'ፌስአፕ'ን እንመነው?

ፌስአፕን በመጠቀም ሲያረጁ ምን እንደሚመስሉ ማወቅ ይቻላል? Image copyright FaceApp

ሲያረጁ ምን እንደሚመስሉ ማወቅ ይፈልጋሉ? እንግዲያውስ 'ፌስአፕ' የተባለውን መተግበሪያ ይሞክሩ። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ምን አይነት ገጽታ እንደሚኖርዎ ያሳይዎታል።

ፌስአፕ የሰሞነኛ መነጋገሪያ ሆኗል።

ብዙ ሺዎች የወጣትነት ፎቷቸውን እና ፌስአፕ 'ስታረጁ ይህን ትመስላላችሁ' ያላቸውን ፎቶ እያጣመሩ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተጋሩ ነው።

ፌስአፕ እድሜዎ ሲገፋ ምን እንደሚመስሉ ከማሳየት ባለፈ ብዙ ጣጣ ይዞ የሚመጣ መተግበሪያ ነው የሚሉም አልታጡም። መተግበሪያው ለግላዊ መረጃ ምዝበራ ይውል ይሆን? የሚል ስጋትም አለ።

የሰዎችን ማንነት የሚለየው ቴክኖሎጂ እያከራከረ ነው

ፌስአፕ የተጠቃሚዎችን የግል መረጃ እንደማይወስድና ጥቅም ላይ የሚያውለው ፎቶም በተጠቃሚዎች የተመረጠውን ብቻ እንደሆነ ገልጿል። ሰዎች ለአርትኦት (ኤዲት እንዲደረግ) ከመረጡት ፎቶ ውጪ ሌላ ፎቶ ከስልካቸው እንደማይወስድና የተጠቃሚዎችን ፎቶ በ48 ሰዓት ውስጥ ከክምችት ክፍሉ እንደሚያጠፋም ይፋ አድርጓል።

ለመሆኑ ፌስአፕ ምንድን ነው?

ፌስአፕ ገናና የሆነው ከሁለት ዓመት በፊት ነበር። በወቅቱ መተግበሪያው የሰዎችን የቆዳ ቀለም በመቀየር ፎቶ በማቀናበሩ ሲወቀስ ነበር።

ፌስአፕ አንድ ፎቶን ይወስድና በፈለጉት መንገድ ያቀናብራል። ፌስአፕ ማንኛውም ፎቶ ላይ መጨመር የሚፈልጉትን ነገር ያክላል።

አይን፣ ቅንድብ፣ አፍንጫ፣ ከንፈር. . . የትኛውም የሰውነት አካል በፌስአፕ እንደየአስፈላጊነቱ ሊቀየር ይችላል።

ፌስአፕ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ኤአይ) በመጠቀም፤ ፊታቸው ላይ ምንም ስሜት የማይነበብባቸው ሰዎች ፈገግ ያሉ ያስመስላል። የሰዎች ፎቶ ላይ መዋዋቢያ በመጨመር ማቀናበርም ይቻላል።

Image copyright Olly Gibbs
አጭር የምስል መግለጫ መተግበሪያው ለሰው ብቻ ሳይሆን ለስዕልም ይውላል

ታድያ ችግሩ ምንድንነው?

መተግበሪያውን የሠራው ጆሽዋ ኖዚ ይባላል። ፌስአፕ ተጠቃሚዎች ስልክ ውስጥ ያሉ ፎቶዎችን ያለፍቃድ እንደሚወስድ ሲናገር ነበር ብዙዎች መደናገጥ የጀመሩት።

በቴክኖሎጂ ኢ-ፍትሐዊነትን የምትታገለው ኢትዮጵያዊት

ሆኖም አንድ የፈረንሳይ የመረጃ ደህንነት ተመራማሪ በሠራው ጥናት መሰረት፤ ፌስአፕ ተጠቃሚዎች ከመረጡት ፎቶ ውጪ ሌሎች ፎቶዎችን መውሰድ እንደማይችል ገልጾ ነበር።

ፌስአፕ ለቢቢሲ እንደተናገረውም፤ መተግበሪያው መውሰድ የሚችለው በተጠቃሚዎች ለአርትኦት የተሰጠውን ፎቶ ብቻ ነው።

ከዚህ በተቃራኒው ፌስአፕ የሰዎችን ፎቶዎች በመውሰድ ለ 'ፌሻል ሪኮግኒሽን' እንደሚያውል የሚያምኑ በርካቶች ናቸው። የ 'ፌስ ሪኮግኒሽን' ቴክኖሎጂ በአንድ ምስል ወይም ቪድዮ ላይ ያሉ ሰዎችን ማንነት የሚለይ ነው።

የፌስአፕ ሊቀ መንበር ዮርስላቭ ጎንቻሮቭ ለቢቢሲ "ፎቶዎችን ለፌስ ሬኮግኒሽን አንጠቀምም፤ ፎቶዎች ላይ የአርትኦት ሥራ ብቻ እንሠራለን" ብለዋል።

እና ፌስአፕን እንመነው?

አንዳንዶች ፌስአፕ የሰዎች ፎቶ ላይ አርትኦት ለመሥራት ፎቶዎቹን መጫን ብቻ ሲያስፈልገው፤ ለምን ፎቶውን ወደ 'ክላውድ' መውሰድ አስፈለገው ብለው ይጠይቃሉ።

ፌስአፕ የሩስያ ድርጅት ነው። የሰዎችን ፎቶ የሚያቆይበት ቅርጫፉ ግን መቀመጫውን አሜሪካ አድርጓል።

ሞና ሊሳ "ነፍስ ዘራች"

ተጠቃሚዎች ምን እየተከናወነ እንደሆነ ያውቃሉ?

አሜሪካዊቷ ጠበቃ ኤልዛቤት ፖትስ ዋይንስቲን፤ መተግበሪያው የተጠቃሚዎችን ፎቶዎች ለንግድ ሊያውል እንደሚችል ይገልጻል ይላሉ። ለምሳሌ የአንድ ሰው ፎቶግራፍ ፌስአፕን ለማስተዋወቅ ሊውል ይችላል።

የግለ መረጃ ጥበቃ ባለሙያ ፓት ዋልሽ እንደሚሉት፤ ፌስአፕ የሰዎችን ፎቶዎች ለማስታወቂያ ግብአትነት ሊያውል ይችላል። "ሆኖም ግን ለተጠቃሚዎች ግልጽ መረጃ አይሰጥም፤ ተጠቃሚዎች በምርጫቸው ውሳኔ እንዲያስተላልፉም እድል አይሰጥም" ይላሉ።

አምስቱ የአፍሪካ ቴክኖሎጂ ጎዳናዎች በ2018

የፌስአፕ ሊቀ መንበር ዮርስላቭ ጎንቻሮቭ በበኩላቸው፤ ፌስአፕ የተጠቃሚዎችን ፎቶግራፍ ለማስታወቂያ ድርጅቶች አሳልፎ አይሰጥም ይላሉ። መተግበሪያውን ለመጠቀም ከተመዘገቡ ሰዎች በሚያገኘው ክፍያ ገቢ እንደሚሰበስብም አክለዋል።

ሊቀ መንበሩ ፌስአፕ የሰዎችን ፎቶ 'ክላውድ' ላይ የሚያስቀምጠው ተጠቃሚዎቹ ፎቶዎችን በተደጋጋሚ እንዳይጭኑ ለማድረግ ነው ይላሉ። በ48 ሰዓት ፎቶዎቹን እንደሚያጠፏቸውና የተጠቃሚዎች መረጃ ወደ ሩስያ እንደማይወሰድ ያስረግጣሉ።