አቶ ቶማስ ታማ፡ «እኔ አዞዎችን እንደቤት እንሰሳ ነው የማያቸው»

አቶ ቶማስ ታማ

ቶማስ ታማ ይባላሉ፤ የአርባምንጭ ከተማ ነዋሪ ናቸው። አዞ ማለት ለእርሳቸው የቤት እንሰሳ ነው። ለአዞ ፍቅር አላቸው፤ አዞዎችም ያውቋቸዋል፤ ይወዷቸዋል።

ለኢትዮጵያ ብርቅዬ የሆነው የአርባምንጭ አዞ እርባታ ጣብያ የተመሠረተው በ1976 ነው፤ አቶ ቶማስ ድርጅቱን የተቀላቀሉት ደግሞ 1981 ላይ፣ ድርጅቱ ገና የአምስት ዓመት ታዳጊ ሳለ ነበር። የእርባታ ጣብያው መመሥረት ዋነኛ ዓላማ በሕገ-ወጥ መንገድ አዞ እየገደሉ ቆዳ እና ስጋውን የሚሸጡ ሰዎችን ለመከላከልና በሕጋዊ መንገድ የአርባንምጭ አዞን ለመጠበቅ ነበር።

ምንም እንኳ አሁን አሁን የአዞ ገበያ ቢቀዛቃዝም የአዞ እርባታ ጣብያው ሌላኛው ዓለም የውጭ ምንዛሪ ማስገኘትም ነበር፤ ከጉብኝት የሚገኘው ገቢ ሳይረሳ።

የኢትዮጵያ አዞ ቆዳና ሥጋ ገበያ አጥቷል

«81 ታኅሳስ ላይ ነበር መጀመሪያ በጊዜያዊነት የተቀጠርኩት። ከዚያ 1993 ላይ በቋሚነት ተቀጠርኩ፤ ይኸው እስከዛሬ በተለያዩ ዘርፎች እያገለገልኩ አለሁኝ » ይላሉ አቶ ቶማስ፤ ጣብያውን የተቀላቀሉበትን ጊዜ ሲያስታውሱ።

ታድያ በእነዚህ 30 ዓመታት አቶ ቶማስ በአዞ እርባታ ጣብያው ያላዩት ጉድ የለም። ከአዞ ጋር ውሎ ማምሸት ምን ይመስላል?

«እጅግ በጣም ደስ ይላል። ከተፈጥሮ ጋር ኑሮ እጅግ ማራኪ ነው። እርግጥ ነው መጀመሪያ ላይ በጣም አስፈሪ ነበር። ኋላ ላይ ግን እየለመድነው መጣን። አሁን ሰዉ ከኦዘዎች ጋር ተስማምተን ሲያየን ይገረማል፤ ወይም ፍራቻ ያድርበታል፤ ነገር ግን እኛ ከአዞዎች ጋር ያለን ቁርኝት ደስታ ይሰጠናል።»

«እኔ አዞዎችን እንደቤት እንሰሳ ነው የማያቸው»

በጣም ከሚፈሩና የከፋ አደጋ ማድረስ ከሚችሉ የውሃ ውስጥ እንስሳት አዞ አንዱ መሆኑን መናገራችን አዲስ ነገር የፈጠረን ላያስመስለን ይችል ይሆናል። አዞ የቤት እንሰሳ መሆን ይችላል ብለን አፍ ሞልተን ማውራቱም አያዋጣንም። አቶ ቶማስ ግን ይላሉ. . . «አዞ እንደቤት እንሰሳ ነው።»

ወንዶች አዞ ለመምሰል ቆዳቸውን የሚበሱባት ሃገር

«ሰዎች ሁሌም የሚሉን ነገር ቢኖር አዞ እኮ ጨካኝ ነው። እንዴት ከአዞ ጋር ትሠራላችሁ ነው። እኔን ጨምሮ እዚህ 'ራንች' ውስጥ ለምንሠራ ሠራተኞች ግን አዞ እንደቤት እንሰሳ ነው። እየተንከባከብን ስለምናሳድጋቸው፤ ቀናቸውን ከእኛ ጋር ስለሚያሳልፉ በጣም ይለምዱናል፤ ልክ እንደቤት እንሰሳ። በጣም የሚቀርቡና ፍቅር ያላቸው ናቸው።»

አርባምንጭ አዞ እርባታ ውስጥ የሚገኙ አዞዎች ገና ከእንቁላላቸው እንተደፈለፈሉ ነው ወደ መጠበቂያ ጣብያው የሚመጡት። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የሚያስፈልጋቸው እንክብካቤ እየተደረገላቸው እንደ እድሜያቸው በመከፋፈል አንድ ላይ እንዲያድጉ ይደረጋሉ።

አቶ ቶማስ እና ባልደረቦቻቸውም አዞዎቹን ከጨቅላ ዕድሜያቸው ጀምሮ ነው የሚያውቋቸው፤ አዞዎቹም እንዲሁ።

«ስጋዬ ተቦጭቆ ሆስፒታል ገብቼ ነበር»

ጊዜው 1989፤ የዚያኔ አዞ እርባታው አሁን ከሠፈረበት አካባቢ ፈንጠር ብሎ የሚገኝ ቦታ ላይ ነበር የተገነባው። የቀድሞው ሥፍራ የአዞዎች ሰፊ መኖሪያ ለሆነው የአባያ ሐይቅ እጅጉን የቀረበ ነበር።

ታድያ ክረምት ሲገባ በአዞ እርባታ ታላቅ ሰቀቀን ይሰፍናል፤ አባያ ሐይቅ እየሞላ የአዞዎቹን ገንዳ ይጎበኛል። አንዳንዴም ሞልቶ ሲፈስ አጋጣሚውን የተጠቀሙ አዞዎች ወደ ጥልቁ ሐይቅ ይጠልቃሉ።

«. . . እና ሐይቁ ሲሞላና ግቢውን ሲያጥለቀልቀው በጀልባ እየቀዘፍን ነበር የምንሠራው። ያኔ እኔ የአዞዎቹን ውሃ እየቀየርኩ ነበር። የቀድሞው ግቢ ሰው እንዲረማመድበት ተብሎ የተሠራ የእንጨት ድልድይ ነበር። ከድልድዩ ላይ ወደነሱ ለመውረድ ቀኝ እግሬን ስሰድ ከሥር ተደብቆ የነበረ አንድ አዞ ዘሎ ያዘኝ። ይሄኔ በድንጋጤ እግሬን ብድግ ሳደርግ እግሬን እንደያዘ ተነሳና ስጋዬን ቦጭቆ ጣለው። ከዚያ ስጮህ የሰሙ ጓደኞቼ መጥተው በጨርቅ ጉዳት የደረሰበትን ቦታ ጠምጥመው ወደ ሆስፒታል ወሰዱኝ።»

«ከፍተኛ ጉዳት ነበር የደረሰብኝ። እርግጥ ነው አጥንቴ አልተነካም ግን ከጉልበቴ በታች ስጋዬን ቦጭቆብኛል።»

እና ተመልሰው ወደ አዞዎች ጋር መጠጋት አላስፈራዎትም?

«ሰፈር ውስጥ ያሉ ሰዎች፣ ጎረቤቶችም እንደዛ ነበር ያሉኝ፤ 'ሁለተኛ ይሄን ሥራ ብለህ ወደ እርባታ ጣብያው እንዳትመለስ፤ ሕይወትህን ሁላ ልታጣ ትችላለህ' ነበር ያሉኝ። ቢሆንም ቁስሉ ሲሽርልኝ ተመልሼ መጣሁ።»

የአዞ ስጋ

እርግጥ ኢትዮጵያ በርካታ ሥፍራዎች የአዞ ስጋ መመገብ ከባሕል እንደማንፈንገጥ ይቆጠር እንጂ ሌሎች ሀገራት በሰልፍ እንኳ የማይገኝ ምግብ መሆኑን ሰምተናል። ቅርጥፍ አድርገው የበሉም ሞልተዋል።

ለአቶ ቶማስ፤ የአዞ ስጋ ቀምሰው ያውቃሉ? የሚል ጥያቄ ስናቀርብላቸው በፈገግታ በመታጀብ ነበር የመለሱልን።

«እንግዲህ በኃይማኖታችንም ይሁን በባሕል የአዞ ስጋ መብላት ብዙ አይመከረም። ቢሆንም እኔ ቀምሼ አውቃለሁ። ያው ጣዕሙ እንደ ዓሳ ነው፤ በተለይ ተጠብሶ በጥሩ ሁኔታ ሲቀርብ። መልኩም ቢሆን ነጣ ያለ ነው። ግን ጥርስ ላይ ትንሽ ጠንከር ይላል። በጥሩ ሁኔታ ከተሠራ ይጣፍጣል። እና ቀምሻለሁ ውሸት መናገር አያስፈልግም. . .[ሳቅ]»

ከእርሳቸውና ባልደረቦቻቸው ውጭ ወደ ጣብያው ለጉብኝት የሚመጡ ኢትዮጵያውያን የአዞ ስጋ ለመብላት እንደማይደፍሩ አቶ ቶማስ ሹክ ብለውናል።

ነገር ግን በዓላትን አስታከው የሚመጡ የውጭ ሃገር ዜጎች፤ በተለይ ደግሞ ቻይናውይንና እና ጣልያናውያን አልፎ አልፎ መጥተው አዞ ገዝተው ካስበለቱ በኋላ ስጋውን አስጠብሰው እንደሚመገቡ አልደበቁንም።

አንድ ጫማውን ለአዞ የገበረው ጎብኝ

ክብሩ ይስፋ በጎብኝዎች አካል ላይ የደረሰ ጉዳት እኔ እስካማስታውሰው ድረስ አጋጥሞ አያውቅም ይላሉ አቶ ቶማስ። ነገር ግን አንዳንድ ዕቃዎች ከእጃቸው ከወደቁ የመመለሳቸው ዕድል ኢምንት መሆኑን ነግረውናል።

«ለምሳሌ አንድ ጎብኝ አንድ ጊዜ ኦዞዎቹ ሲንቀሳቀሱ ማየት ፈልጎ እግሩን ሲያወዛውዝ ጫማው ወደ ገንዳው ውስጥ ይወድቅበታል። ይሄኔ ኦዘዎቹ ተረባርበው ጫማውን ይዘው ውሃው ውስጥ ገቡ። አንድ ነገር ከያዙ ደግሞ አይለቁም። እና ጎብኚው በአንድ እግር ጫማ መመለሱን አልረሳም [ፈገግ]።»

«ከዚህ ውጭ ተንቀሳቃሽ ስልኮች እና ካሜራዎች ወድቀውባቸው ከጥቅም ውጭ የሆኑባቸው ጎብኝዎች አውቃለሁ። አንድ ጎብኝ ደግሞ ሸሚዙን አውልቆ ሲያውለበልብ ዘለው ነጥቀውታል። ምንም እንኳ እኛ ጎብኝዎች እነዚህን ነገሮች እንዳያደርጉ በፅሑፍም በቃልም ብናስጠነቅቅም።»

ታድያ የአቶ ቶማስ ሥራ አዞዎችን መንከባከብ ብቻ አይደለም። ለእርድ የደረሱ አዞዎችን አርዶ መበለትንም ተክነውበታል። የአዞ ቆዳን ፍቆ በጨው ዘፍዝፎ ለጥቅም እንዲውል ማድረግም ጥርሳቸውን የነቀሉበት ሙያ ነው።

አቶ ቶማስ የስድስት ልጆች አባት ናቸው። ከአዞ መንጋ ጋር ተጋፍጠው በሚያገኙት ገቢ ቤተሰቦቻቸውን ያስተዳድራሉ። ጎብኝዎች አቶ ቶማስና ባልደረቦቻቸው ከአዞዎች ጋር እየተጋፉ ገንዳ ሲያፀዱ እና ሲንከባከቡ ሲመለከቱ በአድናቆት ይመለከታሉ። አቶ ቶማስ ግን ከቤት እንሰሳዎቻቸው ጋር በፍቅር 30 ዓመት ኖረዋል። ታድያ ይህ ፍቅራቸው በቅርቡ የሚያበቃም አይመስልም።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ