ኢራንና እንግሊዝ በሆርሙዝ ወሽመጥ ተፋጠዋል

በጂብራልተር የተያዘው የኢራን መርከብ ለሶሪያ ድፍድፍ ነዳጅ እንደጫነ ይገመታል Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ በጂብራልተር የተያዘው የኢራን መርከብ ለሶሪያ ድፍድፍ ነዳጅ እንደጫነ ይገመታል

የዩናይድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢራን በሕገ-ወጥ መንገድ የያዘቻትን መርከብ በአስቸኳይ እንድትለቅ አሳስቡ።

የውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ጄረሚ ሀንት እንዳሉት በሆርሙዝ ወሽመጥ የመርከቢቱ መያዝ የደኅንነት ጥያቄን የሚያጭር ነው።

ዛሬ ኢራን የለቀቀችው ቪዲዮ አርብ ዕለት መርከቡ በቁጥጥር ሥር በዋለበት ጊዜ የነበረውን ሁኔታ ያሳየ ነው።

ኢራን በበኩሏ መርከቡን የያዝኩት የዓለም የባሕር ትራንስረፖት ደንብን የጣሰ ተግባር በመፈጸሙ ነው ብላለች።

የእንግሊዙ የውጭ ጉዳይ ለኢራኑ አቻቸው ስልክ ከመቱ በኋላ በሰጡት አጭር ጋዜጣዊ መግለጫ ኢራን ድርጊቱን የፈጸመችው በጂብራልታር የተያዘባትን መርከብ ለማስለቀቅ እንደመያዣ በመውሰድ ነው ብለዋል።

በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ያለው ሁኔታ ወደ ሙሉ ጦርነት እንዳያመራ ከፍተኛ ሥጋትን ፈጥሯል።

እንግሊዝ የነዳጅ መርከቧ በኢራን በመታገቱ ስጋት ገብቷታል

የፈረንሳይ ጦር ደራሲያንን "የወደፊቱን ተንብዩልኝ" አለ

ስቴና ኢምፔሮ በኢራን ልዩ የአብዮታዊ ዘቦች የተያዘው አርብ ዕለት ነበር።

ኢራን በለቀቀችው ተንቀሳቃሽ ምሥል የልዩ ብርጌድ ወታደሮቿ ከሄሊኮፍተር ተንጠላጥለው ሲወርዱና መርከቡን በቁጥጥር ሥር ሲያውሉ ያሳያል።

ተንቀሳቃሽ ምሥሉን የለቀቀው በኢራን እንደሚደገፈው የሚጠረጠረው የፋርስ የዜና አገልግሎት ነው።

Image copyright Reuters

የእንግሊዝ ሮያል አየር ኃይል ደህንነት ጥበቃ ቡድን ስቴና ኢምፔሮ የተሰኘውን ንብረትነቱ የስዊድናዊያን የሆነውን ይህንን መርከብ በኢራን እንዳይያዝ እንዲያደርግ የይድረሱልኝ ጥሪ ቢደርሰውም በጊዜው ሊደርስ አልቻለም።

የኢራን ዜና አገልግሎት እንደሚለው መርከቡ የተያዘው አንድ የአሳ ማጥመጃ ጀልባን ገጭቶ ሊያመልጥ ሲል ነው።

ጀርሚ ሀንት እንደሚሉት ግን መርከቡ የተያዘው በኦማን የውሃ ክፍል እንጂ በኢራን አይደለም። ወደ ኢራን የውሃ አካል የደረሰውም ተገዶ ነው።

የእንግሊዝ ካቢኔ በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ ስብሰባ ያደረገ ሲሆን ዛሬ ወይም ነገ ምን እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ያሳውቃል።

የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጃቫድ ዛሪፍ በትዊተር ገጻቸው እንደጻፉት እንግሊዝ የአሜሪካ የኢኮኖሚ ሽብርተኝነትን አስፈጻሚ መሆኗን ማቆም ይገባታል ብለዋል።

የትራምፕ አስተዳደር በኢራን ላይ ግዙፍ ማዕቀብን ከጣለ በኋላ በገልፍ አካባቢ ከፍተኛ ውጥረት ሰፍኗል። ሁኔታዎች ከዲፕሎማሲ እጅ ወጥተው ወደ ለየለት ጦርነት እንዳያመሩም ተፈርቷል።