በቡሩንዲ የተሰጠ ሹመት ቁጣን ቀሰቀሰ

በቡሩንዲ የተሰጠ ሹመት ቁጣን ቀሰቀሰ Image copyright AFP

በበርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂ የሚደረጉት የቡሩንዲ ሚሊሻ ኃላፊ የሃገሪቱ ብሔራዊ የሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ጣቢያ ኃላፊ ተደርገው መሾማቸው ቁጣን ቀሰቀሰ።

ሂዩማን ራይትስ ዎች የኤሪክ ናሺሚሪማን ሹመት ''የሰብዓዊ መብት ጥስት ለተፈጸመባቸው ዳግም በደል ነው፤ ለነጻ ፕሬስም አፈና ነው'' ብለዋል።

ኤሪክ ናሺሚሪማን ይመሩት የነበረው ቡድን ሰዎች ገድሏል፣ አስገድዶ ደፍሯል እንዲሁም ዘረፋ ፈጽሟል የሚል ክስ በተደጋጋሚ ይቀርብታል።

የቡሩንዲ መንግሥት ተፈጸሙ የሚባሉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ከእውነት የራቁ ሲል ያጣጥላቸዋል።

በደቡብ አፍሪካ ኬፕ ታውን እየጨመረ የመጣውን ውንብድና ለመቆጣጠር ጦር ተሰማራ

የጋዜጠኛዋ መገደል ለምን የዓለም መነጋገሪያ ሆነ?

ኤሪክ የሚመሩት ኢምቦኔራኩሬ ቡድን የገዢው ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ ሲሆን ፕሬዝዳንት ፒዬር ኒኩሩንዚዛ እአአ 2015 ላይ አጨቃጫቂ በነበረው ምርጫ አሸንፈው ስልጣን ከያዙ ወዲያ ተፈጸሙ በተባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ነው ቡድኑ ክስ የሚቀርብበት።

አጨቃጫቂ ምርጫውን ተከትሎ በርካታ የተቃውሞ ሰልፎች እና ግጭቶች ተከስተው ነበር። ይህም ብቻ ሳይሆን ፕሬዝደንት ኒኩሩንዚዛ ላይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተካሂዶ ነበር። ግጭቱን በመሸሽ ሃገር ጥለው የተሰደዱ ቡሩንዲያውያን ቀላል አይደሉም።

የሂዩማን ራይትስ ዎች የመካከለኛ አፍሪካ ዳይሬክተር የሆኑት ለዊስ ሙግዴ ለቢቢሲ ሲናገሩ፣ ''ግድያዎቹ፣ እሰሮች፣ ማስፈራራቱ እና ማስቀየቱ ዛሬም ቀጥሏል'' ብለዋል።

''ናሺሚሪማን ለፈጸሟቸው ወንጀሎች ተጠያቂ ነው መደረግ ያለባቸው እንጂ በአገሪቱ ከቀሩት ጥቂት የሚዲያ ተቋማት አንዱን እንዲያስተዳድሩ ሹመት መሰጠት የለበትም ይላሉ።

ናሺሚሪማን የሚመሩት ቡድን በተለይ ደግሞ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ሴት ዘመዶች ላይ ያነጣጠረ የወሲብ ትንኮሳን ይፈጽማል ሚል ተደጋጋሚ ክስ ይቀርብበታል። የቡሩንዲ መንግሥት ግን ኢምቦኔራኩሬ ይፈጸማል የተባለውን የወሲብ ትንኮሳ ያጣጥላል።

በቀጣዩ የፈረንጆቹ ዓመት ቡሩንዲ ሃገር አቀፍ ምርጫን ለማካሄድ እየተዘጋጀች ትገኛለች።

ከአንድ ዓመት በፊት የተሻሻለው የቡሩንዲ ሕገ-መንግሥት ፕሬዝደንቱ በቀጣዩ ምርጫም እንዲሳተፉ እድል የሚሰጥ ቢሆንም፤ ኑኩሩንዚዛ ግን ይህ የመጨረሻ የስልጣን ዘመኔ ነው ብለዋል።

ተያያዥ ርዕሶች