አፖሎ 11፡ የሰው ልጅ ጨረቃ ላይ የተራመደበት 50ኛ ዓመት እየታሰበ ነው

ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው ዋሽንግተን መታሰቢያ ሃውልት ላይ ከአፖሎ 11 የተወሰዱ ምሥሎች ለዕይታ ቀርበዋል። Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው ዋሽንግተን መታሰቢያ ሃውልት ላይ ከአፖሎ 11 የተወሰዱ ምሥሎች ለዕይታ ቀርበዋል።

የሰው ልጅ ለመጀመሪያ ግዜ ጨረቃ ላይ የተራመደበት 50ኛ ዓመት እየታሰበ ነው።

እ.አ.አ. ጁላይ 20፣ 1969 ኦፖሎ 11 መንኮራኮር በጨረቃ ላይ አረፈች። ከሰዓታት በኋላም ኒል አርምስትሮንግ በጨረቃ ላይ በመራመድ የመጀመሪያው ሰው ሆነ።

ናሳ የሰው ልጅ ለመጀመሪያ ግዜ ጨረቃ ላይ የተራመደበትን 50ኛ ዓመትን ምክንያት በማድረግ፤ በወቅቱ አፖሎ 11ን ሲያስወነጭፍ የሚያሳይ ምስል ለቋል።

ይህን ታሪካዊ ሁነት ከ50 ዓመታት በፊት በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት ከግማሽ ቢሊዮን ሰዎች በላይ ተመልክተውት ነበር።

የአፖሎ 11 መንኮራኩር ተቆጣጣሪ ኒል አርምስትሮንግ ከሦስት ቀናት በረራ በኋላ ከሁለት ባልደረቦቹ ጋር ጨረቃ ላይ ሲደርሱ ''ሂይውስተን፤ ንስሯ አርፋለች'' ሲል ተናግሮ ነበር። ሂውስተን በቴክሳስ ግዛት የምትገኝ የጠፈር ማዕከል ናት።

የመንኮራኩሯ የምድር ላይ ተቆጣጣሪ የነበረው ቻርሊ ዲዩክ በበኩሉ ለኒል አርምስትሮንግ ምላሽ ሲሰጥ ''ከምድር ሆነን ሰምተንሃል። በርካታ ባልደረቦችህ ይህን ማመን ተስኗቸዋል። እየተነፈስን ነው'' ብሎት ነበር።

ወደ ጠፈር በመሄድ የመጀመሪያው ይሆን የነበረው አፍሪካዊ በሞተር አደጋ ሞተ

የብሪታኒያ አየር መንገድ ወደ ካይሮ የሚያደርገውን በረራ አቋረጠ

ኢራንና እንግሊዝ ተፋጠዋል

በ82 ዓመቱ እ.አ.አ 2012 ላይ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው አሜሪካዊው ጠፈርተኛ በጨረቃ ላይ የመጀመሪያ እርምጃውን እንዳደረገ ''ይህ ለአንድ ሰው ኢምንት እርምጃ ነው፤ ለሰው ልጆች ግን ግዙፍ ከፍታ ነው'' ሲል ተናግሮ ነበር።

አርምስትሮንግ በዝ አልደሪን እና ማይክል ኮሊንስ ከሚባሉ ሁለት ባልደረቦቹ ጋር ነበር ወደ ጨረቃ ጉዞውን ያደረገው። ሦስቱም ጠፈርተኞች እ.አ.አ. 1930 ላይ የተወለዱ ሲሆን የአርምስትሮንግ ሁለቱ ባልደረቦች አሁንም በሕይወት ይገኛሉ።

አልደሪን ጨረቃ ላይ በመራመድ ሁለተኛው ታሪካዊ ሰው ነው።

Image copyright PA Media
አጭር የምስል መግለጫ በዝ አልደሪን ጨረቃ ላይ በመራመድ ሁለተኛው ታሪካዊ ሰው ነው።

ሌላኛው ጠፈርተኛ ማይክል ኮሊንስ ለፎክስ ኒውስ ሲናገር ''የተረጋጋ ሕይወት ነው የምመራው። አመሻሽ ላይ ሁሉም ወደ የመኝታው ሲያመራ እኔ የእግር መንገድ ማድረግ አዘወትራለሁ። በዛ ጭለማ ወደ ላይ ቀና ብዬ እመለከታለሁ። ከዚያም 'ኦ ጨረቃ። እዛ ላይ ነበርኩ' ብዬ ለእራሴ 'ነግረዋለሁ'' ብሏል።

የሰው ልጅ ጨረቃ ላይ የተራመደበት 50ኛ ዓመትን ለማሰብ በርካታ የዓለማችን ከተሞች የተለያዩ መርሃግብሮችን እየከወኑ ነው።

በሂውስተን ቴክሳስ የአየር ኃይሉ አባላት በሙዚቃ ባንድ ታጅበው የአየር ላይ ትርዒት አሳይተዋል።

ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው እስሚዞኒያንስ የአየር እና ጠፈር ሙዚያም ደግሞ ኒል አርምስትሮንግ ለብሶት የነበረውን የጠፈር ልብስ እና ከጨረቃ የመጡ ቁሶችን ለዕይታ አቅርቧል።

በሲያትል የሚገኘው የበረራ ሙዚያም ደግሞ ከ50 ዓመታት በፊት ጠፈርተኞቹን ጨረቃ ላይ ሲያርፉ የሚያሳይ ምሥልን ለዕይታ አቅርቧል።

Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ ኒል አርምስትሮንግ ጨረቃ ላይ ለመጀመሪያ ግዜ ሲረመድ ለብሶት የነበረው ልብስ።

በፓሪስ የሚገኘው ግራንድ ፓላይስ የጨረቃው ጉዞ ላይ ትኩረት የሚያደርግ ኤግዚብሽን ለዕይታ አቅርቧል።

የስፔን አርቲስቶችም ግዙፍ ምሥለ ጨረቃ ቀርጸው በማድሪድ ለዕይታ አቅርበዋል።

ተያያዥ ርዕሶች