በደቡብ አፍሪካ ኬፕ ታውን እየጨመረ የመጣውን ውንብድና ለመቆጣጠር ጦር ተሰማራ

የደቡብ አፍሪካ ጦር ኃይል አባላት Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ የደቡብ አፍሪካ ጦር ኃይል አባላት

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በወደብ ከተማዋ ኬፕ ታውን እየጨመረ የመጣውን የወሮበላ ቡድን እኩይ ድርጊቶችን ለመቆጣጠር የሃገሪቱ ጦር ወደ ከተማዋ አሰማራ።

የፖሊስ ሚንስትር የሆኑት ብሄኪ ኬሌ የሃገሪቱ ጦር ከፖሊስ ጋር በመጣመር ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ እና አደንዛዥ እጾችን ያድናል ብለዋል።

ከሳምንት በፊት በአንድ ቅዳሜ እና እሁድ ብቻ በተደራጁ አደገኛ ቦዘኔዎች 13 ሰዎች በኬፕ ታውን ተገድለዋል።

የጋዜጠኛዋ መገደል ለምን የዓለም መነጋገሪያ ሆነ?

በኬፕ ታውን የተደራጁ አደጋኛ ቦዘኔዎች የሚፈጽሙት የወንጀል ድርጊቶች አስርት ዓመታትን ያስቆጠረ ነው።

ሰሞኑን ደግሞ በአደገኛ ቡድኖች የሚፈጸሙት ጥቃቶች እጅጉን ጨምረዋል። ለዚህም እንደምክንያትነት የተቀመጠው በቡድኖች መካከል በተፈጠረ ግጭት እና የአጸፋ እርምጃዎች ናቸው።

በአሁኑ ወቅት በከተማዋ የተለያዩ ስፍራዎች በርካታ የፖሊስ እና የሃገሪቱ መከላከያ ጦር አባላት ተሰማርተዋል።

የፖሊስ ሚንስትሩ ይህ መሰል ''ያልተለመደ'' ውሳኔ ላይ ለመድረስ መንግሥት የተገደደው የህዝቡን ደኅንንት የማረጋጋጥ ኃላፊነት ስላለበት ነው ብለዋል።

''ቤት ለቤት እንሄዳለን። ሕገ-ወጥ የጦር መሰሪያዎችን እንሰበስባለን፣ የሚፈለጉ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ሥር እናውላለን'' በማለት የፖሊስ ሚንስትሩ ብሄኪ ኬሌ ተናግረዋል።

Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ኬፕ ታውን ድህነት እና ሥራ አጥነት የተንሰራፋባቸው፣ እንዲሁም የተደራጁ አደጋኛ ቦዘኔዎች መኖሪያ በሆኑ ትናንሽ ከተሞች ተከባ ትገኛለች።

በከተማዋ የተሰማሩት የጦር ኃይሉ አባላት ትዕዛዝ የሚቀበሉት ከፖሊስ እንደሆነ የሚናገሩት የፖሊስ ሚንስትሩ፤ በከተማዋ መንግሥት የሕግ የበላይነትን የማስከበር ኃላፊነቱን ነው የሚወጣው ብለዋል።

ጦሩ የተሰማራው ለሦስት ወራት ለሚዘልቅ ኦፕሬሽን እንደሆነ እና በዚህም ችግሩ የማይቀረፍ ከሆነ እንደ አስፈላጊነቱ ሊራዘም እንደሚችል ተጠቁሟል።

በርካቶች ግን በኬፕ ታውን ዘረፋ እና መሰል ወንጀሎች የተበራከቱት በከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ያለው የኑሮ ልዩነት እየሰፋ በመምጣቱ ነው በማለት መንግሥት ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ጥያቄን በኃይል ለመመስ እየሞከረ ነው በማለት ትችት ይሰነዝራሉ።

ከ3.4 ሚሊዮን በላይ ሕዝብን ትልቋ የደቡብ አፍሪካ ከተማ የሆነችው ኬፕ ታውን፤ በቅንጡ መኖሪያ መንደሮች የሚኖሩ የሃብታሞች እና የሚመገቡት እንኳ የሌላቸው ድሆች መኖሪያ ከተማ ናት።

ሥራ አጥ እና ደሃ ለሆኑ ወጣቶች እነዚህ ወሮበላ ቡድኖች ገንዘብ ማግኛ አማራጮችን ይሰጧቸዋል።