"የለውጥ አመራሩን ሳይረፍድ ከጥፋት መመለስ ይቻላል" እስክንድር ነጋ

እስክንድር ነጋ

በጋዜጠኛና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ የሚመራው የባላደራ ምክር ቤት ዛሬ ሐምሌ 3፣ 2011 ዓ. ም በምክር ቤቱ ቢሮ የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ተቋርጧል።

መግለጫው በዋነኛነት ያተኮረው ከሰሞኑ የታሠሩበት አባላቱን ኤልያስ ገብሩና ስንታየሁ ቸኮል ላይ ሲሆን፤ ከአንድ ዓመት በፊት እስረኞች ተፈተው የነበረው ሁኔታ ወደ ኋላ እንደተቀለበሰም እስክንድር ተናግሯል።

"ከጄ/ል አሳምነው ጋ በምንም ጉዳይ ያወራሁበት አጋጣሚ የለም" እስክንድር ነጋ

"ታከለ ኡማ አዲስ አበባን መምራት የለባቸውም" እስክንድር ነጋ

"እስር ቤቶቻችን የህሊና እስረኞች አልባ የነበሩ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን የህሊና እስረኞች ያሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፤ እነዚህም እስረኞች ኢ- ሰብአዊ በሆነ ሁኔታ ነው የተያዙት፤ ይህንንም መግለጫ ስንጠራ ያሉበትን ሁኔታ ለማሳወቅ እንዲሁም ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ለመጠየቅ ነው" ብሏል።

መግለጫው ተጀምሮ ለምን ያህል ደቂቃ ተሰጥቶ እንደነበር በትክክል እንደማያውቅ ለቢቢሲ ገልጾ፤ መግለጫው ተነቦ ጋዜጠኞች ሁለት ጥያቄ ጠይቀው መልስ መስጠት ሲጀምሩ እንደተቋረጠ ተናግሯል።

መግለጫው ለመቋረጥ የበቃው "ጥያቄ አለን" በሚሉ ሰዎች በተነሳ ረብሻ ሲሆን፤ በባላደራው ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ላይ የተገኙ በቁጥር 10 የሚሆኑ ወጣቶች ደምፃቸውን ከፍ አድርገው ''ባንዲራችን ይህ ነው'' በማለት ባለ ኮከቡን የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ከፍ አድርገው ሲያሳዩ ነበር።

''አገር መገንባት ነው የምንፈልገው አንጂ ማፍረስ አይደለም''፣ ''አይሳካልህም''፣ ''ምክር ቤቱ ኦሮሞን ያገለለ ነው''፣ ''ታከለ [የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ] መጤ አይደለም''፣ ''አዲስ አበባ የሁሉም ናት'' የሚሉ መፈክሮችን ደጋግመው ሲያሰሙ ነበር።

የነበረውን ሁኔታ አረጋግቶ መቀጠል አይቻልም ነበር ወይ? በሚል ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ "ማረጋጋት አይቻልም" የሚል ምላሽ የሰጠው እስክንድር፤ የታቀደበት እንደነበርና የተደራጀም እንደነበር ገልጿል።

"ሰንደቅ አላማዎቹ በደንብ ተዘጋጅተው፣ ጥቃት የሚያደርሱበት ስውር መሣሪያዎች ይዘው፤ የሚናገሩት ነገር በስሜት ሳይሆን በደንብ የተጠና እንደነበር የሚያመላክቱ ነገሮች አግኝተናል" ብሏል።

ነገሮችን ለማረጋጋትና ሁኔታው ወደ ሌላ ከማምራቱም በፊት ቶሎ ከአዳራሹ እንደወጣም ይናገራል።

“የመከላከያው በአደባባይ ሚዲዎችን እከሳለሁ ማለት አስፈሪ ነው” ዶ/ር አብዲሳ ዘርዓይ

ለባለስልጣናቱ ግድያ አዴፓ ራሱን ተጠያቂ እንዲያደርግ ህወሐት ጠየቀ

"የምናዝነው ከመልዕክቱ ይልቅ የተፈጠረው ነገር በመጉላቱ ነው፤ የተነሳንበትን ዋነኛ አላማ ውጦብናል፤ በዚህም በጣም እናዝናለን" ብሏል።

መግለጫውን ከመስጠታቸው ከአንድ ቀን በፊት "የተለመዱ" የሚላቸው ማስፈራሪያዎችና ዛቻዎች እንደነበሩ የሚናገረው እስክንድር በስልክ፣ በቪዲዮም ማስፈራሪያ እንደደረሰው ገልጿል።

ጥዋት ላይም ቢሮ ሊገባ በነበረበት ወቅት 'ሲቪል የለበሰ' አንድ ፖሊስ ቢሮ ላይ ጠብቆ እንዳይገባ ከልክሎት እንደገፈተረው ለቢቢሲ ተናግሯል።

ከዚህም በተጨማሪ ጋዜጠኞች እንዳይገቡ እንደተከለከሉና የምክር ቤቱ አባል ጠበቃ ሔኖክ አክሊሉና ሌላ አንድ አባል በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው እንደነበር ግን ብዙም ሳይቆይ እንደተለቀቁ ገልጿል።

በተደጋጋሚ የባልደራስ ምክር ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ሲዘጋጅ የተሰረዘበትን እስክንድር የፖለቲካ ምህዳሩ ስለመጥበቡ አንድ "ቁንፅል ማሳያ" ነው ይላል።

ከዚህ በላይ ግን ሰሞኑን አገሪቱ ውስጥ ከተከሰቱ ችግሮች ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በፀረ-ሽብር ሕግ መጠየቃቸው "ግዙፋ ማሳያ" እንደሆነም ይናገራል።

"አገራችን ወደ ኋላ እየተጓዘች ስለ መሆኗ፤ የተገባው ዲሞክራሲ፣ ይመጣል ተብሎ የተገባው ቃል ለመታጠፉ ምንም ማስረጃ የለም፤ ያ ትልቅ ማስረጃ ነው" ብሏል።

አክሎም "በአጠቃላይ አገራችን ጥሩ አቅጣጫ ላይ አይደለም። ነገር ግን አሁንም መናገር የምፈልገው ተስፋ የሚያስቆርጥ አይደለም፤ ምንም እንኳን መብታችን እየተደፈጠጠ ቢሆንም መብታችን እየተነፈገ ቢሆንም፤ አዲሱ የለውጥ አመራር እየከጀለ ነው፤ በጥፋት መንገዱ ላይ አንድ እርምጃ ነው የወሰደው፤ ብዙ አልተጓዘም። ከዛ ሳይረፍድ መመለስ ይቻላል። ነገሮች ሳይባባሱ የማንመልሳቸው ደረጃ ሳንደርስ እንዲመለስ ነው ጥሪ ማስተላለፍ የምፈልገው" ብሏል።

አገሪቷ እስካሁን የነበረችበት ሁኔታ "መስቀለኛ መንገድ" ነበር የሚለው እስክንድር፤ አሁን ደግሞ "ወደ ጥፋቱ የመሄድ አዝማሚያ " እንዳለ ይገልፃል። ከወዲሁ "መንግሥት አካሄዱን ሊያስተካክል እንደሚገባ" ይናገራል።

በተለይም አባላቶቹ በፀረ ሽብር ሕጉ እየተጠየቁ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞም " ከዚህ በፊት ጦርነት እናውጃለን ተብሎ ነበር፤ ይሄው በዴሞክራሲ ሽግግሩ ላይ የታወጀ ጦርነት ነው፤ ከግድያ አንድ ደረጃ ዝቅ ያለው በሽብር መክሰስ ነው። ይህ የሚያዋጣ መንገድ አይደለም። የለውጡ አመራር ከዚህ የጥፋት መንገድ ሊስተካከል ይገባዋል። ለአገር፣ ለኢህአዴግም ሆነ ለራሳቸው የሚያዋጣው የዲሞክራሲ መንገድ ነው" ብሏል።