"የመጀመሪያውን ድራማ አንተ፤ ሁለተኛውን እኔ እፅፈዋለሁ" ኤርሚያስ አመልጋ

ኤርሚያስ አመልጋ Image copyright Anteneh Yigzaw

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ 'የማይሰበረው' የተሰኘና በአቶ ኤርሚያስ አመልጋ ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጥን መጽሐፍ ለንባብ በቅቷል። በአቶ ኤርሚያስ ከአገር መሰደድና በተደጋጋሚ መታሰር በመቋረጡ የመጽሐፉ ዝግጅት ሰባት ዓመታትን ፈጅቷል። ስለ መጽሐፉ ዝግጅትና በመጨረሻ እንዴት ለህትመት እንደበቃ ጸሐፊውን አቶ አንተነህ ይግዛውን አነጋግረነዋል።

መፅሃፉን የማዘጋጀት ሃሳብ ከማን ነው የመጣው መጀመሪያ?

አቶ አንተነህ፡ ሃሳቡ የመጣው ከአቶ ኤርሚያስ ነው። የቀድሞ የሥራ ባልደረባዬ በነበሩ ሰው የሕይወት ታሪካቸውን ማፃፍ እንደሚፈልጉ ነገሩኝ። ይህ የሆነው 2003 ዓ. ም መጨረሻ ወይም 2004 ዓ. ም መጀመሪያ ላይ ይመስለኛል። ከዚያ የመረጃ ስብሰባ፣ መረጃ ማደራጀት እና ቃለ መጠይቅ የሚደረግላቸው በርካታ ሰዎች ነበሩ፤ እንደገና ድምፁን ገልብጦ ወደ መጽሐፍ ስክሪፕት የመቀየር ሥራዎች ተሠሩ። 2005 ዓ. ም ወይም 2006 ዓ. ም አካባቢ ተጠናቀቀ። ግን ሥራው ወዲያው ተቋረጠ።

መጽሐፍ ቅዱስን መጀመሪያ ወደ ኦሮምኛ የተረጎሙት ኦኒስሞስ ነሲብ ማን ናቸው?

ለምን ነበር የተቋረጠው?

አቶ አንተነህ፡ የመጀመሪያውን ረቂቅ እያዘጋጀን እያለ አቶ ኤርሚያስ ከአክሰስ ሪል እስቴት ችግር ጋር በተያያዘ አገር ጥለው ወጡ። አቶ ኤርሚያስ የአክሰስ ሪል እስቴትን ችግር እፈታለሁ ብሎ ከመንግሥት ጋር በተደረገ ድርድር ከሁለት ዓመት የዱባይና አሜሪካ ቆይታ ሲመለስ መጽሐፉን ለምን አንቀጥለውም የሚል ሃሳብ አነሳልኝና እንደገና ቀጠልን። ምክንያቱም የአክሰስን ቀውስ ያላካተተ መጽሐፍ የኤርምያስ ታሪክ አይሆንምና፤ በቆይታህ ምን ስታደርግ ነበር? እንዴትስ መጣህ? እና ከመጣህስ ምን አደረግክ? የሚሉት ነገሮች ላይ እንደገና ቃለ መጠይቅ አድርጎ ወደ መጽሐፍ መቀየር ያስፈልግ ነበር። ያን ጨርሰን ወደ መጨረሻ የዲዛይን ሥራ ልንገባ ስንል ደግሞ ከዚሁ ከአክሰስ ችግር ጋር በተያያዘ አቶ ኤርሚያስ ማዕከላዊ ታሰረ። ለሁለተኛ ጊዜ መጽሐፉ ተቋረጠ።

አልቆ ከነበረ አቶ ኤርሚያስ እስር ቤት ቢገባም መጽሐፉን ማውጣት አይቻልም ነበር?

አቶ አንተነህ፡ እሱን ማግኘት አልችልም ነበር ምክንያቱም ከአባቱ፣ ባለቤቱና እህቱ ውጭ ማንንም ማግኘት አልተፈቀደለትም ነበር። በቃ ይህንን ታሪክ እንድንጀምር እንጂ እንድንቀጥል አልተፈቀደልንም አልኩና ተውኩት።

ከዚያ እንዴት እንደገና ራው ተጀመረ?

አቶ አንተነህ፡ እንደገና ሲፈታ አቶ ኤርሚያስ ደወለልኝ።

ደውሎ ምን ነበር ያለህ?

አቶ አንተነህ፡ [ይሄን መጽሐፍ እንደገና መቀጠል አለብን ታሪኩ እየጦፈ ወደ ክላይማክሱ እየሄደ ነው] አለኝ። እስር ቤት ከነማን ጋር እንደነበር፣ ምን ያደርግ እንደነበር? አፈታቱስ እንዴት ነበር? የሚለውን ደግሞ አዲስ ምዕራፍ ጨምረን ሥራ ጀመርን። አሁንም ሥራችንን እያጠናቀቅን እያለ ከኢምፔሪያል ሆቴል ሽያጭ ጋር በተያያዘ አቶ ኤርሚያስ እንደገና ታሰረ። ነገሩ ለኔ በጣም አስደንጋጭ ነበር። 2004 ዓ. ም ገደማ የተጀመረ መጽሐፍ ለሦስተኛ ጊዜ መቋረጡ በመሆኑ ተስፋ ቆረጥኩ።

"ኢህአዴግ ነፃ ገበያም፣ ነፃ ፖለቲካም አላካሄደም" ፀደቀ ይሁኔ (ኢንጂነር )

በመጨረሻ መጽሐፉ አሁን እንዴት ለህትመት በቃ?

አቶ አንተነህ፡ አንድ ቀን ኤርሚያስ ከሚገኝበት ቂሊንጦ እስር ቤት አስጠራኝ። [እንግዲህ አንተ ይሄን መጽሐፍ እዚህ አድርሰኸዋል] አለኝ። እኔ የፃፍኩት ከማዕከላዊ እስከተፈታበት ምሽት ድረስ ያለውን ነበር። [ከዚህ በኋላ ቂሊንጦ ከገባሁ በኋላ ያለውን እኔ ራሴ እፅፈዋለሁ። አንተ የፃፍከው ይታተም] አለኝ። በዘህ ተስማምተን መጽሐፉ ወደ ህትመት ገባ።

Image copyright Anteneh Yigzaw

አሁን አቶ ኤርሚያስ የቂልንጦ ቆይታውን እየፃፈ ነው?

አቶ አንተነህ፡ አሁን ቂሊንጦ ስለተገኘበት የሜቴክ/የኢምፔሪያል ሆቴል ሽያጭ ክስ ጉዳይ እዚያው ቂሊንጦ ሆኖ የሠራቸው ወደ አስር የሚሆኑ የጥናት ፅሁፎች 'ኢትዮጵያ አት ኤ ቲፒንግ ፖይንት' [Ethiopia at a Tipping Point] በሚል ርዕስ ታትመው አማዞን ላይ ወጥቷል። ከሁለት ከሦስት ሳምንት በኋላ ደግሞ ኢትዮጵያ ይገባል። ይኸው ፅሁፍ እንደገና በአማርኛ 'ኢትዮጵያ በመስቀለኛ መንገድ ላይ' በሚል ርዕስ ተተርጉሞ ለገበያ ይቀርባል።

አሁን ቂሊንጦ የሚገኘው አቶ ኤርሚያስ ለንባብ የበቃው 'የማይሰበረው'ን ከመታተሙ በፊት አንብቦታል?

አቶ አንተነህ፡ እስር ቤት እየገባ ኤዲት ተደርጓል፤ አምስት ጊዜ አይቶታል። ጠበቃውን ጨምሮ ኤርሚያስን እንዲያዩ ከተፈቀደላቸው ሰዎች መካከል አንዱ እኔ ስለሆንኩኝ እኔም እየገባሁ እያሳየሁት እያነበበው እየተስተካከለ ነው የሠራነው።

ጽሐፉ ለምን አሁን ታተመ? አቶ ኤርሚያስ እስር ላይ ስለሆነ ተፅእኖ ለመፍጠር ነው?

አቶ አንተነህ፡ መጽሐፉ ሦስት ጊዜ ተቋርጧል። በዚህ ሳይሆን በሌላ ርዕስ ዲዛይን ተደርጎም ነበር አንድ ጊዜ። ግን በተደጋጋሚ መታሰር መፈታቱና አጠቃላይ ርዕሱንም የታሪኩንም ትኩረት እንዳስተካክል የሚያስገድዱ ሁኔታዎች መጡብኝ። ከአራት ከአምስት ዓመታት በፊት ሊታተም የነበረ መጽሐፍ ነው። አሁን ምንም አይነት ተፅእኖ ለመፍጠር አይደለም። በነገራችን ላይ አሁንም ላሳትመው አልፈለግኩም ነበር።

ታዲያ እንዴት ታተመ?

አቶ አንተነህ፡ በኤርሚያስ ግፊት። [አሁን መታተም አለበት ከዚህ በኋላ የምጠብቀው ጊዜ የለኝም። የመጀመሪያውን ክፍል ድራማ አንተ ፃፈው ሁለተኛውን እኔ እፅፈዋለሁ] ስላለኝ። በመጽሐፉ ድህረ ታሪክ ገፅ ላይ እኔ ያሰፈርኩት ነገር የነበረውን ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

የመጽሐፉ አሳታሚ ማን ነው?

አቶ አንተነህ፡ ኤርሚያስ አመልጋ

ስንት ኮፒ ታተመ? ምን ያህል ብርስ ፈጀ?

አቶ አንተነህ፡ አስር ሺህ ኮፒ ነው የታተመው፤ ግን ስለ ወጪ እና ገቢ አሁን መናገር ይቸግረኛል።

ዕድሜ ጠገቧ የጥድ መፃሕፍት ቤት መደብር ትውስታ

ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ብዙዎች 'የማይሰበረው' እያሉ እየፃፉ መጽሐፉን ለማስተዋወቅ የተሞከረበት መንገድ ለየት ያለ ነበር። የማን ሃሳብ ነው?

አቶ አንተነህ፡ የኔ ሀሳብ አይደለም። ከዚህ በፊት በአንዲት ደራሲ ጓደኛዬ ሃሳብ የአዳም ረታን 'መረቅ' በዚህ መልኩ ለማስተዋወቅ ተሞክሯል። ለአዳም ረታ ሥራዎች የተለየ ቦታ በምንሰጥ ሰዎችና አድናቂዎቹ። እና ከዚያ ልምድ በመነሳት የተደረገ ነው።

ፌስክ ገፅ ላይ እንዳሰፈርከው በአጠቃላይ መጽሐፉ ሰባት አመት ፈጅቶብሃል?

Image copyright Antenh Yigzaw

አቶ አንተነህ፡ አዎ ሰባት አመት ገደማ፤ በተደጋጋሚ በመቋረጡ። ይህን መጽሐፍ በማዘጋጀት ሂደት እንደ ፀሃፊ ለኔ ትልቁ ፈተና ከኤርሚያስ የሕይወት ፍጥነት ጋር እኩል መራመድ ነበር። የሱ ሕይወት ሁሌም በአዳዲስ ስኬትና ውድቀት የተሞላ ስለሆነ፤ መሰደድ መታሰር ነው። ሠራሁት ብለሽ ስጨርሽ ሌላ ታሪክ ጨምሮ ይጠብቅሻል። ለዚህ እንጂ የመፃፍ ጉዳይ ጊዜ የሚወስድ ሆኖ አይደለም።

ተያያዥ ርዕሶች