ግን እናሸንፋለን"

አቶ የሱፍም በቀዳሚነት በየክልሉ የሚታዩ ግጭቶችና መፈናቀሎችን ማስቆም እንደሚያስፈልግ በማንሳት "በፖለቲካ ልሂቃኑ መካከል ባሉ የሚቃረኑ ፍላጎቶችና መጠራጠሮች ላይ በመነጋገር ሰጥቶ በመቀበል መርህ ስምምነት ላይ መደረስ አለበት።"

ሁሉንም ነገር በአንድ ጀንበር መቀየር ሃገሪቱን ለከፋ ምስቅልቅል የሚዳርጋት ስለሆነ፤ ያለምንም ጥድፊያ በረጅም ጊዜ ሂደት መደረግ ያለባውን ጉዳዮች በመለየት ማንም ሳይገለል ይመለከተኛል የሚሉ ሁሉም ወገኖች ተሳታፊ ሆነው የጋራ መግባባትና ስምምነት ላይ መድረስ ወቅቱ የሚጠይቀው ነገር እንደሆነ አቶ የሱፍ ይገልጻሉ።

ሰሞኑን ከተከሰተው ጉዳይ ጋር በተያያዘ በርካታ ጥርጣሬን የሚያጭሩ ነገሮች እየተከሰቱ በመሆናቸው "የተፈጠረውን ነገር በማጣራትና በመመርመር ረገድ ገለልተኛ አካላትን ማሳተፍ ተአማኒነት እንዲኖር ያደርጋል ብለው እንደሚያስቡ የሚናገሩት ዶ/ር ሰማኸኝ አክለውም መንግሥት "በአሁኑ ወቅት የአማራ ክልል ዋናውን ሥራ እንዲሰራ በማድረግ፤ የፌደራል ፖሊስም ሆነ ሌላ የፌደራል የፀጥታ ኃይል በክልሉ የሚወስዳቸው እርምጃዎች የተቆጠቡ መሆን አለባቸው" ይላሉ።

"ብ/ጄነራል አሳምነው በባጃጅ ለማምለጥ ሲሞክሩ ነው የተገደሉት''

በርካቶች ሃገሪቱ አሳሳቢ ሁኔታ እንደገጠማት ይስማማሉ፤ ቀጣይ አቅጣጫዋ ወደ የት ሊያመራ እንደሚችል ማወቅ የበርካቶች ፍላጎት ነው። ፕሮፌሰር ሼትል ትሮንቮል እንደሚሉት "ኢትዮጵያ በመጪዎቹ አጭር ጊዜያት አንገብጋቢና ጊዜ የማይሰጡ ጥያቄዎችን መፍትሄ ልታገኝላቸው ይገባል" ይላሉ።

ከእነዚህም ውስጥ በሚቀጥለው ዓመት ግንቦት ወር ይደረጋል ላይ የሚባለው ምርጫ ዋነኛው ጉዳይ ነው። እየተከሰቱ ካሉ ሁኔታዎች አንጻር ሃገሪቱ እንዴት ነው ሰላማዊ ምርጫ የምታደርገው? የሚለው አሳሳቢ ነገር እንደሆነ ጠቅሰው "ምርጫውንም አለማድረግም ሌላ ፈተና" እንደሆነ ፕሮፌሰር ሼትል ያመለክታሉ።

ኢትዮጵያ ከገጠማት ፈተና አንጻር ከችግር ለመውጣት በፖለቲካ ልሂቁ መካከል ሃቀኛ ንግግር ማድረግና ሰጥቶ በመቀበል ስምምነት ላይ መድረስ ወሳኝ እንደሆነ በርካቶች ያምናሉ።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ