በደቡብ ወሎ 'የህፃናት ስርቆት' ስጋት መነሻ ምንድን ነው?

ህጻን የሚያናግር ግለሰብ Image copyright Getty Images

ሰኔ 21 ቀን 2011 ዓ.ም በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን፣ ለጋምቦ ወረዳ 'ህፃናት አፍነው ሊወስዱ ነው' በሚል አምስት ግለሰቦች በአካባቢው ነዋሪዎች በደቦ መገደላቸው ይታወሳል። ይህ ግለሰቦችን በደቦ እስከመግደል የሚያደርስ የህፃናት ስርቆት ስጋት መነሻው ምንድን ነው?

አምስት ሰዎች ደቡብ ወሎ ውስጥ በደቦ ጥቃት ተገደሉ

የደሴ ከተማና የለጋምቦ ወረዳ ነዋሪዎች በተለይ ካለፉት ሁለት ወራት አንስቶ 'ልጆቻችን ይሰረቁብናል' በሚል ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደወደቁ ይናገራሉ።

ስማቸውን እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ነዋሪዎች ልጆቻቸው ለጨዋታም ቢሆን ለአፍታ ከዓይናቸው ሥር ሲሰወሩ ወዲያው ወደ አዕምሯቸው የሚመጣው መሰረቃቸው እንደሆነ ነው የሚገልፁት።

ለጋምቦ ወረዳ ነዋሪ የሆኑ አንዲት ወላጅ "ልጆችን መቆጣጠር በጣም አስቸጋሪ ቢሆንም ከወትሮው በተለየ ከዓይናችን ሥር እንዳይጠፉ ክትትል ለማድረግ ተገደናል" ሲሉ ስጋታቸውን ያካፍላሉ።

የደሴ ከተማ ነዋሪ የሆኑ አንድ አባት ደግሞ ልጆቹ ከሚማሩበት ትምህርት ቤትም 'ልጆቻችሁን በጊዜ ከትምህርት ቤት ውሰዱ፤ በእረፍት ጊዜያቸው ሲጫወቱም ክትትል አድርጉላቸው' የሚል ማስታወሻ እንደሚላክላቸው ነው የሚናገሩት።

ነዋሪዎቹ በተለይ በየአካባቢው የሚናፈሰው የህፃናት ስርቆት ወሬ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደከተታቸው ገልፀውልናል።

ስጋቱ እንዴት ሊፈጠር ቻለ?

ጊዜውን በውል ባያስታውሱትም ከአንድ ወር በፊት የሆነ ነው። የደቡብ ወሎ ዞን ሐይቅ ከተማ ላይ አንዲት እናት ልጇን ለማሳከም ወደ ጤና ተቋም ታመራለች።

እዚያም ከአንዲት ነጭ ገዋን ከለበሰች ሴት ጋር ይገናኛሉ። ሴትዮዋም 'ልጅሽ በጣም ታማለች ለተሻለ ህክምና ደሴ መሄድ አለባት' ትላታለች - የህክምና ባለሙያ በመምሰል።

እናትም የህክምና ባለሙያ ከመሰለቻት ሴት ጋር ህጻኗን ይዘው ወደ ደሴ ያመራሉ። በሁኔታው የተደናገጠችው እናት ለባለቤቷ እንኳን ስልክ ለመደወል ፋታ አላገኘችም ነበር።

ወደ ደሴ ጉዞ ከጀመሩ በኋላ ደውላ ገንዘብ ይዞ እንዲከተላት ለባለቤቷ መልዕክት አስተላለፈች። ከዚያም ደሴ ከተማ 'ምስጋናው' የተባለ የግል ክሊኒክ ይዘዋት ይገባሉ። በመሃል 'ባልሽን ተቀበይ እኔ ልጅሽን እይዛለሁ' ትላታለች።

ሴትዮዋ የህክምና ባለሙያ ናት ብላ እምነት ለጣለችባት ሴት ልጇን ትታ ዞር ስትል ነበር ሴትዮዋ የተሰወረችው።

ከዚያም ለደሴ ከተማ ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ ሪፖርት ተደርጎ ክትትል ይጀመራል። በአጋጣሚ ተጠርጣሪዋ ተቀምጣበት የነበረው ወንበር ላይ ትንሽ ቦርሳ ያገኛሉ። ቦርሳውን ሲከፍቱት ግን የተፋቀ የሞባይል ካርድ እንጅ ሌላ ቁስ የለውም።

ካርዱ በማን ስልክ እንደተሞላ በማጣራትና ከአጎራባች ከተሞች ፖሊስ ጋር በመነጋገር ኬላዎች እንዲዘጉና ፍተሻ እንዲደረግ ተደረገ። በመጨረሻም 'ነጭ ገዋን ለባሿ ሴት' አፋር ክልል አዋሽ አርባ ኬላ ላይ በቁጥጥር ሥር ዋለች። ህጻኗም በማግስቱ በሰላም ከቤተሰቦቿ ጋር ተቀላቀለች።

ድርጊቱን አቀነባብራለች ተብላ የተጠረጠረችው ሴት እና አሽከርካሪውን ጨምሮ ሦስት ወንዶች በቁጥጥር ሥር ውለው በደሴ ማረሚያ ቤት ይገኛሉ።

ይህንን ልብ-ወለድ የመሰለ እውነተኛ ታሪክ ያጫወቱን የደሴ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ደረጀ አሰፋ፤ ከዚህ ቀደም በደሴ ከተማ ከሚገኝ 'አሊፍ' ከተባለ የግል ትምህርት ቤት ሁለት ዕድሜያቸው ሰባት ዓመት ገደማ የሆኑ ህጻናት ጠፍተው በክትትል ከከተማ ወጣ በሚል ቦታ መገኘታቸውን ያነሳሉ። በጉዳዩ የተጠረጠሩት ግለሰቦችም ተመሳሳይ ሆነው ተገኝተዋል።

ተጠርጣሪዋ "ባለቤቴ ወደ ውጭ አገር ሲሄድ ነፍሰ-ጡር ነኝ ብየው ስለነበር፤ ያን የዋሸሁትን ነገር ለመሸፈን ብየ ነው ያደረግኩት" የሚል መልስ እንደሰጠች ኮማንደሩ ያክላሉ። እውነተኛ ምክንያቱን ለማጣራትም ምርመራ እየተደረገ እንደሆነ ነው የሚያስረዱን።

ይህ ክስተት ከተፈጠረ አንስቶ በከተማውና በተለያዩ ወረዳዎች ወሬው በስፋት መራገብ ጀመረ። ሕብረተሰቡም ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ወደቀ።

360 ብር ለአንድ ሕጻን

"በወንድሜ ለአምስት ዓመታት ተደፍሬአለሁ"

የደቡብ ወሎ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ተወካይ ግን ከሐይቅ ከተማው ስርቆት ሌላ ሕፃን ጠፋብኝ ብሎ ሪፖርት ያደረገ ሰው እንደሌለ ይገልፃሉ።

የተናፈሰው ወሬ ምን አስከተለ?

በደቡብ ወሎ ዞን ለጋምቦ ወረዳ ህፃናትን አፍነው ለመውሰድ የመጡ ሰዎች ናቸው በሚል አምስት ሰዎች በደቦ ጥቃት መገደላቸውን፤ የሰማነው ሰኔ 21 ቀን 2011 ዓ.ም ነበር።

ግለሰቦቹ በአንድ የአካባቢው ነዋሪ ቤት አርፈው ነበር፤ ካረፉበት ቤት ወጣ ብለው በአካባቢው እየተንቀሳቀሱ ሳለ ነው በሕብረተሰቡ በደረሰባቸው ጥቃት ሕይወታቸው ያለፈው።

የወረዳው አስተዳዳርና ፀጥታ ኃላፊ አቶ ከበደ ይማም አምስቱ ግለሰቦች በተገደሉበት ሥፍራ ወደ 300 ሰዎች ገደማ እንደነበሩና ፖሊሶች ሁኔታውን መቆጣጠር ስላልቻሉ መሸሻቸውንም ነግረውናል።

ኃላፊው አክለውም በወረዳው ከዚህ ቀደም ሕፃን ስለመሰረቁ የደረሳቸው ሪፖርት እንደሌለና በስጋት ተነሳስተው ድርጊቱን እንደፈፀሙት ነው የሚያስረዱት።

ድርጊቱን ፈፅመዋል የተባሉ 8 ተጠርጣሪዎችም የተለዩ ሲሆን አምስቱ በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሆነ የፀጥታ ኃላፊው ነግረውናል።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ተወካይ ኮማንደር ለማ ተስፋየ በለጋምቦ ወረዳ የደቦ ጥቃቱ ከተፈፀመ በኋላ በቦረና ወረዳም 'ህፃን ሊሰርቅ ነው' በሚል አንድ ግለሰብ ታግቶ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ይሁን እንጂ በግለሰቡ ላይ ምንም ጥቃት ሳይደርስ በፖሊስ ክትትል ሊለቀቅ እንደቻለ ይገልፃሉ።

"ደላላው ወደ ቤቱ ወሰደኝ፤ በዚያው ቀን አስገድዶ ደፈረኝ"

'በሕብረተሰቡ ክፍተኛ ስጋት የፈጠረ አሉቧልታ አለ' የሚሉት ኮማንደር ደረጀ በከተማው ጢጣ በሚባል አካባቢ አንድ ጥቆማ ደርሶ በጅምላ አንድን ግለሰብ ለመግደል ተሞክሮ በከፍተኛ ጥረት ሊተርፍ ችሏል ብለዋል።

እንዲሁም በደሴ ከተማ አራዳ አካባቢ ሌላ ግለሰብ በህብረተሰቡ ድብደባ ደርሶባታል። ይሁን እንጂ ኮማንደሩ እንዳሉት የፖሊስ ምርመራ ውጤቱ ጉዳዩ ከህፃናት ስርቆት ጋር እንደማይገናኝ ያሳያል።

"በደሴ፤ በጢጣ እና በአራዳ የሆነው ከህፃናት ስርቆት ጋር ባይገናኝም፤ እንዲህ ዓይነት ወንጀሎች የሉም ማለት ግን አይደለም" የኮማንደር ደረጀ አስተያየት ነው።

በለጋምቦ ወረዳ በደቦ የተገደሉት ግለሰቦች እነማን ናቸው?

አምስቱ ግለሰቦች ከአዲስ አበባ፣ ከከሚሴ፣ ከሳይንትና ከደሴ የመጡ ሲሆን፤ አንደኛው ግለሰብ ከየት አካባቢ እንደመጣ አለመታወቁን የለጋምቦ ወረዳ አስተዳደርና ፀጥታ ኃላፊ አቶ ከበደ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ወደ አካባቢው ያመሩት በቁጥር ስድስት መሆናቸውን የሚገልፁት ኃላፊው እስካሁን አንደኛው ማምለጡንና እየተፈለገ መሆኑን አክለዋል።

ግለሰቦቹ ወደ አካባቢው 'ዘመድ ለመጠየቅ' እንዳቀኑ መግለፃቸውን፤ አሁን ግን ወንጀል ለመፈፀም በአካባቢው የተሰማሩ ሰዎች እንደነበሩ አንዳንድ ማስረጃዎች እየወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል- አቶ ከበደ። ምን ዓይነት ወንጀል? ለምን ዓላማ? የሚለውን ፖሊስ እያጣራ ነው ብለዋል።

ለጊዜው አሳርፏቸው የነበረው ግለሰብም በወቅቱ ድብደባ ስለደረሰበት በሕክምና ላይ እንደሚገኝ ገልፀው የተገደሉት ግለሰቦች መታወቂያቸው ላይ ባለው መረጃ መሰረት አስክሬናቸው ወደ የቤተሰቦቻቸው መላኩንና የአራቱ ሥርዓተ-ቀብር መፈጸሙን ሰምተናል።

የአንደኛው ግለሰብ መታወቂያ ላይ ያለው አድራሻ ግን ሀሰተኛ በመሆኑና ቤተሰብ ጋር ማገናኘት ባለመቻሉ ሥርዓተ ቀብራቸው በወረዳው መፈፀሙን አቶ ከበደ ነግረውናል።

ምን እየተሰራ ነው?

ሕብረተሰቡ ልጆቹን የመከታተልና፣ የማስተማር፣ አካባቢውን የመጠበቅ፣ ልጆችን የሚያታልሉ እንኳን ቢኖሩ ልጆች በጨዋታ ቦታ፣ መንገድ ላይም ሆነ በትምህርት ቤት እንዳይታለሉ ማስተማርና ክትትል ማድረግ እንዳለበት ኮማንደር ደረጀ ያሳስባሉ።

"ከሌላ ቦታ ለሌላ ጉዳይ የሚመጣንና የሚንቀሳቀስን ሰው፤ 'ህጻናት ሊያፍኑ ነው' በማለት በተሳሳተ ስጋት አላስፈላጊ ጉዳት ከማድረስ መቆጠብ አለበት፤ ከተጠራጠረም ለህግ መጠቆም አለበት" የኮማንደሩ መልዕክት ነው።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ተወካይም "ማንኛውም ሰው ህፃን ሊሰርቅ እንደማይመጣ፤ የሚሞክርም ቢኖር ተባብረው ለህግ ማቅረብ እንዳለባቸው ከህዝቡ ጋር ውይይት እየተካሄደ እንደሆነና ህብረተሰቡም 'ድርጊቱን እንዳወገዘው' ያስረዳሉ።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ