በባህር ዳሩ የተኩስ ልውውጥ ሦስት ሰዎች ሞቱ

ባህር ዳር

ትናንት እሁድ ባህር ዳር ከተማ ውስጥ አባይ ማዶ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በአካባቢው ሚሊሻዎችና ሲፈለግ በነበረ በአንድ ግለሰብ መካከል በተደረገ የተኩስ ለውውጥ የሦስት ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገለጸ።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የባህር ዳር ፖሊስ አባል ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከዚህ ቀደም ተፈጸሞ ከቆየ ሌላ የግድያ ወንጀል ጋር በተያያዘ ተጠርጥሮ ሲፈለግ የቆየ ነው የተባለን ግለሰብ ሊይዙ ሲከታተሉት የነበሩ የአካባቢው ሚሊሻዎች ላይ ተኩስ በመክፈቱ ነው ጉዳት የደረሰው።

ሸፍቶ ነበር የተባለውን ግለሰብ ሲከታተሉ የቆዩት ሁለት የሚሊሻ አባላት፤ እሁድ ምሳ ሰዓት አካባቢ ተጠርጣሪው አለበት ወደተባለው ቤት በሄዱበት ጊዜ ተተኩሶባቸው ህይወታቸው ሲያልፍ ተጠርጣሪው በሌሎች የጸጥታ አባላት እንደተተኮሰበት ለማወቅ ተችሏል።

“የኢህአፓና መኢሶን ነገር አማራ ክልል ላይ ሊከሰት ይችላል ብዬ ነበር”

"መግለጫ የምንሰጠው ሰዎችም ልንታሰር እንችላለን" የአማራ ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ

በተኩስ ለውውጡ የተመቱት ሁለቱ ሚሊሻዎች ወዲያው ህይወታቸው ሲያልፍ ተፈላጊው ግለሰብ ግን ከቆሰለ በኋላ ወደ ሆስፒታል ተወስዶ ነው ህይወቱ ያለፈው ተብሏል።

ከሳምንታት በፊት መንግሥት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ነው ካለው ግድያ ጋር በተያያዘ ከገባችበት ድንጋጤ በማገገም ላይ በምትገኘው የባህር ዳር ከተማ ውስጥ እሁድ ዕለት ያጋጠመው የተኩስ ልውውጥ በነዋሪዎች ላይ ስጋትን ፈጥሮ ነበር።

ስለክስተቱ ከክልሉም ሆነ ከባህር ዳር ከተማ የፖሊስ ኃላፊዎች ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ኃላፊዎቹ ስብሰባ ላይ በመሆናቸው ምክንያት አልተሳካም።

ተያያዥ ርዕሶች