ለሲዳማ ክልልነት 'ይሁንታ ተሰጠ' በሚል በርካቶች ሐዋሳ ውስጥ ደስታቸውን እየገለጹ ነው

የሲዳማ ወጣት

የሲዳማ ክልል የመሆን ጥያቄ 'ይሁንታ ተሰጠ' በሚል በሐዋሳ በርካቶች ደስታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

ምንም እንኳን ከየትኛውም የመንግሥት አካል የተሰጠ ይፋዊ መግለጫ ባይኖርም፤ ክልሉን የሚያስተዳድረው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ሲዳማ በክልል እንዲዋቀር 'ያለውን ድጋፍ ገልጿል' በሚል በርካቶች በተለያየ መንገድ ደስታቸውን እየገለጹ ነው።

ዛሬ ከረፋዱ ጀምሮ የሲዳማ የዘመን መለወጫ በዓል በሚከበርበት ጉዱማሌ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በርካቶች እየተሰባሰቡ ይገኛሉ።

ደኢህዴን ባለፉት 9 ቀናት በአዲስ አበባ ከተማ ስብሰባ እያካሄደ የሚገኝ ሲሆን ከሚነጋገርባቸው ጉዳዮች መካከል በክልሉ ውስጥ የቀረቡ ክልል የመሆን ጥያቄዎች ዋነኛው እንደሚሆን ይገመታል።

ባለፈው ዓመት ክልል የመሆን ጥየቄን የተነሳበት የሲዳማ ዞን ነዋሪዎች ትናንት እሁድ በሐዋሳ ከተማ ተሰብስበው የሲዳማ ክልል በሚመሰረትበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸውም ተነግሯል።

በሲዳማ የሐገር ሽማግሌዎች በተመራው በዚህ ስብሰባ ላይ በርካታ በማኅበረሰቡ ውስጥ ተሰሚነት ያላቸው ሰዎች የተገኙበት ሲሆን ዋነኛው አጀንዳም ውጥረትን በፈጠረው የክልል የመሆን ጥያቄ ሂደት ላይ ነበር።

በስብሰባው መጀመሪያ ላይ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር አለመግባባት የነበረ ሲሆን በስብሰባው መሪዎችና በጸጥታ አካላት መካከል ንግግር ከተደረገ በኋላ ያለምንም ችግር ስብሰባው መካሄዱን ተሳታፊዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ያልተነገረለት የኮንሶ ጥያቄ

በጉዱማሌ በተካሄደው በዚህ ስብሰባ ላይ ከተለያዩ የሲዳማ አካባቢዎች የመጡ የሐገር ሽማግሌዎች፣ ባህላዊ መሪዎችና የብሔረሰቡ ወጣቶች ተወካዮች ተሳትፈዋል።

በስብሰባው ላይ በዋናነት ምላሽ እየተጠበቀበት ስላለው ክልል የመሆን ጉዳይ ውይይት መደረጉን ከታዳሚዎቹ መካከል ለቢቢሲ የገለጹ ሲሆን፤ በዋናነት ከህጋዊ ሂደቱ ቀደም ብሎ ክልልነትን ለማወጅ የተያዘው ዕቅድ ዙሪያ ከተሰብሳቢዎቹ ሃሳብ መሰንዘሩም ተገልጿል።

በዚህም ዞኑ ክልል የመሆን ጥያቄን ያቀረበበት ሐምሌ 11ን መሰረት በማድረግ፤ በዚሁ ዕለት ክልልነትን ማወጅ ወይም ይህንን ውሳኔ ማዘግየት በሚሉት ሁለት ሃሳቦች ዙሪያም ውይይት መደረጉን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ስብሰባው የታደሙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አምስት ነጥቦች ስለጌዲዮ ተፈናቃዮች

በስብሰባው ላይ ስለተደረሰበት ውሳኔ በግልጽ የተነገረ ነገር ባይኖርም አንዳንድ ሰዎች የሲዳማ የሐገር ሽማግሌዎች ዞኑን ወደ ክልል የመሸጋገሩ ሂደት እንደታቀደው እንዲካሄድ ወስነዋል ቢሉም ቢቢሲ ያነጋገራቸው የስብሰባው ተሳታፊዎች ግን ግልጽ ያለ ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።

የስብሰባው አስተባባሪዎችም ስለደረሱበት የመደምደሚያ ውሳኔ የሰጡት መግለጫ የለም፤ ነገር ግን በጥቅሉ የዞኑ ሕዝብ ከራሱ በኩል ክልል የመሆን ጥያቄውን በተመለከተ የሚጠበቅበትን ማድረጉንና ቀሪው ጉዳይ የደቡብ ክልልና የማዕከላዊው መንግሥት እንደሆነ ገልጸዋል።

ሲዳማ ዞን ወደ ክልል እንዲሸጋገር በዞኑ ምክር ቤት ጥያቄ የቀረበው ባለፈው ዓመት ሐምሌ 11 ሲሆን እስካሁን ተግባራዊ ምላሽ ስላልተሰጠ በዚሁ ዕለት ክልልነትን ለማወጅ እንቅስቃሴ መጀመሩ እርምጃው ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዳይሄድ ስጋትን ፈጥሯል።

ደቡብ ክልል አዲስ ለተፈናቀሉ 54 ሺህ ጌድዮዎች የፌደራል መንግሥትን ድጋፍ ጠየቀ

ይህንንም በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ከሳምንት በፊት በተወካዮች ምክር ቤት እንደተናገሩ ለቀረበው ጥያቄ ሕጋዊ ምላሽ እስኪሰጥ ድረስ በትዕግስት መጠበቅ እስደሚያስፈልግ ገልጸው "በኃይል እና በደቦ ለማስፈጸም የሚሞክሩ አካላት ካሉ" ሕግን ለማስከበር መንግሥት እርምጃ እንደሚወስድ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።

የደቡብ ክልልን የሚመራው ፓርቲ ደኢህዴን አዲስ አበባ ውስጥ ስብሰባ ማድረግ ከጀመረ ቀናት ያለፉት ሲሆን ከስብሰባው በኋላ የሲዳማን ጉዳይና ስለክልሉ አጠቃላይ አወቃቀር አንዳች ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ከሃምሳ በላይ ብሔር፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚገኑበት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ማኅበረሰቦች መካከል ሲዳማን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉት ክልል የመሆን ጥያቄ እያቀረቡ ነው።

ተያያዥ ርዕሶች