አብን አቶ ክርስቲያንን ጨምሮ ከአምስት መቶ በላይ አባላቶቹ እንደታሰሩ ገለፀ

አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (የአብን) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ Image copyright Christian tadele Facebook page

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለ በዛሬው ዕለት መታሰራቸው ተገልጿል።

በቁጥጥር ስር የዋሉት ዛሬ ረፋድ ላይ ስለታሰሩ የአብን አባላት ሁኔታና አያያዝ ሁኔታ ጋር ለመወያየት ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባመሩበት ወቅት እንደሆነ የአብን ሊቀ መንበር ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በወቅቱ ቦታው ላይ የነበሩት ዶ/ር ደሳለኝ እንዲሚያስረዱት ውይይታቸውን ጨርሰው በር ላይ እንደደረሱ የደህንነት ሰዎች ነን የሚሉ ግለሰቦች ለምርመራ እንደሚፈለጉ ገልፀው አቶ ክርስቲያን መውጣት እንደማይችሉ ነግረዋቸዋል።

አብን ከ100 በላይ አባላቶቼ ታስረዋል አለ

"ብ/ጄኔራል አሳምነውን ቀድቻቸዋለሁ" ጋዜጠኛ ፋሲካ ታደሰ

ለምንድን ነው ብለው በጠየቁበትም ወቅት ያገኙት ምላሽ " አቶ ክርስቲያን የተጠረጠሩበት ወንጀል እንዳለና እሱን መግለፅ እንደማይችሉ" እንደገለፁላቸው ዶ/ር ደሳለኝ ይናገራሉ።

አቶ ክርስቲያን በቁጥጥር ሲውሉ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም። ከጥቂት ቀናት በፊትም በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ውስጥ ሰከላ በሚባል ወረዳ የታሰሩ አመራር አባላትን ለመጎብኘት በሄዱበት በቁጥጥር በቁጥጥር ስር ውለው ከአዴፓ አመራሮች ጋር በተደረገ ንግግር በነገታው እንደተፈቱ ይናገራሉ።

ከአቶ ክርስቲያን በተጨማሪ በተለያዩ የአዲስ አበባ ክፍሎች ሌሎች አዳዲስ እስሮች እንዳሉም የሚናገሩት ዶ/ር ደሳለኝ ቁጥራቸውንም ከ20-30 ሊደርስ እንደሚችልም ይገምታሉ።

"ይሄ እስርም በተለያዩ የአዲስ አበባ ከተማ መዋቅር ውስጥ የሚሰሩ የመንግሥት ሰራተኞች ላይ ያነጣጠረ እንደሆነና፤ የአማራን ህዝብ በገፍ ማሰር ማቆም አለበት ብለው የጠየቁ አንዳንዶችም አሉበት" በማለት ዶ/ር ደሳለኝ ይናገራሉ።

"የለውጥ አመራሩን ሳይረፍድ ከጥፋት መመለስ ይቻላል" እስክንድር ነጋ

በአጠቃላይ በኃገሪቱ ከአምስት መቶ በላይ አባላቶቻቸው እንደታሰሩባቸው የሚገልፁት ዶ/ር ደሳለኝ በተለይም በአዲስ አበባ፣ ኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ላይም ያተኮረ እንደሆነ ይናገራል።

"አንዳንድ ቦታዎች ላይም አብን ህገወጥ ድርጅት ነውና በገንዘብ ረድታችኋል ተብለው 56 የሚደርሱ ሰዎች በዋስ እንደተፈቱም ይናገራል።

እስረኞቹን ለማየት እንደተቸገሩ የሚናገሩት ዶ/ር ደሳለኝ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቢሮም ጋር በነበራቸው ውይይትም እንዳነሱትና ምርመራው በአስቸኳይ እንዲጠናቀቅና ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የሚሉ ሃሳቦችንም ማንሳታቸውን ይናገራሉ።

እስካሁን በመደበኛ ሁኔታ ክስ የተመሰረተባቸው የሌሉ ሲሆን፤ ፍርድ ቤት የቀረቡና ቀጠሮ የተጠየቀባቸው ወደ 13 የሚደርሱ አባላት ሲሆኑ ወደ አራት አምስት የሚሆኑት ደግሞ ከሰኔ 15 ግድያ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረዋል በሚል እንደሆነም ዶ/ር ደሳለኝ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

"እስሩ ህገወጥ ነው። አብንን ለማዳከምና በዚህ ተደናግጠን ከጀመርነው ትግል እንድናፈገፍግ ታስቦ የሚደረግ ይመስለኛል። እንደዚህ አይነት የፖለቲካ እስሮች አብንን ያጠናክሩታል እንጂ የሚያስፈሩን ወይም ወደ ኋላ እንድንሸሽ የሚያደርጉን አይደሉም"