“በአሁኗ ኢትዮጵያ በፀረ ሽብር ሕጉ ክስ መኖር የለበትም” ዳንኤል በቀለ

ዳንኤል በቀለ Image copyright Getty Images

የሰብአዊ መብት ተሟጋችና ጠበቃ ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) በሂውማን ራይትስ ዋች ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግሏል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከ2011 እስከ 2016 የተቋሙ የአፍሪካ ክንፍ ዋና ዳይሬክተር ነበር። ኦክስፋም፣ አርቲክል 19፣ የዓለም ባንክ እና ዩኤስኤድን አማክሯል።

በበርካታ የሲቪል ማኅበራት ውስጥ የሠራው ዳንኤል፤ የ97ቱ ምርጫ ነጻ እንዲሆን እንዲሁም ሰብአዊ መብት እንዳይጣስ ያላሰለሰ ጥረት አድርጓል። ከምርጫው በኋላ የተፈጠረውን ቀውስ ለማርገብም ሞክሯል። በዚህም ለእሥር ተዳርጎ ነበር።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 2009 ላይ ላይ 'አሊሰን ደስ ፎርጅስ አዋርድ ፎር ኤክስትራኦርዲነሪ አክቲቪዝም' የተሰኘ ሽልማት አግኝቷል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመጀሪያ ዲግሪውን በሕግ፣ ሁለተኛ ዲግሪውን ደግሞ በሪጅናል ዴቨሎፕመንት ስተዲስ አግኝቷል። በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ በሌጋል ስተዲስ ሁለተኛ ዲግሪ የያዘ ሲሆን፤ ፒኤችዲውን በዓለም አቀፍ ሕግ አግኝቷል።

ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ባለፈው ማክሰኞ ሰኔ 25/2011 ዓ. ም. በኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ሆኖ ተሹሟል። ይህንን ተከትሎም ከቢቢሲ አማርኛ ጋር ቆይታ አድርጓል፤ እነሆ . . .

እሾማለሁያውም ባሰረህ በኢህአዴግ መንግሥት እሾማለሁ ብለህ አስበህ ታውቃለህ? ይህ ቀን ይመጣል ብለህ ታስብ ነበር?

ዳንኤል በቀለ ይህ ቀን ሊመጣ ይችላል ብለህ ታስብ ነበረ ወይ? ለተባለው ኢትዮጵያ ውስጥ የዚህ አይነት ለውጥ ሊመጣ ይችላል ብለህ ታስብ ነበር ወይ? ማለት ከሆነ፤ አስብ ነበር። እንደሚመጣ ይሰማኝ ነበር። እኔ ራሴ ግን ያለሁበትን ሁኔታ ከሆነ ይህንን በተለየ አስቤው አላውቅም።

ይሄኛውን [በኢህአዴግ መንግሥት መሾምን] በጭራሽ አስቤ አላውቅም በእውነት። እመኝ የነበረው ለአገሬ የሰብአዊ መብት መከበር፣ የሰብአዊ መብት መስፋፋት ወይም የዴሞክራሲ መዳበር ወይም በአጠቃላይ ለአገሬ ሰላም፣ እድገት፣ ብልጽግና በማንኛውም አይነት መንገድ አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁና ፍቃደኛ መሆኔን አስበዋለሁ።

ረዥም ጊዜ የሠራሁት በሲቪል ማኅበር ድርጅቶች ውስጥ ስለነበረ፤ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ውስጥ አስተዋጽኦ ላደርግ እችላለሁ እያልኩ አስባለሁ እንጂ የዚህ አይነቱን ሹመት፣ የዚህ አይነቱን ኃላፊነት በተለይ በኢህአዴግ መንግሥት ሊሆን ይችላል ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር።

አምነስቲ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ለውጥ እንዲደረግበት ጠየቀ

ነገር ግን ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው የኢህአዴግ አስተዳደር በነበረበት ዴሞክራሲያዊ ያልሆነና የሰብአዊ መብቶችን በሚረግጥ መንገድ የነበረው አስተዳደር ግን ዘላቂ እንዳልሆነ፣ ማንኛውም ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ ሥርዓት በአንድ ወቅት ላይ ከውስጡ የለውጥ ሀዋርያት ሊወለዱ እንደሚችሉ፣ ከውስጡ የሚወለዱ የለውጥ ሀዋርያት ደግሞ የተሀድሶ አጀንዳ ሊመሩ እንደሚችሉና በእንደዚህ አይነት መንገድ ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል አስብ ነበር።

በእርግጥ ደግሞ ሌላ የሚያስፈራ፣ ሌላ አሳሳቢ ሁኔታም ሊፈጠር ይችል ይሆን ነበር የሚለው ስጋት እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው።

ከ1997 ምርጫ በኋላ ከተነሳው ቀውስ ጋር ተያይዞ ለሁለት ዓመት ያህል ታስረሀል። ያንን የእስር ጊዜ እንዴት ነው የምታስታውሰው?

ዳንኤል በቀለየእስሩን ዘመን እንዴት ታስታውሰዋለህ ለሚለው፤ መቼም እንደሚታወቀው እስር አስቸጋሪ ጊዜ ነው፤ ጥሩ ጊዜ አይደለም። በተለይ የኢትዮጵያ እስር ቤት እና በተለይ ደግሞ ያኔ እኛ ታስረን የነበረበት ጊዜ አስቸጋሪና ከባድ ጊዜ ነበር።

ነገር ግን እኔ ከማስታውሰው ነገር ውስጥ አንዱ ከራሴ የሚበልጥ በቤተሰቤ ላይ የተፈጠረው ችግርና መጉላላት ሁልጊዜም አልረሳውም። አሁንም ሰው ሲታሰር ብዙ ጊዜ ስለቤተሰቦቻቸው አስባለሁ።

ከዚያ በተረፈ ግን እስር ጥሩ ነገር ባይሆንም ያንን እስር አሁን የማስታውሰው በምሬት፣ በንዴት፣ በቁጭት፣ በበቀል ስሜት ሳይሆን ይልቁንም በሕይወት ውስጥ ሊያጋጥም እንደሚችል አንድ ችግር፣ አንድ መሰናክል ከዛም ደግሞ የምወስደውን ትምህርት ወስጄ ሕይወትን መቀጠል እንደሚቻል በማስታወስ ነው።

በእስር ቤት ውስጥ በነበርኩ ጊዜ ደግሞ የራሴን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ በርካታ እስረኞች የሚገኙበት ቦታ ምን እንደሚመስልም ለማየትም የሚያስችል ሁኔታ ስለሆነ፤ በኢትዮጵያ እስር ቤት ውስጥ ያሉ እስረኞች አይነታቸው፣ ብዛታቸው፣ የታሰሩበት ጉዳይ አይነት፣ የእስር ቤቱ አያያዝ የመሳሰለውን ነገር ሁሉ ለማየት እድል ይሰጣል።

ስለዚህ ከዚያ አንጻር አንድ ላየው የማልችለው የነበረ ነገርን እንዳይ እድል የሰጠኝ ይመስለኛል። እስር ጥሩ አይደለም ግን ነገሩ እዚያ ውስጥ ሆነሽ ከተገኘሽ ግን የሚያሳይሽን ነገር መመልከት ጥሩ ነው። እና ያንን ስላሳየኝ ጠቃሚ ትምህርት ሰጥቶኛል ብዬ አስባለሁ።

ለዓመታት የኢትዮጵያን ሰብአዊ መብት አያያዞችን ስትተች ነበር። በቅርቡ ደግሞ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነል። ይህንን ቦታ ስትቀበል ምን አይነት ማሻሻያዎችን ከግምት ውስጥ አስገብተህ ነው? የእስረኞች መፈታት የመሳሰሉ ያየናቸው ማሻሻያዎች አሉ።

ዳንኤል በቀለኢትዮጵያ ውስጥ በእውነቱ ከሆነ ከዛሬ አንድ ዓመት ገደማ ወዲህ ይህ የለውጥ አመራር ወደ ኢትዮጵያ አመራር ላይ ከመጣ በኋላ የታዩት ለውጦች ሊካዱ የሚችሉ አይመስለኝም። ኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ በጣም መሰረታዊ የሆነ በታሪካችን ምናልባት ለየት ያለ ነው በሚባል ደረጃ ከፍተኛ ለውጥ ታይቷል።

በተደጋጋሚ የሚገለጸው ያላግባብ የታሰሩ ሰዎች ከእስር ከመለቀቅ አንስቶ የፖለቲካ ሜዳው ለሁሉም ክፍት መደረጉና ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ተሳትፎ መብት ሁሉንም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዳይ ያገባናል፣ ይመለከተናል የሚሉ ተገለው የነበሩ ሰዎች ሁሉ በሚያቅፍ መንገድ በሩ ተከፍቷል።

በምንም አይነት ሁኔታ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ በተከፈተው የፖለቲካ ሂደት የተገለለ ሰው ወይም ቡድን አለ ብሎ ለማለት የሚቻል አይመስለኝም። ሰፊ ድንኳን ነው የተጣለው፤ ሰፊ በር ነው የተከፈተው፤ ስለዚህ በአገራችን ጉዳይ ላይ ያገባናል የሚሉ ሰዎች ሁሉ ሊሳተፉ የሚችሉበት እድል ተፈጥሯል ብዬ አምናለሁ።

በኢትዮጵያ የአዕምሮ ህሙማን ሰብዓዊ መብት እየተጣሰ ይሆን?

ይህ የተፈጠረው እድልም የሰብአዊ መብት አያያዝ ሁኔታን ትልቅ በሚባል ደረጃ አሻሽሎታል፤ ለውጦታል። ነገር ግን ይህ ማለት የሰብአዊ መብት ችግሮች በሙሉ ተፈትተዋል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር የለም ማለት አይደለም። ይልቁንም እጅግ ሰፊ፣ውስብስብ፣ ጥልቅ፣ የሆኑ የሰብአዊ መብት ችግሮችም፤ የፖለቲካ ቀውስም፣ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥም የምንገኝ መሆኑ ሊካድ አይችልም።

የተፈጠረው አዲስ የተሃድሶ ወይም የለውጥ ሥራ ግን እነዚህን ሁሉ ችግሮቻችንን በመተጋገዝና በመተባበር ከሠራን ልንለውጣቸውና ልናሻሽላቸው የሚያስችል እድል አለ ብዬ አምናለሁ። ኢትዮጵያ ውስጥ በታሪካችን ብዙ ጊዜ ዕድል ይፈጠራል፤ እድሎች ግን ሲጠፉ ተመልክተናል። ይህ እድል መጥፋት ያለበት አይመስለኝም።

ስለዚህ አሁን በተፈጠረው ዕድልና ምቹ ሁኔታ በመጠቀም አገራችንን ወደፊት ለማራመድ አብረን መሥራት አለብን በሚል እምነት ነው ይህንን ሹመት ተገቢ ነው ብዬ የተቀበልኩት።

ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መንግሥት የሚፈፅቸውን ጥሰቶች በማለባበስ ለመታት ይተቻል። ብዙ ቅሬታዎች ሲቀርብበት የነበረም ድርጅት ነው። እነሱ ክፍተቶች ተስተካክለዋል? ገምግመኸው ከሆነ በምንሁኔታስ መስተካከል ይችላሉ?

ዳንኤል በቀለእነዚህ ክፍተቶች አልተስተካከሉም። ገና ወደፊት የሚስተካከሉ እንጂ አሁን የተስተካከሉ አይደሉም። አሁን የተጀመረው ነገር እነዚህን መሰረታዊ የሆኑ የዲሞክራሲያዊ ተቋማት የሚባሉ እንደ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ምርጫ ቦርድ የመሳሰሉ የአገሪቱን የዳኝነት አካልን የመሳሰሉ ተቋማትን እውነተኛ፣ ገለልተኛ፣ ነፃ፣ ጠንካራና ውጤታማ ተቋም ለማድረግ የሚያስችል እድል ተፈጥሯል።

ይህንንም ለማድረግ የሚያስችሉት የመጀመሪያዎቹ እርምጃዎች መወሰድ ተጀምረዋል። የለውጡ አመራሮች የፖለቲካ ፈቃደኝነታቸውና የፖለቲካ ቁርጠኛነታቸው ለእነዚህ ተቋማት የሚያስፈልገውን አመራር ለመፍጠር፤ ለሥራው ይሆናሉ ብለው የሚያስቧቸውን ግለሰቦች መምረጥ መጀመር መቻላቸው በእውነቱ አንዱ ትልቅ እርምጃ ነው ብዬ አምናለሁ።

ስለዚህ ተቋማቱን ተአማኒ፣ ተቀባይነት ያላቸውና ውጤታማ ለማድረግ ገና የመጀመሪያው እርምጃ ወይም የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ እንጂ፤ ሥራው ተጀመረ እንጂ ፈፅሞ አልተጠናቀቀም። ግን የተፈጠረው ዕድል ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ስለሆነ እጅግ በጣም ተስፋ ሰጪ ነው ብዬ አምናለሁ።

በቅርቡም ለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ላይ መዋቅራዊ ለውጥ እንዲደረግ ጠይቋል። ኮሚሽኑ ምን አይነት መዋቅራዊ ለውጥ ነው ማምጣት ያለበት? መስተካከል ካለበት በምን መንገድ ነው መስተካከል ያለበት?

ዳንኤል በቀለአምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣውን ሪፖርት አይቸዋለሁ። በእኔም አስተሳሰብ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን መዋቅራዊም ሆነ አሠራራዊ የለውጥ ማሻሻያ ሊያደርግ ይገባዋል የሚል እምነት አለኝ። ነገር ግን ወደ እንደዚህ አይነት የተቋም ማሻሻል፣ ማጠናከር፣ ማደስና የአሠራር ለውጥ ጉዳዮች ውስጥ ከመግባታችን በፊት ትንሽ በጥሞና ማድመጥ፣ ማጥናትና መጠየቅ ያስፈልጋል።

የአለማየሁ ተፈራ ፖለቲካዊ ካርቱኖች

በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ጥሩ የሚባሉ ልምዶችን መመልከትና መፈተሽ ያስፈልጋል። ስለዚህ በአሁኑ ሰዓት ሊደረግ የሚገባውን መዋቅራዊ ለውጥ ይሄ ነው ይሄ ብዬ ለመናገር ዝግጁ አይደለሁም። ይህ ጉዳይ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት መንግሥታዊ የሆኑና መንግሥታዊ ያልሆኑ፣ የልማት አጋሮችና ህብረተሰቡንም በአጠቃላይ ሁሉንም በሚያካትት መልኩ ችግሮቹ ምንድን ናቸው? እድሎቹስ? የሚለውን ማየት ያስፈልጋል። በዚያ ላይ ተመስርቶ የመዋቅር ለውጥና የአሠራር ለውጥ ለማድረግ እንችላለን።

ምንም እንኳን ብዙ ማሻሻያዎች ቢደረጉም ገሪ ውስጥ ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ በብሔራቸው የሚፈናቀሉበት፣ የመንቀሳቀስ መብት የተገደበበት ሆኗልና እንው እንደ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንስ ተግዳሮቶች ብለህ የምታስባቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው?

ዳንኤል በቀለችግሮቹ ብዙ ናቸው። የተወሰነውን ለመጥቀስ ያህል ኢትዮጵያ ውስጥ ጠንካራ ተቋማት አለመኖራቸው በጣም ትልቅ ችግር ነው፤ ምክንያቱም በወንጀል ፍትህ አስተዳደር፣ በዳኝነት ሥራ፣ በፖሊስና በፀጥታ ኃይሎች ብዙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሊፈፀሙ የሚችሉበት ሁኔታ አለ።

ያለው የፖለቲካ ሂደት ብሔርን መሰረት ያደረገ፣ የተካረረ የፖለቲካ ውጥረት መኖሩ ያስከተለው ግጭት፣ የፈጠረው የብዙ ሕዝብ መፈናቀል፣ መሞትና ከኑሮው መስተጓጎል ኢትዮጵያ ውስጥ ከተፈጠረው ለውጥ ጋር ተያይዞ በርካታ የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ የደህንነት ክፍተት መፈጠሩ ማለትም ሕግና ሥርዓትን ማስከበርን ጨምሮ ማለት ነው። አንዳንድ አካባቢዎች ሕግና ሥርዓትን ማስከበሪያ ተቋማት በመዳከማቸው ወይም በመጥፋታቸው የተነሳ የደህንነት ክፍተት ተፈጥሯል።

የአገራችን የፖለቲካ ቀውስ ገና መፍትሔ አለማግኘቱ፤ እነዚህ ሁሉ ደግሞ በሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ላይ ተፅእኖ ፈጣሪዎች ናቸው። ይሄ አሳሳቢ ጉዳይ ነው። አሁን ካለንበት የፖለቲካ አንፃርም እነዚህን ሁሉ ነገሮች ከግንዛቤ ውስጥ ከቶ ሰብአዊ መብት አያያዝን ለማሻሻል እንዴት አድርጎ ይቻላል የሚለው ከባድ ነው።

በአጠቃላይ ከፖለቲካችን፣ ከኢኮኖሚያችንና ከማኅበራዊ ሁኔታችን ጠባይ የተነሳ የሚፈጠሩት ችግሮች በሰብአዊ መብት ሁኔታም ላይ ተፅእኖ ፈጣሪዎች ናቸው። ይህ ትልቅ እንቅፋት ወይም መሰናክል ይሆናል ብዬ አስባለሁ።

ብዙዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደ ስልጣን ሲመጡ ባደረጓቸው ተግባራት እንደ እስረኞች መፍታት የመሳሰሉት ያመሰግኗቸዋል። ከመት በኋላ በብዙዎች ዘንድ አፋኝ በተባለው በፀረ ሽብር ግ ሰዎች እየተጠየቁ ነው፤ እንዲሁም በእስክንድር ነጋ የሚመራው ራሱን የአዲስ አበባባላደራ ምክር ቤት ብሎ የሚጠራው አካልም መንግሥት በነፃ እንዳልንቀሳቀስ አድርጎኛል ይላል። መንግሥት ላይ የሚሰሙ ትችቶችን እንዴት ታያቸዋለህ?

ዳንኤል በቀለሙሉ በሙሉ ያጠናሁትና ያልመረመርኩት ቢሆንም በተወሰነ መንገድ የተነሱትን ሃሶቦች በሚመለከት አድምጫለሁ እና እነዚህ አሳሳቢ ጉዳዮች ናቸው። በጣም በጥንቃቄ መጣራት የሚያስፈልገው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ለምሳሌ የፀረ ሽብር ሕጉ ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ጊዜ ከፍተኛ ትችት የቀረበበትና አሁንም የለውጥ እርምጃ መወሰድ ከተጀመረበት በኋላ ሊሻሻሉ ይገባል ተብለው ከታሰቡት ሕጎች ውስጥ አንዱ እሱ ነው።

የማሻሻል ሥራም ተጀምሮ የተወሰነ ደረጃ የደረሰ መሆኑ ይታወቃል። እና ያንን ሕግ መሰረት ተደርጎ ሊቀርብ የሚችል ወይም የሚገባ ክስ ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖራል ብዬ አልገምትም፤ መኖርም የለበትም።

ተፈፀመ የተባለ ወንጀል ካለ ሌሎች አግባብነት ባላቸው የወንጀል ሕግ ሊጣራ ወይም ሊመረመር ይገባል። እንጂ እጅግ የተወቀሰ፣ የተነቀፈና ሊሻሻልም እንደሚገባው ታምኖ የመሻሻል እርምጃ የተጀመረበት ሕግ በአሁኗ ኢትዮጵያ ውስጥ የወንጀል ክስ ለማቅረብ መሰረት ይሆናል ብዬ አልገምትም። እንደዚህም አይነት እርምጃ መወሰድ ተጀምሮ ከሆነ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም። ዝርዝሩን በደንብ ባላውቀውም ትክክል ነው ብዬ አላምንም።

ወደ ትችቶቹ ስመጣ አሁን ባለው የኢትዮጵያ አስተዳደር የተቃውሞ አስተሳሰብ ሊኖር እንደሚችል እገምታለሁ። ያም ሁኔታ በራሱ መጥፎ አይደለም። ሁሉም ሰው አንድ አይነት አስተሳሰብ ይኖረዋል ተብሎ መጠበቅ የለበትም፤ ሊሆንም አይችልም።

ስለዚህ በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ እስከተገለፀ ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በሚመሩት መንግሥት ላይ ተቃውሞ ቢነሳ፣ ትችት ቢቀርብና የተለየ ሃሳብ ቢስተናገድ በራሱ እንደ ችግር ወይም እንደ መጥፎ ነገር የሚታይ አይደለም። ይልቁንም ይበረታታል፤ የተለያዩ ሃሳብ መኖራቸው መልካም ነው።

በጣም አበክሬ የምናገረው ግን የተፈጠረው እድል በጣም ትልቅ ነው። ይህንን እድል እንዳናበላሽ በጥበብና በማስተዋል መስራት ያለብን ይመስለኛል። የአገራችን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በመክተት እንዴት ነው በመተጋገዝና በመተባበር ወደፊት መሄድ የምንችለው የሚለውን ማሰብ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው።

እስሮችም ሆነ ሌሎች መንግሥት የሚወስዳቸው እርምጃዎች ከብሔር ጋር ይተሳሰራሉ። እንደ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ያለው ሪፖርት በሚያወጣበትም ጊዜ አንደኛው ብሔር ሊያኮርፍ ይችላል። ሁሉም ነገር በብሔር መነጽር ስለሚታይ ማለት ነው። እንደ መፍትሔ ወይም እንደ አቅጣጫየምታስቀምጣቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው?

ዳንኤል በቀለበጣም ሰፊና ከባድ ጥያቄ ነው። በአጭሩ በቀላሉ ሊመለስ የሚችል ነገርም አይመስለኝም። ለብቻዬም የምመልሰው ነገር አይደለም። በርካታ ባለድርሻ አካላት በጋራ በመተባበር ሊሠሩበት የሚገባም ነገር ይመስለኛል።

ነገር ግን እንደው ምናልባት አግባብነት ያለው አንድ ነጥብ ለማንሳት የምፈልገው ቢኖር፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ከብሔር ጋር የተያያዘ የተወሳሰበ የፖለቲካ ጥያቄ ቢኖርም፤ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ሊስማሙበት የሚገባው ወይም ሊያስማማቸው ይገባል ብዬ ተስፋ የማደርገው አንድ ነገር ግን የሰብአዊ መብት ጉዳይ ከብሔር ጋር የተያያዘ አይደለም።

የማንኛውም የሰው ልጆች ሁሉ መብት ነው። ስለዚህ የትኛውም አይነት በብሔር ፖለቲካ የተደራጁ ወይም በሌላ አይነት መልክ ፖለቲካ የተደራጁ ቡድኖች በሙሉ በያሉበት፣ በየሚሠሩበት አካባቢ ሊቆሙለት የሚገባ አንድ መርህ ነው ብዬ የማስበው ነገር የሰዎች መብት መከበር ነው።

የሰዎች መብት መከበር ደግሞ ማለት የአንድ አካባቢ ተወላጆች የሚባሉ ሰዎች መብት ብቻ ሳይሆን የማንኛው ሰው መብት ማለት ነው። በአንድ ክልል የሚኖሩ ሰዎች የሌላውን ሰው መብትም ካላከበሩ እነዚያ ሰዎች እነሱም በሌላ አካባቢ የሚከበር መብት አይኖራቸውም ማለት ነው።

ስለዚህ ሁሉም የፖለቲካ ቡድኖች ወይም አደረጃጀቶች እነዚህ ከዚህ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ አስተሳሰቦች በሙሉ ሊስማሙበት፣ ሊቆሙበት፣ ሊታገሉለት የሚገባ ነገር የሰብአዊ መብት መከበር ነው። የሰብአዊ መብት ለሁሉም ነው። ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም የሰው ልጆች ሊከበር የሚገባው ነገር ነው። እና ትንሽ ተስፋ የማደርገው ነገር ብዙ የማስተማር፣ የማሳወቅ ሥራ ሊጠይቅ ይችላል።

ነገር ግን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ቡድኖች፣ የኢትዮጵያ ሕዝብና ህብረተሰብ በሙሉ በሰብአዊ መብት ጉዳይ ላይ ሊስማማ ይችላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። በጣም ከባድ ችግር ወይም እንቅፋት እንዳለውም እገነዘባለሁ።