ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአሥመራ ጎዳናዎች ላይ መኪና ሲያሽከረክሩ ታይተዋል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ እና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ Image copyright Yemane G. Meskel

ለጉብኝት ወደ ኤርትራ የተጓዙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ መኪና እያሽከረከሩ ከኤርትራው ፕሬስዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የሚታዩበት ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ መነጋገሪያ ሆኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ መኪና እያሽከረከሩ ከውጪ ሃገር መሪ ጋር ሲታዩ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም። ባለፈው ዓመትም የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ልዑል ሞሐመድ ቢን ዛይድ ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መኪና እያሽረከሩ ታይተዋል።

የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት ኢኮኖሚያዊ ትርፍ?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በሁለቱ ሃገራትና በአካባቢያዊ ጉዳዮች ለመመካከር ለሁለት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አሥመራ የገቡት ሐሙስ ነበር።

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በፍጥጫ የቆየውን ግንኙነት ለማሻሻል ያስቻለውንና ፈር ቀዳጅ የተባለውን የመጀመሪያ ጉዟቸውን ወደ አሥመራ ካደረጉ ከአንድ ዓመት በኋላ የተደረገ ነው።

መስመር ያልያዘው የኢትዮ-ኤርትራ የንግድ ግንኙነት ወዴት ያመራል?

ይህንን ጉብኝት በተመለከተ የኤርትራ መንግሥት ቴሌቪዥን ባሳየው ምስል ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ከልኡካን ቡድናቸው ጋር በአሥመራ ጎዳናዎች ላይ በእግራቸው ሲጓዙ፤ ከዚያም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መኪና እያሽከረከሩ ከሁለቱ መሪዎች የጉብኝቱ አካል የሆኑ ስፍራዎችን እየተዘዋወሩ ሲመለከቱ ያሳያል።

ይህ ቪዲዮም በተለያዩ የማህበራዊ መገናኛ ዘርፎች ላይ በስፋት እየተዘዋወረ ሲሆን የተለያዩ ሰዎችም በቪዲዮው ላይ አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው።

ናቲ ብርሃኔ ይፍሩ የተባሉት ግለሰብ በትዊተር ላይ እንዳሰፈሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንግዳ ሆነው ሳለ ስለምን አስተናጋጁን ፕሬዝዳንት አሳፍረው እንደሚያጓጉዙ ይጠይቅና፤ ኤርትራ የተረጋጋች መሆኗን ለማሳየት የተደረገ ገጽታ ግንባታ እንደሆነ ይጠቅሳል።

ሁለቱ ሃጋራት ባለፈው ዓመት ግንኙነታቸውን ለማሻሻል የሚጠቅሙ የተለያዩ ስምምነቶችን የተፈራረሙ ቢሆንም የአየር መጓጓዣ አገልግሎት መልሶ መጀመሩና ኤምባሲዎቻቸውን መልሶ ከመክፈት ባሻገር ጉልህ የሆነ እንቅስቃሴ እስካሁን አልታየም።

በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ንግድ ተጧጡፏል

አንዳንዶች በዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ባለፈው ዓመት የተጀመሩትን ሥራዎች ወደተግባር ለመቀየርና በሌሎች ጉዳዮችም ላይ በጋራ ለመስራት ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ።

በሁለቱ ሃገራት መካከል ያሉት የድንበር መተላለፊያዎች ለተወሰነ ጊዜ ተከፍተው ነጻ የሰዎችና የሸቀጦች ዝውውር የነበረ ሲሆን አሁን ግን መዘጋታቸውን የድንበር አካባቢ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

በተጨማሪም ለሁለቱ ሃገራት ደም አፋሳሽ ጦርነት ምክንያት የሆነችው ባድመን በተመለከተ የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በሰጠው ውሳኔ መሰረት እስካሁን ኢትዮጵያ ቦታውን ለኤርትራ እንዳለቀቀች ይነገራል።

ነገር ግን የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረመስቀል በሁለቱ ሃገራት መካከል እየተካሄደ ያለው ግንኙነት ጠንካራና በሂደት ላይ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።