ዮአኪን ''ኤል ቻፖ'' ጉዝማን የዕድሜ ልክ እስራት ተበየነበት

ኤል ቻፖ ጉዝማን Image copyright EPA
አጭር የምስል መግለጫ ዮአኪን ''ኤል ቻፖ'' ጉዝማን

የአሜሪካ ፍርድ ቤት ዕጽ አዘዋዋሪው ዮአኪን ''ኤል ቻፖ'' ጉዝማን ላይ የዕድሜ ልክ እስራት በየነ።

ከወራት በፊት በኒው ዮርክ የተሰየመው ፍርድ ቤት ኤል ቻፖ በዕጽ እና ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ጨምሮ በ10 ወንጀሎች ጥፋተኛ ሲል ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል።

ከዕድሜ ልክ እስሩ በተጨማሪ ኤል ቻፖ በሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ አጠቃቀም ወንጀል በሚል ተጨማሪ የ30 ዓመት እስር የተላለፈበት ሲሆን፤ 12.6 ቢሊየን ዶላር መቀጮ እንዲከፍልም ተፈርዶበታል።

አቃቤ ሕጎች ኤል ቻፖ የእስር ዘመኑን የሚያሳልፈው ከአርማታ ብረት ከሚወፍር ብረት በታጠረ እስር ቤት ውስጥ ነው በማለት ከአሜሪካ እስር ቤት ማምለጥ እንደማይችል ጠቁመዋል።

ኤል ቻፖ ከሜክሲኮ ወደ አሜሪካ ተላልፎ ከመሰጠቱ በፊት ከፍተኛ ጥበቃ ከሚደረግላቸው ሁለት የሜክሲኮ እስር ቤቶች ማምለጡ የሚታወስ ነው።

በችሎት አደባባይ የወጣው የኤል ቻፖ ገመና

ኢትዮጵያዊቷ የዕፅ ነጋዴው ኤል ቻፖን ጉዳይ ለመዳኘት ተመረጠች

በድጋሚ ታህሣሥ 2008 በቁጥጥር ሥር የዋለው ኤል ቻፖ 2009 ላይ ለአሜሪካ ተላልፎ ተሰጥቷል።

ኤል ቻፖ ይመራው የነበረው ሲናሎዋ የተባለው የእጽ አዘዋዋሪ ቡድን ወደ አሜሪካ ለሚገቡ ዕፆች ተጠያቂ ይደረጋል።

ትናንት የፍርድ ውሳኔው ከመተላለፉ በፊት ዮአኪን ኤል ቻፖ ጉዝማን የእስር ክፍል በፍጹም ምቹ አለመሆኑን እና ''ስቃይ'' እንደሆነበት ለፍርድ ቤቱ በአስተርጓሚ ተናግሯል።

''ኤል ቻፖ'' በሳምንት ለሁለት ሰዓታት ከእስር ክፍሉ ውጪ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ያቀረበው ጥያቄ ከሳምንታት በፊት በኒው ዮርክ ፍርድ ቤት ዳኛ ውድቅ ተደርጎ ነበር።

ዳኛው ኤል ቻፖ ይህን ምክንያት ያመጣው ከእስር ለማምለጥ አስቦ ነው ሲሉ ተከራክረዋል።

ኤል ቻፖ ከእስር ክፍሉ መውጣት አይችልም

ትናንት ኤል ቻፖ ላይ የተላለፈውን የፍርድ ውሳኔውን በመቃወም ይግባኝ እንደሚጠይቁ ጠበቆቹ ተናግረዋል።

ጠበቃ ጄፈሪ ሊችትማን ዳኞቹ በመገናኛ ብዙሃን ዘገባ ምክንያት ጫና ስር ወድቀው ነው ይህን አግባብ ያልሆነ ፍርድ የሰጡት ብለዋል።

Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ በጉዝማን (ቀኝ) እና የቀድሞ አጋሩ

እድሜያቸው እስከ 13 ዓመት ድረስ የሚገመቱ ሴት ህጻናት ልጆችን በዕጽ ራሳቸውን እንዲስቱ ካደረገ በኋላ ደፈሯል የሚል ክስ የቀረበበት ሲሆን፤ አንድ የዓይን እማኝ ደግሞ ጉዝማን ሶስት ሰዎችን ተኩሶ ሲገድል አይቸዋለሁ ሲል መስክሯል።

ተቀናቃኝ የዕጽ አዘዋዋሪ ቡድንን የተቀላቀሉ ሁለት የቀድሞ ባልደረቦቹን ከደበደበ በኋላ በጥይት መትቶ በመግደል አስክሬናቸው በእሳት እንዲቃጠል አድርጓል ሲል የቀድሞ የግል ጠባቂው ኤል ቻፖ ላይ መስክሯል።

ዮአኪን ኤል ቻፖ ጉዝማን ትናንት ወደ ፍርድ ቤቱ ክፍል ሲገባ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ምን ሊሆን እንደሚችል ያወቀው ይመስላል ስትል የፍርድ ሂደቱን የተከታተለችው የቢቢሲዋ ጋዜጠኛ ናዳ ታዋፊክ ትናገራለች።

ኤል ቻፖ የፍርድ ሂደቱን ከመከታተል ይልቅ ትኩረቱ የነበረው ባለቤቱ ላይ እና የቤተሰብ አባላቱ ላይ ነበር። ከተቀመጠበት ሆኖ ጣቶቹን እየሳመ ወደ ሚስቱ እና ቤተሰቡ የሰላምታ መልዕክት ያሳይ ነበር።

Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ የኤል ቻፖ ባለቤት ኤማ ኮርኔል የፍርድ ሂደቱን ተከታትላለች

ኤል ቻፖ ጉዝማን ማነው?

"ኤል ቻፖ'' ማለት ''አጭሩ'' እንደማለት ሲሆን በሰሜናዊ ሜክሲኮ ሲናሎአ የተሰኘ የዕፅ አዘዋዋሪ ቡድን መሪ ነበረ።

ኤል ቻፖ የሚመራው ቡድን ወደ አሜሪካ ለሚላከው ዕፅ ትልቁን ድርሻ ይዞ ነበር። እአአ 2009 ፎርብስ ኤል ቻፖ ጉዝማን የተጣራ 1ቢሊዮን ዶላር ያስመዘገበ ከበርቴ ነው በማለት የዓለማችን 701ኛው በማለት የሃብታሞች ዝርዝር ውስጥ አካቶታል።

የፍርድ ሂደቱ ተደብቆ የቆየውን የኤል ቻፖ ጉዝማን ህይወትን አደባባይ ያወጣ እንደሆነ በርካቶች ይስማማሉ። በፍርድ ሂደቱ ላይ የቀድሞ የቅርብ አጋሩ የነበሩ ሁሉ መስክረውበታል።

ጉዝማን ለቀድሞው የሜክሲኮ ርዕሰ ብሔር ኤንሪክ ፔና ኒቶ በ2012 ስልጠን ከያዙ በኋላ እርሱ ላይ የሚደረገው ክትትል እንዲቆም በመጠየቅ አንድ መቶ ሚሊየን ዶላር ጉቦ መክፈሉም የተሰማው ችሎት ላይ ነበር።

ርዕሰ ብሔሩ ግን ይህ ውንጀላ እውነትነት የለውም ሲሉ አስተባብለዋል።

ገድሎ ያቃጠላቸው የአደንዛዥ ዕፅ ከበርቴ ተፎካካሪዎች እንዳሉ ከዘመዶቹ መካከልም የገደላቸው እንዳሉ ተገምቷል።

ችሎቱ ኤል ቻፖ በ2015 በሜክሲኮ እጅግ ጥብቅ ከሆነው እስር ቤት እንዴት እንዳመለጠም በዝርዝር አድምጧል። ልጁ በእስር ቤቱ አቅራቢያ የሚገኝ ቤት እንደገዛ እና ጂፒኤስ ያለው ሰዓት ወደ እስር ቤቱ በድብቅ ማስገባቱ ተመስክሯል።

በሚስቱ እና በቅምጦቹ ላይ ለመሰለል በስልኩ ላይ ሶፍትዌር ይጠቀም እንደነበርም ተመስክሮ፤ ኤፍ ቢ አይ የተለዋወጣቸውን የፅሑፍ እንዲያቀርብ ተደርጓል።

በአንድ የፅሁፍ መልዕክቱ ላይም ከነበረበት ቤት አሜሪካዊያንና ሜክሲኳዊያን ከከፈቱበት ድንገተኛ ዘመቻ እንዴት እንዳመለጠ የሚገልጽና ልብስ እና ጫማ እንዲመጣለት የጠየቀበት መልዕክቱም ተነቧል።

ጉዝማን በአሜሪካ የፍትህ አደባባይ ለፍርድ ከቀረቡ የሜክሲኮ የአደንዛዥ ዕፅ ከበርቴዎች መካከል ትልቁ ነው።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ