"በጎጃም ማርያም ቤተክርስቲያን ለመስጊድ 3ሺ ብር ረድታለች' ተባልኩኝ" ሐጂ ዑመር ኢድሪስ

ተቀዳሚ ሙፍቲህ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ በሚሊንየም አዳራሽ ከጠ/ሚ ዐብይ የክብር ዶክትሬት በተቀበሉበት ወቅት Image copyright office of the PM
አጭር የምስል መግለጫ ተቀዳሚ ሙፍቲህ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ በሚሊንየም አዳራሽ ከጠ/ሚ ዐብይ የክብር ዶክትሬት በተቀበሉበት ወቅት

ተቀዳሚ ሙፍቲህ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ባለፈው ቅዳሜ በሚሌኒየም አዳራሽ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ተበርክቶላቸዋል። ይህንኑ ተከትሎ ከሙፍቲህ ሐጂ ዑመር ጋር ያደረግነውን አጭር የስልክ ቃለ ምልልስ እነሆ፤ [ማስታወሻ፡ በርሳቸው የተነገሩ የአረብኛ ቃላትን ሙሉ በሙሉ ከመግደፍ ይልቅ በቅንፍ አቻ የአማርኛ ትርጉም መስጠትን ወደናል።]

እንኳን ደስ አለዎት ሐጂያውቁ ነበር እንዴ እንደሚሸለሙ? መቼ ነበር የሰሙት?

ወላሂ አሁን ለታ..ማነው ሐሙስ ማታ ነው ታከለ፣የተከበሩ ምክትል ከንቲባ፣ ደውለው የነገሩኝ። 'ቅዳሜ እንዲህ ያለ ነገር ስላለ እንዲትመጡልን' ብለው ምክትል ከንተባው ደወሉልኝ። አሁን ለታ ማታ። በጣም ነው የደነገጥኩት፣ እኔ እንዳው።ይሄ ነገር መስመሬም ስላልሆነ ደሞም ያሰብኩትም፣ የጠረጠርኩትም ስላልሆነ በጣም በጣም ነው 'ያኣጀበኝ' [የደነቀኝ]፤ አለቀስኩኝ የሚገርምህ ነገር...ወላሂ አለቀስኩኝ...

"መንግሥት የሚደግፈው የሙስሊሙን ሕብረተሠብ ነው" ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

ሐጂ! ለምን የተሸለሙ ይመስሎታል ግን...?

ምን አልከኝ...ልጄ!

በምን ምክንያት የተሸለሙ ይመስሎታል...ምን ስላበረከቱ...?

ወላሂ እንግዲህ የሽልማቱ ምክንያት የልፋት ውጤት ነው የሚመስለኝ። እንግዲህ አዲስ አበባም 54 ዓመቴ ነው ከመጣሁ። እንግዲህ እዛም አገራችን 'ስቀራ' [ቅዱስ ቁርዓንን ስማር]፣ ሳስቀራ [ሳስተምር]...በሌላም በሌላም ለሕዝብ ልፋቴ በጠቅላላ ወደ 70 ዓመት ይሆናል። አንድ ቀን ለልጆቼ ወይ ለራሴ ብዬ አላቅም።

በየክፍለ አገሩ በየዞኑ በየወረዳው እዞራለሁ። በኢትዮጵያ በሙሉ 'ፈትዋ' ሳደርግ ነው የኖርኩት። ደግሞ በኋላ አንድነት ብለን የዛሬ 11 ዓመት ገደማ ጀምረን ነበር። ኋላ አንድነቱ ደስ ያላላቸው ሰዎች አፍርሰውት ነበር። [እኔንም] ተው አሉኝ፣ ተውኩት። አላህ ደግሞ ጊዜያት አምጥቶት የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዐቢይ አሕመድ እሳቸው ናቸው እንግዲህ ወደ አንድነት እንድንሄድ ያደረጉን። 'ጀዛቸውን' [ውለታቸውን] አላህ ይክፈላቸው።

በኮምቦልቻ ከተማ በተከሰተ ግጭት ሰዎች ላይ ጉዳት ደረሰ

ቴምር በረመዳን ለምን ይዘወተራል?

አላኩሊሃል [ያም ሆነ ይህ] ሽልማቱ መሠረቱ የመሰለኝ አንደኛው በሙስሊሙና በክርስቲያኑ መካከል ሰላምና አንድነት የምፈልግ መሆኔና በዚህም መልፋቴ። ሁለተኛ በመንግሥት እና በሕዝበ ሙስሊሙ መካከል የሚያቀራርብ ሰላም መፈልጌ፤ ሦስተኛ ሙስሊሙና ሙስሊሙ ደግሞ ከመቃረን፣ ከመዳማት [ወጥቶ] አንድ መሆን አለበት እያልኩ እንግዲህ ወደ 40 ዓመታት መድከሜ ይመስለኛል። ዋናው ይሄ ይመስለኛል።

ከይህ ሌላ 'አላኩሊሃል' [እንዲሁ በአጠቃላይ] የሙስሊም አገልግሎት በብዙ ዓይነት ነው። በማስተማር በዳእዋ [የስብከት አገልግሎት]። ቁርዓን እንዲሁ በሁለት በሦስት ዓይነት ተርጉሚያለሁ። ሌሎችም የተውሂድ ኪታቦችን [መጻሕፍትን] ብዙ የተረጎምኳቸው አሉ።

ሌላ በአረብኛ ደግሞ 'ዱአ'ን [ጸሎትን] በተመለከተ የነብያችንም ውዳሴ በተመለከተ ወደ 80 መጽሐፎች በአማርኛ ደርሻለሁ። እንግዲህ መቼም 'አላኩሊሃል' [ከሞላ ጎደል] ሕይወቴን መቼም የጨረስኩት ሕዝብን በሚያቀራርብ ነገር ነው።

አሁንም ደግሞ ዶ/ር ዐቢይ አንድነት ኮሚቴ ሰብሳቢ አድርጎኝ በዚያ ምክንያት አንድነት ባይገኝ ኖሮ ብዙ ደም እንደሚፋሰስ ሙስሊሙ በጣም በጣም ከባድ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ነበር ጥርጣሪያችን፤ አልሀምዱሊላህ ይኸው መቼም አንድነቱ ተከናውኖ ጀምረነዋል። አላህ መጨረሻውን ቢያሳምረው መቼም።

ለሲዳማ ክልልነት 'ይሁንታ ተሰጠ' በሚል በርካቶች ደስታቸውን እየገለጹ ነው

በአጠቃላይ ስለ ሙስሊሙም ሆነ ስለ ክርስቲያኑ፣ ስለመንግሥትም ሆነ ስለ ሕዝብ በለፋሁት ልፋትና በተጨነኩት ምክንያት ይመስለኛል [የተሸለምኩት]።..ብዙ አልቅሻለሁ፤ ብዙ ለቅሶ ነው ያለቀስኩት [ይህ እንዲሆን]። በዚያ መነሻ አላህ ይህን [ስጦታ] ያመጣው ይሆናል እንጂ የምለው... እኔ [ይህ ይመጣል ብዬ] የጠረጠርኩት ጉዳይ አይደለም። መንግሥትም ይሄን ጉዳይ ያስብበታል ብዬ ትዝ አላለኝ...።

ለሃይማኖት አባት እንደዚህ ያለ ደረጃና ሽልማት መሸለም በተለይ በአገራችን እኮ ይሄ የመጀመርያ ነው፤ ታይቶም አይታወቅም፤ ተሰምቶም አይታወቅም። ለክርስቲያኖች አልተሠራም፣ እንኳን ለሙስሊሙና። እኔ ብቻ ሳይሆን የሚያስደስተኝ ሙስሊም ሁላ ሊደሰትበት የሚገባ ነው። በሕይወት ያሉት አደለም የሞቱት የታገሉት አባቶቻችን ሁላ ውጤት ነው የሚል አመለካከት ነው ያለኝ መቼም...

ሐጂ ዑመር፤ ሙስሊሞች ብቻ ሳይሆን የሌላ እምነት ተከታዮችም'ኮ እንደ ሃይማኖት አባት ለርስዎ መልካም ስሜት ያላቸው ይመስለኛል፤...ሰዎች ያንን ይነገርዎታል? እርስዎስ ያውቃሉ ይሄን?

አውቃለሁኝ'ና፤ አሁንም ሳይሆን ፊትም ቀደም ባለ ጊዜ መጅሊስ ባለ ጊዜ ከ[ሃይማኖት] አባቶች ጋራ ስንሰባሰብ፣ ስንነጋገር ወዲያው እዚያው ጽፈው ይሰጡኛል። 'እርስዎ ንግግርዎ ወርቅ ነው፤ ብር እንኳ አይደለም፣ ወርቅ ነው' ይሉኛል።

ሁለተኛ ደግሞ አጠቃላይ ነው ስለሃይማኖትህ ብቻ፣ ስለመስጊድ ብቻ ሳይሆን አንተ የምትናገረው ስለ አጠቃላይ ስለ ሙስሊሙም ስለክርስቲያኑም፣ ስለሆነ ንግግርህ መልካም ነው ይሉኛል። 'እንዳው ሙስሊሞች ጥሩ መሪ ሰጥቷቸዋል' እያሉ ሁልጊዜ ጽሑፍም ይሰጡኛል።

ባሁን ደግሞ እኔንጃ ከሙስሊሙ የበለጠ ክርስቲያኑ ነው ደስ ያለው የሚመስለኝ። በትናንቱ ሁኔታ ከሙስሊሙ የባሰ ክርስቲያኑ ነው ደስ ያለው።[እሑድ' ለታ ነበር ያነጋገርናቸው] በሄድኩበት 'አብረነህ ፎቶ እንነሳ፣ ዕድሜህ ይቆይልን' የማይል አንድ እንኳ የለም።

"ኢስላማዊ ባንክ ለኢትዮጵያ ምን ይፈይዳል?"

እኔም ደሞ ሙስሊምና ክርስቲያን ልዩነት የለኝም። የብሔር፣ የሃይማኖት ልዩነት አላውቅም፤ ድሀ ሀብታም አልልም። የተማረ ያልተማረ አልልም። እምነቴና አመለካከቴ እኩልነት የተመረኮዘ ስለሆነ የዚያ ውጤት ቢሆን ነው እንጂ [ተሸለምኩ] የምለው በጣም እንደው [የሰው ፍቅር] ካቅሜ በላይ ነው። ይህን በጣም አመሰግናለሁ።

ዕድሜዎ ስንት ደረሰ ሐጂ?

አሁንም ምናልባት ወደ 85ኛ ሳልጀምር አልቀርም... ይመስለኛል።

ጠ/ሚ ዐቢይ መምጣት ጋ ብዙ ተስፋዎች ነበሩ፤ አሁን ደግሞ 'ይቺ አገር መፍረሷ ነው፤ የሃይማኖትም ሆነ የብሔር እልቂት አይቀርላትም' የሚል ፍርሃት አለ። እርስዎ እንደው በቀረው የሕይወት ዘመንዎ ይህ ክፉ አጋጣሚ ይመጣል ብለው ይጨነቃሉ?

እኛ እንግዲህ በንጉሡ ጊዜ መቼም ዳር እስከ ዳር የኢትዮጵያ ሰላም ነበረ፥ እኛ የምናውቀው እንኳ በአገራችን በገጠር እንኳ በመንግሥት የተባለ እንደሁ የተቀመጠው አይነሳም፣ የቆመው አይቀመጥም። እግሩ ሊራመድ አንስቶ እንደሆነ መሬት አያስቀምጥም። ያንን ወቅት አይተናል።

በደርግም ደግሞ ያንን እልቂት፣ ያንን ረብሻም፣ ያንን 'ፊትና'ም [የሕይወት ፈተና] ደግሞ አይተናል።

ከዚያም በኢህአዴግ እንዲሁ ያየነውን አይተናል።

አሁን ግን የኔ አመለካከትና እንደኔ ሐሳብ ተሆነ ለእውነቱ እኔ ሰው አለሥራው ማመስገን አላውቅም። ዶ/ር ዐቢይ በተመረጡ ጊዜ በማግሥቱ ሲጠይቁኝ 'ባካችሁ ተስድስት ወር በኋላ ጠይቁኝ፤ አሁን አመስግኜ በኋላ ማማረር አልፈልግም' ነው ያልኳቸው።

እና አሁን ያሉት መሪ አመለካከታቸው አንድነት፣ ሰላም፣ ልማት፣ ዕድገት ስለሆነ 'የሚያአጅብ' [የሚደንቅ] እኮ ነው። አይተንም ሰምተንም አናውቅም። የደካሞች ቤት እኮ እየተሠራ ነው'ኮ በምክትል ከንቲባና በዶ/ር ዐቢይ አመራር። የሽማግሌዎች የባልቴቶች ቤት እየተሠራ ነው።

አል ሻባብ የጎሳ መሪዎችን አስጠነቀቀ

መቼም አሁን ችግር እፈጥራለሁ ቢል ችግር ፈጣሪውም ይሳካለታል ብዬ ምንም ሐሳብ የለኝም። ጥርጣሬም የለኝም። ይሄን [መልካም ጅማሮ] መቼም የማይቀበል አእምሮ ያለው ሰው፣ አለ ብዬ አልገምትምና ሁሌም አገራችን ታድጋለች፣ ትለማለች፣ አንድነታችን ይጠናከራል የሚል ሐሳብ ነው ያለኝ እንጂ እኔ አገር ይፈርሳል፣ ሽግር ይፈጠራል አልልም።

በዚህ ረመዳን ወቅት በሙስሊም አካባቢ ሰላም ይከርማል ወይ ብሎ ሰው ጥርጣሬም ነበረው፤ አላህ ግን ሰላም አክርሞናል። ሐሳቤ የኔ አመለካከትም ይኸው ነው። ከይህ ሌላ ያለውን ደግሞ 'ረበል አለሚን አላህ' [የዓለማቱ ጌታ] ያውቃል።

አላህ ደግሞ ችግር ፈጣሪውን ወደ ሰላም እንዲመለስ፣ ሥልጣን ፈላጊውም በመንገዱ እንጂ አለመንገዱ እንዳይፈልግ አላህን እንለምናለን፤ ዱአ አናደርጋለን።

ዓለማዊ ትምህርትን ምን ያህል ገፍተውበታል ሐጂ?

ዓለማዊ ትምህርት የለኝም፤ እኛ ከቶም ሀሁ ማለት ያን ጊዜ ፊደል በ'መሻኪኮቻችን' [በሃይማኖት አዋቂዎች ዘንድ] እና እንደ 'ኩፍር' [ከሃይማኖቱ ማፈንገጥ] ነበር የምንቆጥረው። እኛ ነን ከተማ ከገባን በኋላ አሁን ደረሳውንም ተማሩ ያልነው። ያን ጊዜ ከተማረ በሴት ወይ በሥልጣን ደልለው 'ያከፍሩታል' [ሃይማኖቱን ያስጥሉታል] ተብሎ በወሎ ኡለማው በጣም ያስጠነቅቅ ነበር። ስለዚህ እኔ ሃይማኖታዊ እንጂ ዓለማዊ ትምህርት የለኝም።

ግን የሚገርመው ዓለማዊ ትምህርት የተማሩትን ጽፈው ያመጡትን ማስተካከል እችላለሁ። ይሄ የተፈጥሮ ጸጋ ይመስለኛል።

ከወሎ ብዙዎቹ ወደ አልአዝሃር ዩኒቨርስቲ እየሄዱ ይማሩ ነበር በዚያን ጊዜ?እንዴት ሳይሄዱ ቀሩ?

አልአዝሃር አልሄድኩም። ከወሎ ብቻ ነው የተማርኩት፤ ሐጂ መሀመድ ሳኒ ዘንዳ መጣሁ እንጂ ..። ደግሞስ ለሃይመኖት ትምህርት አል አዝሃርም ሆነ ማንም ሆነ እንደው ዲግሪ ለመቀበሉ፣ ስም ለማውጣት ነው እንጂ በትምህርት በኩል እኮ የአገራችንን 'ዑለማ' [የሥነ መለኮት ምሁር] የመሰለ አንድ እንኳ በዓለም አይገኝም። ጥልቅ ዕውቀት ያላቸው የአገራችን 'ዑለማዎች' ናቸው። ችግሩ ብቻ ወደ ከተማ አልገቡም፤ እና ወደ አመራሩም ኪታብ ወደማበጀቱ [መጽሐፍ መድረሱ] ውስጥ አልገቡም ነው እንጂ አገራችን ዑለማዎችን የሚያህል አንድም የለም፤ በየትም።

በሊቢያ የሚገኙ የስደተኛ ማጎሪያዎች እንዲዘጉ ተጠየቀ

እርስዎ የቀድመው ተወዳጅ የሃይማኖት አባት ሐጂ መሐመድ ሳኒ ሀቢብ ተማሪ ነዎት እንዴ?

አዎ እርሳቸው ዘንዳ 'ሐዲስ 'ልቀራ'፣ ሌላውን 'ፊቂሁን' [ኢስላማዊ ሕግ] ነህው [የአረብኛ ሰዋሰው] ጨርሼ እዛ ተመልሼ ሼክነት ልወጣ ነበር ሼኮቹ የላኩኝ። አላህ እሳቸውን እዚህ [አዲ'ሳባ] አመጣ፣ እሳቸውን ብዬ እዚህ መጣሁኝ፤ እዚህ ሕዝብ ያዘኝ፣ በዚያው ቀረሁ፣ እሳቸውም እዚሁ ቀሩ።

በሚሊንየም አዳራሽ በብዙ ሙያ ዘርፍ ለተመረቁ ብዙ ሺህ ተማሪዎች ንግግር ሲያደርጉ ነበር። እርስዎ ግን የቱ ትምህርት ዘርፍ ይበልጥብዎታል?

[ሳቁ] እኔ ይሄን ይሄን አልልም። ሁሉም ጠቃሚ ነው። ያስተዳደሩን ብታየው፣ አለ አስተዳደር አይሆንም። የኢኮኖሚውን ብታየው አለ ኢኮኖሚስት ታልሆነ መቼም ይሆንም። የማስተማርም ሙያ ብታየው አስተማሪ ከሌለ ተማሪ የለ። እና ዕውቀት ሁሉም አስፈላጊ ነው። ሁሉም አንገብጋቢ ነው። ግን እገሌ ከእገሌ ትምሀርት ይሻላል አልልም። ዝንባሌው እንጂ በኔ በኩል ሁሉም እኩል ጠቃሚ ነው፤ ሁሉም ጥሩ ነው የሚል አመለካከት ነው ያለኝ፤

እኔንኳ ጥያቄዬ የነበረው ሐጂ... እርስዎ ዝንባሌዎ ምን ነበር? ከዓለማዊው ትምህርት...

ወላሂ እኔ ብማር ኖሮ የምማረው ኢኮኖሚን በተመለከተ ይመስለኛል። እኔ ሼክነቱ በቀረ ነጋዴ ነበር የምሆነው። ሥልጣንን አልወደውም። የአመራር ትምህርት አልመርጥም። የኢኮኖሚ ትምህርት ነበር የምመርጠው ይሆናል።

የግል ሕይወት በተመለከተ ትንሽ ጥያቄ ላንሳልዎ? ስንት ቤት አለዎ...?ስንት መኪና?

[በአጭሩ ከሳቁ በኋላ] እኔ የምኖርበት ብታየው ያስቀሃል፣ ያስገርምሃል። እላይ መርካቶ ቤት ነበረኝ። እኔ መስጊድ እሠራለሁ እንጂ መኖርያ ቤት አልሠራም ብዬ የሚመጣው ሁላ 'የሙፍቲ ቤት ይሄ ነውንዴ?' ጉድ አረ ይሄን ቤት ለውጡ' ያላለኝ ሰው የለም። አሁን ደግሞ አዲስ ቦታ ነው ያለሁት።

የጋዜጠኛዋ መገደል ለምን የዓለም መነጋገሪያ ሆነ?

ሁን የት አካባቢ ነው የሚኖሩት ታዲያ?

እዚህ ጋርመንት የሚባል ሐና ማርያም ይባላል። በሱ አሻጋሪ ነው የምኖረው። አሁን እዚህ ከመጣሁ ሦስት ዓመቴ ነው። ሰፊ ቦታ ነው። ቆርቆሮ ነው፤ ግድግዳውም፣ ጣሪያውም ቆርቆሮ በቆርቆሮ ነው። ግን ሰፊ ነው።

ይሄን ያህል'ኮ ጭንቅ የለኝም፤ እኔ አዲስ አበባ ይሄን ያህል 54 ዓመት ስቀመጥ ሙተአሊም [ተማሪዎቼ] ጋ ነው የምቀመጠው። የምበላው ሙተአሊም ጋ ነው። ገንዘቤን ለሙተአሊም ነው የማወጣው። ይሄን ያህል የደላ ኑሮም የለኝም።

ስንት ልጆች አለዎት?

ዐሥራ አንድ ነበሩ። አንድ ሞቷል። አሁን 10 አሉ።

እርስዎ የመጡት ከወሎ አካባቢ ይመሰለኛል እና እዛ ደግሞ ሙስሊምና ክርስቲያኑ በመተሳሰብ ተፋቅሮ የመኖር ጠንካራ ባህል አለ። የተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ከዚያ አካባቢ ምን ሊቀስም ይችላል?

ወላሂ እኛ እንግዲህ እስካለንበት ሕይወት ድረስ በወሎ ክፍለ አገር የብሔር ወሬ ጭራሽ የለም። ሁለተኛ የሃይማኖትም ልዩነት የለም። ወጣቶች ሙሽርነት እንኳ አብረው ይሞሸራሉ። ልዩነት ነገር አናውቅም፤ ሙስሊሙ ቤተክርስቲያን ሲገነባ ይረዳል፤ክርስቲያኑ ደግሞ መስጂድ ሲሠራ ይረዳል። የሚገርመው ክርስቲያኑ ደረሳ [መንፈሳዊ ተማሪዎች] ጠርቶ፣ አርዶ፤ አሳርዶ ሰደቃ [ዝክር] ይሰደቃል [ያበላል]። ይሄ ወሎን በተመለከተ ነው።

ሌላው ቀርቶ ክርስቲያኑ አገር የሚባለው ጎጃም ሎማኔ የሚባል ከተማ መስጊድ ለምርቃት ሄጄ 'እገሌ ክርስቲያን ለመስጊድ ይሄን ያህል ረድቷል፤ እገሌ ደግሞ ይሄን ረድቷል፤ ከተባለ በኋላ በመጨረሻ 'ማርያም ቤተክርስቲያን 3ሺ ብር ረድታለች' ብለው ነው ያቀረቡልን። እንደዚያ ተባልኩኝ።

ባለጊዜው የግመል ወተት

ይሄ ነው ሕዝባችን። የፖለቲካ ሰዎች በታተኑት እንጂ የኢትዮያ ሕዝብ የብሔር ልዩነት አያቅም፤ የሃይማኖት ልዩነት አያውቅ። ይሄ አሁን [በሃይማኖት መቃቃር] መጤ ተግባር ነው። እና እንዲህ ያለውን አሁንም ቢሆን ከሕዝቡ ልብ ላይ እንዲፋቅና እንዲለቅ ማድረግ ያስፈልጋል። ለመፋቅ ወደፊት ብዙ ዓመታት ይጠይቃል ነው እንጂ የምለው መልቀቁ መቼም እንደማይቀር ነው።

ባለሥልጣኖች እንዲሁ ለሥልጣናቸው ሲሉ [ሕዝቡ ላይ] መርዝ ነሰነሱበት እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲህ አልነበረም። እኛ ተወሎ በዚህ በአርሲ በባሌ በጅማ የመጣ እንደሆነ ተከብሮ ተረድቶ ነበር የሚኖረው። ባሌን ያቀና የወሎ 'ኡለማ' ነው፤ አርሲን ያቀና የወሎ ኡለማ ነው፤ ጅማን በአባጂፋር ጊዜ ያቀና የወሎ ኡለማ ነው፤ ልዩነቱ እኮ በአገራችን አናውቅም ፤ ከመጣበት አናውቅም፤ በሽታው ከመጣበት ይመለስልን እያልን ነው [ዱአ የምናደርገው]።

እየከፋ የመጣውን ዘረኝነትንስ በተመለከተስ ምን ይላሉ ሐጂ...

ዘረኝነትን በተመለከተ ሃይማኖታችን 'ቆሻሻ ነው' ብሎ ነው የሚለው። ነብያችን (አለሂሰላቱ ወሰላም) 'ወደ ዘረኝነት መጠጋት፣ እኔ የገሌ ዘር ነኝ ብሎ በቀለም፣ በሀብት ወይ በሌላ ማድላት፣ መኩራራት ይሄ የሚሸት ነገር [ክርፋት] ነው' ነው ብለው ነው ያስተማሩት።

አሁንም ዘረኝነት ሕዝባችን ቆሻሻነቱን አውቆ እንዲጠነቀቅ ከማስተማር በስተቀር ሌላ ምንም መፍትሄ የለውም። ይለቃል የሚል አመለካት ነው ያለኝ። መልቅቁ ግን ጊዜ ሊወስድ ይችላል።

አንድ በሽታ በአካል ከተሰራጨ መድኃኒቱ ጊዜ ይፈልጋል እኮ፤ ጊዝያዊ በሽታ የሆነ እንደሆነ በአንድ መርፌ በኪኒኒ ይመለሳል። ውሎ ያደረ በሽታ ሕክምና ያስፈልገዋል። [የዘረኝነት] በሽታው ትንሽ ዓመታት ወስዶ ስለነበረ አሁንም ደግሞ ለማስለቀቅ ጥንካሬና ጊዜ ይጠይቃል።

አመሰግናለሁ ሐጂ!

በአገር ጉዳይና በኔ ጉዳይ አስበህ ለመጠየቅህ በጣም አመሰግናለሁ ልጄ፤ ለአገራችንም ሰላም እመኛለሁ፤ ወሰላሙ አለይኩም።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ