አምስት ሰዎች ደቡብ ወሎ ለጋምቦ ውስጥ በደቦ ጥቃት ተገደሉ

የደቡብ ወሎ ካርታ

ሰኔ 21 ቀን 2011 ዓ. ም በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን፣ ለጋምቦ ወረዳ "ህጻናት አፍነው ሊወስዱ ነው" በሚል አምስት ግለሰቦች በአካባቢው ነዋሪዎች በደቦ መገደላቸውን የለጋምቦ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አባተ አረጋ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሰዎቹን በመግደል ከተጠረጠሩት ግለሰቦች መካከል እስካሁን አራት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የለጋምቦ ወረዳ የአስተዳደርና ፀጥታ ኃላፊ አቶ ከበደ ይማም ለቢቢሲ አረጋግጣዋል።

በኢትዮጵያ የመንጋ ፍትህ የሰው ህይወት እየቀጠፈ ነው

አቶ አባተ እንደተናገሩት፤ አምስቱ ግለሰቦች በአንድ የወረዳው ነዋሪ ቤት አርፈው ነበር። በወረዳው እየተንቀሳቀሱ ሳለም "ህጻናት አፍነው ይወስዳሉ" የሚል ያልተጣራ መረጃ ተሰራጭቶ ስለነበር የአካባቢው ማኅበረሰብ ጥቃት ሰንዝሮባቸዋል፤ በደረሰባቸው አሰቃቂ ድብደባም ሕይወታቸው አልፏል።

አምስቱ ግለሰቦች በተገደሉበት ቦታ ወደ 300 ሰዎች ገደማ እንደነበሩና ፖሊሶች ሁኔታውን መቆጣጠር ስላልቻሉ መሸሻቸውንም ተናግረዋል።

ግለሰቦቹ "ህጻናት አፍነው ሊወስዱ ነው የሚል ውዥንብር ተፈጥሮ ነበር" የሚሉት አቶ አባተ፤ "ድርጊቱ ቢፈጸም እንኳን ለፖሊስ ተላልፈው ይሰጣሉ እንጂ በእንዲህ አይነት አሰቃቂ ሁኔታ ሰው መገደል የለበትም" ብለዋል።

ድርጊቱን በማውገዝ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ውይይት እያደረጉ መሆኑንም አክለዋል።

እንደወጡ የቀሩት ተመራማሪዎች

ኦቶ ከበደ "ይህ አሳፋሪና አሳዛኝ ድርጊት የተፈጸመው ልጅ ሳይታፈን በጥርጣሬ ብቻ ነው። ሕዝብ በደቦ ፍትህ መስጠት እንደሌለበትም ከኅብረተሰቡ ጋር እየተነጋገርን ነው" ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ደቡብ ወሎ ውስጥ አንድ ልጅ ታፍና ተወስዳለች የሚል መረጃ ተሰራጭቶ ነበር። ከዚህ ውጪ ግን በአካባቢው ከልጅ ማፈን ጋር የተያያዘ ነገር ተከስቶ አንደማያውቅ ገልጸዋል።

ግለሰቦቹ ከአዲስ አበባ፣ ከከሚሴ፣ ከሳይንትና ከደሴ ወደ ወረዳው የሄዱ ሲሆን፤ አንደኛው ግለሰብ ከየት አካባቢ እንደሄደ አለመታወቁን አቶ ከበደ ገልጸዋል።

ሰዎቹ "ዘመድ ለመጠየቅ" ወደ አካባቢው ማቅናታቸውን እንደተናገሩ ግልጸው፤ ወደ አካባቢው የሄዱበት ምክንያት እስከሚጣራ ድረስ ያሳረፋቸው ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን ጨምረው ተናግረዋል።

በሶማሌ ክልል ከ10 የሚበልጡ አብያተ ክርስትያናት ጥቃት ደረሰባቸው

መታወቂያቸው ላይ ባለው መረጃ መሰረት ግለሰቦቹ በግብርና፣ በንግድ፣ የተሰማሩ እንደነበሩ አቶ ከበደ ገልጸዋል።

"ግለሰቦቹ በዱላና ምሳር ጥቃት ደርሶባቸዋል፤ በአካባቢው ተኩስም ነበር" ሲሉ የጸጥታ አስተዳዳሪው የደረሰውን ጥቃት ተናግረዋል። የግለሰቦቹ አስክሬን ወደ የቤተሰቦቻቸው መላኩንና የሦስቱ ሥርዐተ ቀብር መፈጸሙን ገልጸዋል።