ስጋት ያጠላበት የሲዳማ የክልልነት ጥያቄና የሀዋሳ ክራሞት

የሲዳማ ወጣት

ሰኞ ሐምሌ 8/2011 ዓ.ም ጠዋት አራት ሰዓት አካባቢ የሞተር ሳይክል ጡሩንባ በከተማዋ መስተጋባት ጀመረ። በደስታ የሚጨፍሩ ወጣት ወንድና ሴቶች በቡድን ሆነው በመሃል ሐዋሳ ውስጥ በብዛት መታየት ጀመሩ።

በተለይ አቶቴ ተብሎ በሚታወቀውና በርካታ የሲዳማ ብሔር አባላት የሚኖሩበት የሐዋሳ ክፍል የፈንጠዝያው ማዕከል ነበር።

በከባድ መኪኖች ላይ እየተጫኑ ወደ ስፍራው የሚያመጡ ሰዎች ቁጥሩ እየጨመረ እንዲመጣ አደረገው። በቡድን የተሰባሰቡ ሰዎች ደስታቸውን ለመግለጽ ከሐይማኖታዊ ዜማዎች ጋር የተቀላቀሉ የተለያዩ ዘፈኖችን ያሰሙ ነበር።

በተሰበሰቡት ሰዎች በብዛት ሲዜሙ ከነበሩት መዝሙሮች መካከል በሲዳማ ቋንቋ የእግዚአብሔርን ኃይል የሚያመለክቱ በሲዳምኛና በአማርኛ "አሁን ምን ይላል ጠላቴ" እንዲሁም "ጠላት አይኑ እያየ ጆሮው እየሰማ" የሚሉት መዝሙሮች ደስታቸውን ለማድመቅ ሲያዜሙ ነበር።

አንዳንዶች "የሲዳማ ክልላዊ መንግሥት" የሚል ጽሁፍ የሰፈረባቸውን ከናቴራዎች ደስታቸውን ለሚገልጹት ሰዎች ሲሸጡ፤ ሌሎች ከደስታቸው ብዛት በመንገድ ላይ ያገኙትን ሁሉ እያቀፉ 'እንኳን ደስ አላችሁ' ሲሉ ነበር።

ይህ የደስታ ስሜት በከተማዋ ውስጥ የተፈጠረው የክልሉ ገዢ ፓርቲ ደኢህዴን የሲዳማ ዞን ራሷን የቻለች ክልል እንድትሆን ከሚያስችል ውሳኔ ላይ ደርሷል የሚል ወሬ በመሰማቱ ነበር። ምንም እንኳን የዚህን ወሬ እውነተኛነት የሚያረጋግጥ ከሚመለከተው አካል የተገኘ ማረጋገጫ ባይኖርም ጥያቄው ክልል በመሆን ምላሽ እንደሚያገኝ እምነት ነበራቸው።

ነገር ግን ምንም ሳይሰማ ቀኑ አለፈ። በቀጣዩ ቀን ሐዋሳ በእርግጠኝነትና ግራ በመጋባት ውስጥ ስትዋልል ዋለች። የሰኞ እለቱ የአደባባይ ፈንጠዝያ ማክሰኞ እለት ጉዱማሌ በሚባለው ቦታ ላይ በተደረጉ ስብሰባዎች ተተካ። ስብሰባዎቹም የሚጠበቀው ምላሽን የበለጠ እንዲጠበቅ አደረገው።

ከዚያም በተከታታይ ከደኢህዴን፣ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድና ከሲዳማ ዞን አስተዳደር ጉዳዩን በተመለከተ የተሰጡት መግለጫዎች ከፍ ብሎ የነበረውን የደስታ ስሜት ቀዝቀዝ እንዲል አደረጉት።

ስጋትና ውጥረት

በእርግጥም የሲዳማ ክልል የመሆን ነገር ተቀባይነት አግኝቷል የተባለው ወሬ ከተሰማ በኋላ ባሉት ቀናት የተስተዋለው የደስታ ጭፈራና መዝሙር ብቻ አልነበረም።

ቀይ ቆብ ያጠለቁ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በክፍት መኪኖች ላይ ሆነው የከተማዋን ዋና ዋና አካባቢዎች እየተዘዋወሩ ይቃኙ ነበር።

ይህም የሲዳማ ብሔር የመብት ተከራካሪዎች ሐምሌ 11 ያለማንም ፈቃድ ክልል የመሆን ጥያቄያቸውን ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ካሳወቁ በኋላ በሕብረ ብሔሯ ከተማ ሐዋሳ ላይ ውጥረት መንገሱን የሚያመለክት ነው።

የሲዳማ ብሔር አባል ያልሆነ አንድ የከተማዋ ነዋሪ ለቢቢሲ እንደተናገረው የወታደሮቹ በከተማዋ ውስጥ መሰማራት ደህንነት እንዲሰማኝ አድርጎኛል ይላል። "እውነቱን ለመናገር መጥፎ ነገር ቢከሰት በክልሉ ፖሊስ ላይ እምነት የለኝም" ሲል ያክላል።

ለዚህም አባባሉ ከዓመት በፊት በከተማዋ ተከስቶ የበርካታ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈውን የብሔር ግጭት እንደ ምሳሌ ይጠቅሳል።

ነገር ግን የሲዳማ ብሔር መብት አቀንቃኞች አንዳንዶች እንደሚሰጉት አዲስ ክልል ሲመሰረት ማንነትን መሰረት ያደረገ መድልኦ ወይም ጥቃት ሲዳማ ባልሆኑት ላይ ሊከሰት ይችላል የሚለውን ጥርጣሬ አጥብቀው ይቃወሙታል።

"የሲዳማን ሕዝብ ትግል ለማጠልሸት የሚደረጉ ቅስቀሳዎች አሉ" ሲሉ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህግ ረዳት ፕሮፌሰርና የመብት ተከራካሪ የሆኑት ተሰማ ኤሊያስ ለቢቢሲ ተናግረዋል። "ከዚህም መካከል ሌሎች ብሔሮችን በተለየ ሁኔታ ሊታዩ ይችላሉ የሚለው አንዱ ነው።"

አንዳንድ ምንጮች እንደሚሉት የሲዳማ ክልል ሲመሰረት ከሌሎች ማህበረሰቦች ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት፣ ስለሐዋሳ ከተማና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ እቅዶችን የሚያወጣና የሚመራ ግብረ ኃይል ታዋቂ ሰዎችን አካቶ እየሰራ መሆኑ ይነገራል። የደረሰበትንም ከሐምሌ 19 በፊት ለምርጫ ያቀርባል ተብሎም ይጠበቃል።

እምነት ማጣት

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሲዳማ መብት ተከራካሪዎችና ኤጀቶ የተባለው የሲዳማ ወጣቶች ስብስብ አባል ነን የሚሉ ሰዎች በሁኔታው እንዳዘኑና በክልሉ ገዢ ፓርቲን ደኢህዴን ላይ እምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል።

አንዳንዶቹ እንዲያውም የሲዳማን ክልል የመሆን ጥያቄ ፓርቲው ሲያደናቅፍ ቆይቷል በሚል ጣታቸውን ይቀስራሉ። "ደኢህዴን የሲዳማን ጥያቄ ለማስተናገድ ቁርጠኛ አይደለም። ሕዝበ ውሳኔው እንዲካሄድ ጠንክረው አልገፉም" ስትል ለቢቢሲ የተናገረችው ለምለም ጸጋዬ ናት። "ለዚህም ነው እንዲህ አይነት ችግር ውስጥ የገባነው።"

አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞችና ታዛቢዎች እንደሚሉት የሲዳማ ክልል የመሆን ጥያቄ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ውስብስብ የፖለቲካ ችግር ላይ ተጨማሪ ሸክም ነው ይላሉ።

በዓለም ዙሪያ የሚያጋጥሙ ቀውሶችን የሚከታተለው የኢንትርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ የኢትዮጵያ ተንታኝ የሆነው ዊሊያም ዳቪሰን እንደሚለው በርካታ ብሔሮች ክልል የመሆን ጥያቄ ባቀረቡበት የደቡብ ክልል ውስጥ ያለው ችግር እጅግ ስር የሰደደ ነው።

"ይህም መንግሥት ለመወሰን እንዲቸገር ካደረጉት ነገሮች መካከል ዋነኛው ነው። የሲዳማን ክልል የመሆን ጥያቄ ቢቀበል ቀጥሎ ምን ይከሰታል?" ሲል ይጠይቃል ዳቪሰን ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ። "የቀሩትን የዘጠኝ ብሔሮች ጥያቄ ይቀበላሉ? ካልተቀበሉ ሌሎቹ ምን ይላሉ? ከተቀበሉትስ ቀጥሎ የሚመጡ ክልል የመሆን ጥያቄዎችን ይቀበላሉ?"

የመብት ተከራካሪው ተሰማ ከሲዳማ ሌላ ክልል የመሆን ጥያቄ ያቀረቡትን ቡድኖች በሙሉ ይደግፋል። ነገር ግን አነዚህ ጥያቄዎች እንዲነሱ የተደረገው የሲዳማን ጥያቄ ለማፈን ነው ሲል ለዚህም የክልሉን ገዢ ፓርቲ ይከሳል። "ይህ ካልሆነ ታዲያ እነዚህ ጥያቄዎች እስካሁን የት ነበሩ?" ሲል ይጠይቃል።

ከዚህ ሁሉ ደስታና ግራ መጋባት በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው መግለጫ የሲዳማን ክልልነት ለመወሰን የሚያስችል ሕዝበ ውሳኔ በወራት ውስጥ እንደሚያካሂድ አስታወቋል።

መግለጫውን ተከትሎ አንድ ወጣት ለቢቢሲ "ጥቂት ወራትን ለመታገስ ችግር የለብኝም" ካለ በኋላ ስጋቱን ይገልጻል። "ነገር ግን እኔ የምፈራው፤ ጥያቄያችን ከእጃችን ተነጥቆ ቢወሰድስ?"