የፌስቡክ ዲጅታል ገንዘብ 'ሊብራ' ጥያቄን አስነሳ

ሊብራ በስልክ ላይ Image copyright Getty Images

አዲሱ የፌስቡክ ዲጅታል ገንዘብ በአሜሪካ ጥያቄ ተነሳበት።

የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስቲቭ ማንቺን ጋዜጠኞችን ሰብስበው የፌስቡክ አዲሱ ዲጅታል ገንዘብ ''ለሕገ-ወጥ ገንዘብ አዘዋዋሪዎች እና አሸባሪዎችን ለሚደግፉ መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል'' ሲሉ በዲጅታል ገንዘቡ ላይ ያላቸውን ስጋት ተናግረዋል።

''በዚህ ደስተኛ አይደለንም'' በማለት የፌስቡክ አዲሱ እቅድ በአሜሪካ ብሄራዊ የደህንነት ስጋት መፍጠሩን አስታውቀዋል።

አዲሱ የፌስቡክ ዲጅታል ገንዘብ አፍሪካን ያጥለቀልቅ ይሆን?

ዓለም ሁሉ የሚያወራለት ክሪይፕቶከረንሲ ምንድነው?

በአሁኑ ወቅት በጣም ተፈላጊ የሆኑ የዲጂታል ዘርፍ ሥራዎች የትኞቹ ናቸው?

ከቀጣዩ የፈረንጆቹ ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ ፌስቡክ ወደ ሁለት ቢሊዮን ለሚጠጉ ተጠቃሚዎቹ በዋትስአፕ፣ ኢንስታግራም እና በፌስቡክ መተግበሪያዎቹ አማካኝነት ግብይትን እንዲፈጽሙ ለማስቻል እየሰራ ይገኛል።

ሊብራ ተብሎ በሚጠራው ክሪፕቶከረንሲ ሰዎች በቀላሉ በመተግበሪያዎቹ አማካኝነት ገንዘብ ማስተላለፍ እና ግብይት መፈጸም ይችላሉ ተብሏል።

የፌስቡክ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ዛሬ ከኮንግረሱ ፊት ቀርበው ማብራሪያ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ዴቪድ ማርከስ የተባሉት የሊብራን ትግበራ የሚከታተሉ የፌስቡክ ባልደረባ የሴኔት ባንክ ኮሚቴ ፊት ቀርበው፤ የድርጅታቸውን አዲሱን እቅድ እንዴት እንደሚተገበር ያስረዳሉ።

''ክሪፕቶከረንሲዮች በጠቅላላው በሕገ-ወጥ ቡድኖች፣ በሳይበር ወንጀሎችን፣ ታክስ ለመደበቅ በሚጥሩ ግለሰቦች፣ የጦር መሳሪያዎች እና እጾችን ለመግዛት እና ለመሸጥ ጥቅም ላይ እያዋሉ ይገኛሉ'' በማለት ስጋታቸውን የገለጹት የግምጃ ቤት ኃላፊው፤ ፌስቡክ ከፍተኛ ደረጃ ያለው የደህነንት ማረጋገጫ ማቅረብ እንደሚኖርበት ጠቁመዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የክሪፕቶካረንሲዎችን ''አድናቂ አይደለሁም'' በማለት ፌስቡክ ምናልባትም የባንክ ፍቃድ ሊያስፈልገው እንደሚችል ጠቁመዋል።

የአሜሪካ የፌደራል መንግሥቱ ተቀማጭ ግንዘብ ቤት ኃላፊ ጄሮሜ ፖውል ፌስቡክ ሊተገብረው ያሰበው ሊብራ ብዙ ጥያቄዎች ተነስተውበታል ብለዋል።

ፌስቡክ በበኩሉ ከሊብራ አተገባበር ጋር በተያያዘ በርካታ ጥያቄዎች ከመንግሥት ኃላፊዎች እና ተቆጣጣሪዎች ሊነሱበት እንደሚችሉ እንደገመተ እና ለሁሉም ስጋቶች በንግግር ለመቅረፍ ዝግጁ ነኝ ብሏል።

ፌስቡክ 5 ቢሊየን ዶላር ሊቀጣ ነው

የፌስቡክ ባልደረባ ዴቪድ ማርከስ ''ሊብራ ከሃገራት የመገበያያ ጥሬ ገንዘብ ጋር ውድድር ውስጥ የመግባት ምንም አይነት ፍላጎት የለውም፤ የሊብራ ማህበረም የሊብራን ተቀማጭ ጥሬ ገንዘብ ይቆጣጠራል። ፌስቡክ ከተቆጣጣሪዎች እና መንግሥታት ይሁንታን ሳናገኝ ወደ ትግበራው አንሸጋገርም'' ብለዋል።

ክሪይፕቶ-ከረንሲን ምንድነው? ኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት 'ክሪይፕቶ-ከረንሲን'፤ የገንዘብ ልውውጦችን ደህንነት የሚያረጋግጥ፣ የተጨማሪ አሃዶችን መፈጠርን የሚቆጣጠር እና ገንዘብ መተላለፉን የሚያረጋግጥ ጠንካራ ክራፕቶግራፊ የሚጠቀም መገበያያ እንዲሆን ተደርጎ የተቀረጸ ዲጂታል ገንዘብ ሲል ይገልጸዋል።

ቢትኮይን ምንድነው? ከክሪፕቶከረንሲዎች አንዱ ነው። ቢትኮይን በቀላል ቋንቋ፤ ዲጂታል+ገንዘብ+መገበያያ በማለት ማጠቃለል ይቻላል። ይህ መገበያያ በኪሳችን ተሸክመን እንደምንዞረው የብር ኖት ወይም ሳንቲም ሳይሆን 'ኦንላይን' የሚቀመጥ ዲጂታል ገንዘብ ነው።

ሌላው የቢትኮይንና የተቀሩት የክሪይፕቶከረንሲዎች ልዩ ባህሪ በመንግሥታት እና በባንኮች አለመታተማቸው እንዲሁም ቁጥጥር አለመደረጉ ነው። ቢትኮይን የሚፈጠረው 'ማይኒንግ' በሚባል ሂደት ነው።

ሊብራ ከቢትኮይን በምን ይለያል፡ ሊብራ ልክ እንደ ቢትኮይን የሚፈጠረው 'ማይኒንግ' በሚባለው ሂደት ነው። ልዩነታቸው ሊብራ በሚታወቁ ኩባንያዎች ቁጥጥር ይደረግበታል። ቢትኮይን እና ሌሎች ክሪፕቶ-ከረንሲዎች በመንግሥታት እና በባንኮች አይታተሙም፤ ቁጥጥርም አይደረግባቸውም። የፌስቡኩ ሊብራ ግን በመንግሥታት እና በማዕከላዊ ባንኮች ቁጥጥር ይደረግበታል በተጨማሪም በጥሬ ገንዘብ ተቀማጭ ይኖረዋል።

ተያያዥ ርዕሶች