በአውስትራሊያ አራት ልጆች መኪና ሰርቀው ተሰወሩ

ታዳጊዎቹ ሠርቀው ያሽከረክሯት የነበረችው መኪና Image copyright QUEENSLAND POLICE
አጭር የምስል መግለጫ ታዳጊዎቹ ከወላጆቻቸው ሠርቀው ያሽከረክሯት የነበረችው መኪና

በአውስትራሊያ አራት ትንንሽ ልጆች መኪና ሰርቀው ረዥም ርቀት ከነዱ በኋላ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

ልጆቹ 900 ኪሎ ሜትር ከነዱ በኋላ ነው ፖሊስ የደረሰባቸው።

ተግባሩን የፈጸሙት ታዳጊዎች ገና 14 ዓመት እንኳ ያልሞላቸው ናቸው። ልጆቹ ነዳጅ ሲያልቅባቸው ማደያ እየገቡ ቤንዚል ይሰርቁ ነበር ብሏል ፖሊስ።

"ብ/ጄኔራል አሳምነውን ቀድቻቸዋለሁ" ጋዜጠኛ ፋሲካ ታደሰ

“በአሁኗ ኢትዮጵያ በፀረ ሽብር ሕጉ ክስ መኖር የለበትም” ዳንኤል በቀለ

የጣልያን ፍርድ ቤት በተሳሳተ ማንነት የታሰረው ኤርትራዊ ነፃ መሆኑን ወሰነ

ሦስት ወንዶችና አንዲት ሴትን ያካተተው የጀብደኛ ሕጻናት ቡድን ከአንድ ቤተሰብ የተገኙ ወይም ወንድምና እህት አይደሉም። አንደኛው ልጅ መኪናውን ከወላጆቹ ሰርቆ ነው የጠፋው። ደግነቱ መኪናው ለረዥም ርቀት የሚሆን 4በ4 ሞዴል የሆነ ጠንካራ ተሽከርካሪ ነበር።

ልጆቹ ጉዟቸውን የጀመሩት ከኩዊንስላንድ በሳምንቱ መጨረሻ ሲሆን፤ አንደኛው ልጅ ለወላጆቹ "ሄጃለሁ" የሚል ማስታወሻ ትቶላቸው ከመሄድ ውጭ ለማንም ትንፍሽ አላሉም።

ይህ አዳጊ ለወላጆቹ በተወው ማስታወሻ ወዴት እንደሚሄድ አልጠቀሰም።

እሑድ ጠዋት ልጆቹ 140 ኪሎ ሜትር ከነዱ በኋላ ባናና በምትባለው ከተማ አንድ ማደያ ገባ ብለው ነዳጅ ቀድተዋል። የማደያው አንድ ሠራተኛ በአጋጣሚ አይቷቸውም ነበር።

ይህ ሠራተኛ ለዴይሊ ቴሌግራፍ እንደተናገረው፤ መኪናው እንደ ማንኛውም በመደበኛ ሾፌር እንደሚዘወር ተሽከርካሪ ወደ ማደያው ሲገባ ማየቱንና ከመኪናው የወረደውን ትንሽ ልጅ ሲመለከት ግን መገረሙን አብራርቷል።

"በጣም አጭር ልጅ ነው ያየሁት፤ ቁመቱ መስኮቱ ጋ ራሱ አይደርስምኮ" ይላል ይኸው የማደያው ሠራተኛ።

በዚያኑ ቀን ከሰዓት ፖሊስ መኪናውን ግራፍተን በምትባል ትንሽ ከተማ አቅራቢያ አይቷታል። ሆኖም ጥርጣሬ ብቻ ስለነበረው ፖሊስ ጉዳዩን ቸል ሳይለው አልቀረም።

የኋላ ኋላ ልጆቹ ብዙ ኪሎ ሜትር ከነዱ በኋላ ፖሊስ ተከታትሎ ደርሶ አስቁሟቸዋል። ከመኪናው እንዲወርዱ ሲጠየቁ ግን ልጆቹ በጄ አላሉም። እንዲያው በራቸውን ቆልፈው አንከፍትም ብለው አስቸግረዋል።

ልጆቹ 900 ኪሎ ሜትሩን ለማሸከርከር ከ10 ሰዓት በላይ እንደወሰደባቸው ይገመታል።

ፖሊስ ልጆቹን እንደሚከስ ቢናገርም በምን ወንጀል እንደሚከሳቸው ዝርዝር መግለጫ አልሰጠም።

በኩዊንስላንድም ሆነ በኒው ሳውዝ ዌልስ ትንሹ መንጃ ፍቃድ የማግኘት ዕድሜ 17 ዓመት ነው።

አራቱ ታዳጊዎች ግን ዕድሜያቸው ከ10 እስከ 14 ዓመት ቢሆን ነው።

ልጆቹ ይህንን የስርቆሽ ጉዞ ለማድረግ ምን እንዳነሳሳቸው አልተገለጸም። እንዲሁ ልጅነት ይሆን?

ተያያዥ ርዕሶች