የብሪታኒያ አየር መንገድ ወደ ካይሮ የሚያደርገውን በረራ አቋረጠ

ተሳፋሪዎች በሂትሮ አየር ማረፊያ Image copyright @Ael_sheikh
አጭር የምስል መግለጫ በረራው የተሰረዘባቸው ተሳፋሪዎች በረራው የተቋረጠበትን ምክንያት የሚያስረዳ ደብዳቤ ከአየር መንገዱ ተቀብለዋል።

የብሪታኒያ አየር መንግድ (ብሪቲሽ ኤርዌይስ) ''ለደህንነት ሲባል'' ወደ ካይሮ ግብጽ የሚደርገውን በረራ ለአንድ ሳምንት ያክል አግጄያለሁ ሲል አስታወቀ።

ተጓዦች ለንደን ሂትሮ አየር ማረፊያ ከደረሱ በኋላ የብሪታኒያ አየር መንገድ ወደ ካይሮ የሚያደርገው በረራ መሰረዙ እና ለአንድ ሳምንት ያክል ተለዋጭ በረራ እንደሌላ ተነግሯቸዋል።

አየር መንገዱ በረራውን ለአንድ ሳምንት ለመሰረዝ ያደረሰው የደኅንነት ስጋቱ ምንነት በዝርዝር አልገለጸም።

የካይሮ አየር ማረፊያ ቃል አቀባይ ከአየር መንገዱ ማብራሪያ እየጠበቁ እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የብሪታኒያ አየር መንገድ ቃል አቀባይ በሰጡት መግለጫ ''በመላው ዓለም በሚገኙ መዳረሻ አየር ማረፊያዎች ላይ የደኅንነት ምርመራ እናደርጋለን። ወደ ካይሮ የምናደርገውን በረራም ለአንድ ሳምንት ያክል የሰረዝነው አስፈላጊውን የደኅንነት ምርመራ ለማድረግ ጊዜ ለማግኘት ነው። የደንበኞቻችን እና የሥራተኞቻችን ደኅንነት ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው። ደኅንነት እስካልተረጋገጠ ድረስ በረራ አናደርግም'' ብለዋል።

የጀርመኑ አየር መንገድ የሆነው ሉፍታንዛ በተመሳሳይ መልኩ ወደ ካይሮ የሚያደርገውን በረራ ትናንት ሰርዞ የነበረ ሲሆን ከዛሬ እሑድ ጀምሮ ግን በረራዎቹ እንደሚቀጥሉ አስታውቋል።

ከነመንገደኞቹ የጠፋው አውሮፕላን ሳይገኝ ቀረ

ልብ የረሳው አውሮፕላን

ሰባኪው አውሮፕላን ግዙልኝ አለ

የዩናይትድ ኪንግደም የውጪ ጉዳይ ቢሮ ወደ ግብጽ ለሚጓዙ እንግሊዛውያን የጉዞ ደኅንነት መረጃን አውጥቷል።

በውጪ ጉዳዩ ቢሮ ገጽ ላይ ''በአቪዬሽን ላይ ለመፈጸም የታቀደ ሽብር ስለመኖሩ ከፍተኛ ጥርጣሬ አለ። ከግብጽ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም በሚደረጉ በረራዎች ላይ ከፍተኛ ምረመራ ይካሄዳል'' የሚል መልእክትን አሰፍሯል።

2015 ላይ የሩሲያ አየር መንገድ አውሮፕላን ከግብጽ ከተነሳ በኋላ አየር ላይ ሳለ በውስጡ የነበረ ቦምብ ፈንድቶ በርካቶች መሞታቸው ይታወሳል። ይህን ጥቃት ተከትሎም የብሪታኒያ አየር መንገድን ጨምሮ በርካታ አየር መንገዶች ወደ ግብጽ የሚያደርጉትን በረራ አቋርጠው ነበር።

በብሪታኒያ አየር መንገድ ወደ ካይሮ ለመብረር ትኬት ቆርጠው ከአየር ማረፊያ የተገኙ ተሳፋሪዎች በረራው በመሰረዙ እና ከአየር መንገዱ የተሰጣቸው አገልግሎት ደካማ መሆኑ እጅጉን እንዳበሳጫቸው ቃላቸውን ለቢቢሲ የሰጡ ተሳፋሪዎች ተናግረዋል።

የ70 ዓመቷ ክርስቲን ሼልቦርን ከልጅ ልጇ ጋር ወደ ካይሮ ለመጓዝ ከበረራው ጥቂት ሰዓታት ቀድም ሂትሮ አየር ማረፊያ እንደደረሰች ትናገራለች። አውሮፕላን ለመሳፈር የሚያስችላት የይለፍ ወረቀት (ቦርዲንግ ፓስ) ማግኘት ብትችልም የአየር ማረፊያ መተላለፊያ በሮችን አልከፍት እንዳላት ታስረዳለች።

Image copyright Christine Shelbourne
አጭር የምስል መግለጫ ክርስቲን ሼልቦርን

''የአየር መንገዱ ሠራተኞች የተፈጠረውን ነገር የሚያውቁ አይመስለኝም'' የምትለው ክርስቲን ቀጣዩ በረራ ከአንድ ሳምንት በኋላ እንደሚደረግ ሲነግሩኝ 'በጣም ተበሳጫሁ' ትላለች።

ሌለኛው ተሳፋሪ ማይክል ካህሊል የማልቀርበት ጉዳይ ስላለኝ በሌላ አየር መንገድ ከለንደን ወደ ካይሮ ለመብረር £1200 (43 ሺህ ብር በላይ) ለመክፍል ተገድጄያለሁ ይላል።