"ምርጫ ቦርድ ያላቸው ነገሮች ህጋዊ መሰረት የላቸውም" የህግ ባለሙያ

የሲዳማ ደስታ

በትናንትናው ዕለት ሐምሌ9፣2011ዓ.ም የሲዳማ ዞንን የክልልነት ጥያቄን ለመወሰን በአምስት ወራት ውስጥ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ወስኗል።

ከዚህም በተጨማሪ ከቦርዱ የሚጠበቁ ተግባራትንና ሂደቱ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም የሚጠበቅባቸውን ዝግጅት አስቀምጧል ምርጫ ቦርድ በመግለጫው።

መግለጫው ያስቀመጣቸው ነገሮች "ህጋዊ መሰረት የሌላቸው" ናቸው የሚሉት የህግ ባለሙያው አቶ አብርሃም ቃሬሶ ናቸው።

እንደ ምክንያትነት ከሚያነሷቸው ጉዳዮች መካከልም ምርጫ ቦርድ በአምስት ወራት ውስጥ ህዝበ ውሳኔ አካሂዳለሁ ማለቱ በህገ መንግሥቱ መሰረት የለውም ይላሉ።

በሲዳማ ክልልነት ጉዳይ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ የምርጫ ቦርድ ወሰነ

ለሲዳማ ክልልነት 'ይሁንታ ተሰጠ' በሚል በርካቶች ደስታቸውን እየገለጹ ነው

እሳቸው እንደሚሉት ምክንያቱም ህዝበ ውሳኔው መካሄድ ያለበት ክልል ለመሆን የሚጠይቀው ምክር ቤት በወሰነ በአንድ አመት ውስጥ ነው።

"ህገ መንግሥቱ እንደሚለው ምርጫ ቦርድ ያለው ስልጣን የህዝቡ ውሳኔ ነው አይደለም የሚለውን በህዝበ ውሳኔ እንዲያጣራ ብቻ ነው።" ይላሉ

'ከሕግ ውጪ' የተዋሃዱት አምስቱ ክልሎች

ከዚህ በተጨማሪ የህግ ባለሙያው ጥያቄ የሚያነሱበት ሌላኛው ጉዳይ የክልሉም የዞኑም አስተዳደር ዋና ከተማ ሆና የምታገለግለው የሀዋሳ ከተማ ህዝበ ውሳኔው የሲዳማን ክልልነት ካረጋገጠ፤ ሁለቱ አካላት የሚኖራቸውን መብትና፣ የሃብት ክፍፍል ጥያቄዎችን የሚያስተናግዱበት አሰራር አዘጋጅተው ለቦርዱ እንዲያሳውቁ የሚለው ነው።

"ምርጫ ቦርድ በዚህ ላይ ስልጣን የለውም፤ ምርጫ ቦርድ የተሰጠው ስልጣን የሲዳማ ህዝብ ክልል መሆን ይፈልጋል ወይስ አይፈልግም የሚለውን በህዝበ ውሳኔ ማጣራት ነው። እሱንም የደቡብ ክልል ማድረግ ስለማይችል እንዲደግፈው ነው" ይላሉ

በመግለጫው ላይ በሲዳማ ዞን የሚኖሩ የሌሎች ብሄር ብሔረሰብ አባላት ከህዝበ ውሳኔው በኋላ የሚኖራቸውን ህጋዊ የመብቶች ጥበቃ አስመልክቶ የደቡብ ክልል አስተዳደራዊና ህጋዊ ማእቀፍ በማዘጋጀት ለቦርዱ እንዲያሳውቅ የሚለውም የምርጫ ቦርድ ተግባር እንዳልሆነ የህግ ባለሙያው ያስረዳሉ።

"በመሰረቱ በሲዳማ ዞን እንደ ህዝብ የሚኖር ሌላ ብሄር የለም። ግለሰቦች ናቸው ያሉት። ነገር ግን ቢኖርም እንኳን በህጉ መሰረት ይህ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ አይደለም።መግለጫው ምርጫ ቦርድ ከተሰጠው ስልጣን በላይ የሌለውን ስልጣን መጠቀሙን የሚያመላክት ነው" በማለት ይደመድማሉ።

ፖለቲካዊ ውሳኔዎች የሚመለከቱት የደቡብ ምክር ቤትን ነው የሚሉት የህግ ባለሙያው የደቡብ ክልል አስፈፃሚዎችን እንጂ ምርጫ ቦርድን አይደለም።

ከዚህም በተጨማሪ የኤጀቶ አስተባባሪ ራሔል ኢሳያስ በበኩሏ በህግ ባለሙያው ሀሳብ ትስማማለች። ክልል የመሆን ጥያቄው ለዞኑ ከቀረበ አንድ አመት የሚሆነው ሐምሌ 11 ሲሆን ይህንንም ውሳኔ የሚመለከተው ምርጫ ቦርድን ሳይሆን ምክር ቤቱን ነው ትላለች።

"የክልል ጥያቄ ህገ መንግሥቱ እንደሚያዘው በምክር ቤቱ ከቀረበ በአንድ አመት ውስጥ ህዝበ ውሳኔ ተካሂዶ ምላሽ ማግኘት አለበት" ትላለች።

በዚህም መሰረት የሲዳማ ክልል መሆንን በነገው ዕለት ሐምሌ 11፣2011 ዓ.ም እንደሚያውጁ ለቢቢሲ ገልፃለች።

"አምስት ወር ጠብቁ የሚለውን ሐሳብ አንስማባትም፤ እነሱ ናቸው እንጂ ህጉን ያላከበሩት እኛ በህጉ መሰረት እየተመራን ነው" ትላለች።

የሲዳማ ህዝብ ራሱን ለማስተዳደር በብዙ አመታት በሰላማዊ መንገድ የታገሉ መሆናቸውን የምትናገረው ራሔል "እኛ ለውጥ አለ፣ዴሞክራሲ አለ ብለን ጥያቄያችንን በሰላማዊ መንገድ አቅርበናል። መንግሥትም እውነትም ዲሞክራሲ መኖሩን የተፃፈው ህግ እንደሚሰራ ያሳየን ነው የምለው። ሁከት አንፈልግም፤ አንድም ሰው እንዲሞት አንፈልግም" በማለት ገልፃለች።

ከምርጫ ቦርድ ጋር ተቃርኖ ወይም ከፌደራል መንግሥት ውጭ የሚሆን አይደለም ወይ በሚል ከቢቢሲ ለቀረበላት ጥያቄ "ከመንግሥት ጋር የሚያጋጭ ነገር ይኖራል ብለን አናስብም" ብላለች

የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሚሊዮን ማትዮስን በተደጋጋሚ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ተያያዥ ርዕሶች