የጣሊያን ፖሊስ ከቀኝ ዘመም ጽንፈኛ ኃይሎች ሚሳዔል በቁጥጥር ስር አዋለ

ፖሊስ በወረራው ወቅት የያዝኩት ሚሳዔል እንከን የለሽ የሆነ እና በማንኛውም ሰዓት ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል ነው ብሏል። Image copyright EPA
አጭር የምስል መግለጫ ፖሊስ በወረራው ወቅት የያዝኩት ሚሳዔል እንከን የለሽ የሆነ እና በማንኛውም ሰዓት ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል ነው ብሏል።

የጣሊያን ጸረ-ሸብር የፖሊስ ግብረ-ኃይል በቀኝ ዘመም አክራሪ ቡድኖች ላይ ሰሜናዊ የሃገሪቱ ክፍል ባደረገው ድንገተኛ ወረራ የአየር ላይ የተኩስ ልውውጥ የሚደረግበት ሚሳዔልን ጨምሮ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ የጦር መሳሪያዎችን በቁጥጥር ሥር አዋለ።

ጽንፈኛ ቀኝ ዘመም ቡድኖች የፋሽስት እና የናዚ አመለካከቶችን የሚደግፉ፣ ስደተኛ ጠል ሲሆኑ ጸረ-ኮሚንስት ርዕዮተ ዓለምን ይከተላሉ።

ፖሊስ ባደረገው ድንተገኛ ወረራ 2 ጣሊያናውያንን እና የስዊዘርላንድ ዜጋ በቁጥጥር ሥር የዋለ ሲሆን፤ የናዚ ፕሮፖጋንዳ ቁሳቁሶችም ተይዘዋል።

ጣሊያን አዲስ መንግስት አዋቀረች

ይህ የፖሊስ ግብረ ኃይል በጣሊያን የሚገኙ ጽንፈኛ ቀኝ ዘመም ቡድኖች በሰሜን ዩክሬን ለሚንቀሳቀሱት ተገንጣይ ኃይሎች የሚደረገውን ድጋፍ ለመመርመር የተቋቋመ መሆኑን የጣሊያን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ የናዚ ፕሮፖጋንዳ ቁሶች እና መሳሪያዎች

እኚህ በሰሜን ዩክሬን ለመገንጠል የሚንቀሳቀሱ የሩሲያ አፍቃሪ የሆኑት ኃይሎች በሩሲያ መንግሥት ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ይገመታል።

ፖሊስ በቁጥጥር ሥር የዋለው ፈረንሳይ ሰራሽ ሚሳኤል በኳታር ጦር ውስጥ ጥቅም ላይ ከሚለው ሚሳዔል ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ፖሊስ ተናግሯል።

''በወረራው ወቅት የተያዘው ሚሳዔል እንከን የለሽ የሆነ እና በማንኛውም ሰዓት ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል የኳታር ጦር የሚጠቀመው አይነት ሚሳኤል ነው'' ይላል ፖሊስ ያወጣው መግለጫ።

ከሁለት ሳምንታት በፊት የጣሊያን ፍርድ ቤት በሩሲያ መንግሥት ከሚደገፉት ተገንጣይ ኃይሎች ጋር አብረው ሲዋጉ ነበሩ ያላቸውን ሶስት ዜጎቹ ላይ የእስር ብይን አስተላልፎ ነበር።

እአአ 2014 ጀምሮ በሩሲያ የሚደገፉት ተገንጣይ ኃይሎች የትጥቅ ትግል ከጀመሩ ወዲህ ከ10ሺህ በላይ ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል።